በቀጣዩ በፈረንጆቹ አዲስ አመት ለሚደረገዉ 33ኛዉ የአፍሪካ ዋንጫ ከስምንት አመታት በኋላ የተመለሰዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ተጋጣሚዎቹን በትላንትናው እለት ማወቁ ይታወሳል።
24 ሀገራት የሚሳተፉበት ትልቁ የአህጉራችን ዉድድር ከቀጣዩ አመት ጥር 1 እስከ 29 (ጃኑዋሪ 9- ፌብርዋሪ 6) ድረስ በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚደረግ ይሆናል።
በትላንትናው ዕለት በያዉንዴ እጣው ሲወጣም የወቅቱ የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪክ ሙሴፔን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የእግርኳስ ፌዴሬሽን የበላይ አመራሮች፣ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስፍራው የታደሙ ሲሆን፤ በተጨማሪም ሳሙኤል ኢቶ፣ ዲዲየር ድሮግባ እና ኦሳሙዋ ጂያንን የመሳሰሉ የቀድሞ ተጫዋቾችም በስነስርዓቱ ላይ በመታደም ዕጣ ማዉጣት ችለዋል።
24 ተሳታፊ ሀገራት በስድስት ምድብ ተከፍለዉ ዉድድራቸዉን እንዲከዉኑ እጣ የወጣላቸዉ ሲሆን ፤ በዚህም መሰረት ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶ እና ኬፕ ቨርዲ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያውን ጨዋታ በዕለተ እሁድ ጥር 1/2021 ከኬፕ ቨርዲ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

አስተያየት ይስጡ