በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በነገዉ ዕለት የምድባቸዉን ሶስተኛ ጨዋታ በሜዳቸዉ ባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም የሚያደርጉት ዋልያዎቹ ረፋድ 3:00 ላይ ከነገዉ ጨዋታ አስቀድሞ የመጨረሻ ልምምዳቸዉን መከወናቸዉ ይታወሳል። አመሻሽ 11:30 ላይ ደግሞ የዋልያዎቹ ዋና አስልጣኝ ዉበቱ አባተ ዝግጅታቸዉን እና የነገዉን ጨዋታ በተመለከተ በኩሪፍቱ ሪዞርት ለጋዜጠኞች ሀሳባቸዉን የሰጡ ሲሆን በሀሳባቸዉም ተከታዮቹን ተጥቦች አንስተዋል።
” እንደሚታወቀው ለሶስተኛ እና አራተኛ ዙር የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታችንን ነገ እና ማክሰኞ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የምናደርግ ይሆናል ፤ ለዚህም ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገን ከመስከረም 14 ጀምሮ ስንዘጋጅ ቆይተናል። ”
” በዝግጅታችን ወቅት አቅደን ከነበረዉ የወዳጅነት ጨዋታ አለመሳካት ዉጭ በሚገባ ለነገዉ እና ለማክሰኞዉ ጨዋታ ተዘጋጅተናል። ተጫዋቾቻችንም በጥሩ የመነሳሳት መንፈስ እና በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ ። ”
ከተጫዋቾች ከጥሪ ጋር ተያይዞ….
” እንደሚታወቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በጠራናቸዉ ጊዜ ልናገኛቸው አልቻልንም ነበር ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ከክለቡ ጋር በመነጋገር ተጫዋቾቹ በቶሎ ወደ ዝግጅት እንዲገቡ ተደርጓል። በተጨማሪም ዘግይቶ ተቀላቅሎን የነበረውን ታፈሰ ሰለሞን በዲሲፕሊን ምክንያት ቀንሰን በዛብህ መለዮን ወደ ስብስባችን ቀላቅለን ስንዘጋጅ ቆይተናል። ”
ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር ስላለበት ችግር…
” በእርግጥ ቡድን በአንድ ጀምበር የሚገነባ አይደለም ፤ ጎል ግን ከጨዋታዉ ጅማሮ አንስቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በየትኛውም ሰዓት ላይ ሊቆጠር ይችላል ከዛ በላይ ጎል ለማስቆጠር የምንሄድባቸዉን መንገዶች ለማረም እየሞከርን ነዉ። ምናልባት በሁለት ጨዋታ አንድ ጎል ማስቆጠራችን እንደችግር ሊታይ ይችል ይሆናል ፤ ነገር ግን የገጠምናቸዉን ቡድኖች ከግምት ዉስጥ ማስገባትም ተገቢ ነዉ። ”
” እዚህ ዉድድር ላይ የተገኘነዉ ከተሳትፎ በዘለለ ከምድባችን ለማለፍ ነዉ የምንጫወተው ለዛም የሚሆን ጥሩ ቡድን አለን። በተጨማሪም ከፊታችን ለሚጠብቀን የአፍሪካ ዋንጫ ዉድድርም ይህ የማጣሪያ ጨዋታ በብዙ መልኩ የሚረዳን ይሆናል ሂደቱን እና እንቅስቃሴዉንም እየተመለከትንበት ነዉ። ”
” በመጨረሻም የነገዉን ጨዋታ እንደየትኛዉም ጨዋታ ለማሸነፍ ነዉ ወደ ሜዳ የምንገባዉ ከዛ በዘለለ ግን ሂደቱ ላይ ነዉ የምናተኩረዉ። ”
አስተያየት ይስጡ