ለ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሶስተኛ እና የአራተኛ ዙር ጨዋታዎች ከጊኒ ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል ።
በጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ በግብ ጠባቂነት ሰይድ ሀብታሙን በተከላካይነት ሚለዮን ሰለሞን ፣ ያሬድ ባየህ ፣ አስቻለው ታመነ እና ሱሌማን ሀሚድ በአማካይ ስፍራ ጋቶች ፓኖም ፣ አማኑኤል ዮሐንስ ፣ ታፈሰ ሰለሞን ፣ ሽመልስ በቀለ እና ከነአን ማርክነህ በአጥቂነት ደግሞ አቤል ያለውን ተጠቅሟል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች በኩል ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት እና ከኋላ መስርተው ለመውጣት ሲጥሩ ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኩል ከአስቻለው እና ያሬድ በሚነሱ ኳሶች በአንድ ሁለት ቅብብል ኳሶችን ወደፊት ለማድረስ የሚያደርጓቸው ጥረቶች በቀላሉ ስኬታማ የሆኑ አልነበሩም ።
ቡድኑ ወደ ተጋጣሚው የመጨረሻ የማጥቃት ዞን ላይ የደረሰባቸው አጋጣሚዎች በግራ መስመር ያደለለ ነበር ። ምንም እንኳን በዚህ የሜዳ ክፍል ላይ የረመዳን ዩሰፍን አለመኖር ተከትሎ በቦታው የተሰለፈው ሚሊዮን ሰለሞን በድፍረት ወደ ተጋጣሚ የመጨረሻ ዞን በመድረስ ማጥቃቱን ሲያግዝ ባይታይም ከፊት ያሉ ተጫዋቾች ቦታ በመቀያየር በነበራቸው እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠሩ ሞክረዋል ።
ከግብ ሙከራዎች ርቆ በቆየው ጨዋታ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከከነአን ማርክነህ የደረሰውን ኳስ ሳይጠቀምበት ሲቀር ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም አቤል ያለው በተመሳሳይ ከታፈሰ ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ ሳይጠቀምበቶ ቀርቷል ።
የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን በአንፃሩ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ ሙከራዎችን በማድረግ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደከም ያለ አጋማሽ አሳልፈዋል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን በኩል ከግራ መስመር ወደ ግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ ሚሊዮን ሰለሞን ጨርፎት በራሱ ግብ ላይ ሊቆጠር የነበረ ቢሆንም የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል ። ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ሁሄዚ ፍሬድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳሶ በሰይድ ሀብታሙ ተይዟል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ጅማሮ ላይ የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ የተጠቀማቸውን ተጫዋቾች በሙሉ ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል ።
በአጋማሹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተለይም ቅያሪዎችን ካደረገበት ደቂቃ አንስቶ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል ። በተደረጉት ቅያሪዎችም ዮሴፍ ታረቀኝ እና ብርሀኑ በቀለ ታፈሰ ሰለሞንን እንዲሁም ሱሌማን ሀሚድን ተክተው ገብተዋል ።
በአዳማ ከተማ ባሳየው ድንቅ አቋም ለመጀመሪያ ጊዜ በብሄራዊ ቡድን ስብስብ የተካተተው ዮሴፍ ታረቀኝ በ72ኛው ደቂቃ ላይ ከአቤል ያለው የደረሰውን ኳስ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በሩዋንዳው ግብ ጠባቂው ግብ ከመሆን ድኗል ።
በቀጣዩ ቅያሪም ኪቲካ ጀማ ፣ ቢንያም በላይ እና ይሁን እንደሻው ሽመልስ በቀለ ጋቶች ፓኖምን እና አቤል ያለውን ቀይረዋል ።
ቢንያም በላይ ተቀይሮ በገባ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከአማኑኤል ዮሐንስ የተቀበለውን ግሩም ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ ቢሞክርም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችል ቀርቷል ።
በ84ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ ቢንያም በላይ ወደ ግብ ክልል አሻግሮ በሩዋንዳ ተከላካዮች ሲመለስ ያገኘው ከነአን ማርክነህ ኳሱን አረጋግቶ በመምታት ግብ አስቆጥሯል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የ1 ለ 0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጨዋታው ላይ የታዩትን ክፍተቶች በማረም ለወሳኙ የጊኒ ጨዋታ ለመቅረብ ጥረቶችን እንሚያደርጉ ተናግረዋል ።