በአለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የምድቡን ሶስተኛ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ አቻዉ ጋር በባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ በድን 3ለ1 በሆነ ዉጤት ተሸንፏል።
በጨዋታው ጅማሮ የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ያክል ተጭነዉ መጫዎት የቻሉት ደቡብ አፍሪካዎች በተደጋጋሚ ወደ ዋልያዎቹ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን ፤ ገና ጨዋታዉ በተጀመረ በ7ኛዉ ደቂቃም ባፋና ባፋናዎቹ ከቀኝ መስመር ክሮስ የተደረገን ኳስ በግንባር ገጭተዉ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ኳሷ የአንግሉን አግዳሚ ታካ ወደ ዉጭ ወጥታለች። በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ደቡብ አፍሪካዎች የዋልያዎቹን ተከላካዮችን ሰብረዉ በመግባት ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም ነበር።
በተቃራኒው ባለሜዳዎቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደወትሮው ሁሉ ኳስን መስርተዉ ለመጫዎት ሲሞክሩ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን እንደከዚህ ቀደሙ ቅብብሎቻቸዉ የተሳኩ ናቸዉ ማለት አይቻልም ነበር ። በዚህ ሂደት የቀጠለዉ የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ በ38ኛዉ ደቂቃ ላይ በዋልያዎቹ የፊት መስመር ተጫዋች አቡበከር ናስር አማካኝነት ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ቢያገኙም አቡበከር ሊጠቀምበት አልቻለም። ከአማካዩ ሱራፌል ዳኛቸዉ የተሻገረለትን ኳስ ከተከላካዮች ጀርባ ሾልኮ በመግባት ወደ ግብ ቢልካትም የባፋና በፋናዎቹ ግብ ጠባቂ በአስደናቂ ብቃት አድኖታል። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም ተጨማሪ የግብ እድል አጊኝቶ የነበረዉ አቡበከር አሁንም በድጋሚ ወደ ግብ የላካት ኳስ ግብ ጠባቂዉን ዊሊያም ማለፍ አልቻለችም ነበር።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ተጠናቆ ተጨማሪ አንድ ደቂቃ አራተኛ ዳኛዉ ባሳዩበት ወቅት ነበር የመጀመሪያዋን ግብ ደቡብ አፍሪካዎች ማስቆጠር የቻሉት፤ ከግራ መስመር አካባቢ ያገኙትን ቅጣት ምት በቲቦኖ ሞኮና አማካኝነት በቀጥታ ወደ ግብ ሲልኳት የዋልያዎቹ ግብ ጠባቂ በቀላሉ ከተቆጣጠራት በኋላ አምልጣዉ ወደ ግብነት ልትቀየር ችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላም የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ዋልያዎቹ በተወሰነ መልኩ ተሻሽለው ኳስን በአንድ ሁለት ቅበብል በመጫዎት በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ለመድረስ ፍላጎት ቢኖራቸውም የባፋና ባፋናዎቹ የአማካይ እና የተከላካይ መስመርን አልፈዉ ወደ ግብ ክልላቸዉ መድረስ ሳይችሉ በአመዛኙ በመሀል ሜዳ ላይ ቅብብሎችን ሲያደርጉ ተመልክተናል።
በጨዋታዉ 55ኛ ደቂቃ ላይ ዋልያዎቹ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ደቡብ አፍሪካ የግብ ክልል አካባቢ ከደረሱ በኋላ አማኑኤል ገ/ሚካኤል አክርሮ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ተከላካዩ ተደርቦ ቢመልሰዉም የዋልያዎቹ ተጫዋቾች በእጅ ተነክቷል በሚል የዕለቱ ዳኛ ላይ ቅሬታ ቢያቀርቡም የዕለቱ ዳኛ ግን ጨዋታዉን አሰልጣኝ ቀጥለዋል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም ዋልያዎቹ ሱራፌል ዳኛቸዉ ላይ በተሰራ ጥፋት 67ኛዉ ደቂቃ ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት አጥቂዉ ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ዋልያዎቹን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር።
በተደጋጋሚ በረጃጅም ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ የቆዩት ደቡብ አፍሪካዎች ጌታነህ ከበደ ግብ ካስቆጠረ ከደቂቃዎች በኋላ በዋልያዎቹ ተጫዋቾች መዘናጋት ምክንያት በሞቫላ ሞዞቢ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ቻሉ።
በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቀይረዉ ወደሜዳ በማስገባት ጨዋታዉን ለመቀየር ያሰቡት አሰልጣኝ ዉበቱ ዉጥናቸዉ ሰምሮ ጨዋታዉን በፈለጉት መንገድ መቆጣጠር ባይችሉም ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ደቡብ አፍሪካዎች የግብ ክልል በመድረስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በተቃራኒዉ የጨዋታውን ፍጥነት በማቀዝቀዝ ሰዓት ለማባከን ሲሞክሩ የነበሩት ባፋና ባፋናዎቹ በ90ኛዉ ደቂቃ ላይ በመጎባ ኤቪዮንስ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ጨዋታዉን 3ለ1 በሆነ ዉጤት አሸንፈዋል።