የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድር ዝግጅቱን ምን እንደሚመስል በዚህ መልኩ ዳሰነዋል።

አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የአምስተኛ አመት ቆይታቸውን በሚያደርጉበት የ2019 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቻምፒዮን ከሆነበት 2016 በኋላ ባሉት ተከታታይ አመታት በሊጉ መሐል ሰፋሪ ሆኖ በደረጃ ሰንጠረዡ ሲያሳልፍ ስንመለከተው ቆይተናል። ያለፈውን አመት የቡድኑን ውጤት ስንመለከት ካደረጋቸው 38 ጨዋታዎች 11 አሸንፈው 14 አቻ ውጤቶችን በማስመዝገብ 13 ሽንፈቶችን ደግሞ አስተናግዶ በሊጉ ከፍተኛ የተባለውን 45 ጎል አስቆጥሮ በተቃራኒው የሊጉንም ከፍተኛ 45 ጎል አስተናግዶ በ47 ነጥቦች ያለምንም የግብ ክፍያ 13ኛ ላይ በመቀመጥ ማጠናቀቁ የሚታወሰው የቡድኑ ውጤት ነው።
ላለፉት ጥቂት አመታት ቡድኑ ከነበረበት ውጤት ተሻሽሎ መገኘትን ምርጫው ለማድረግ በክረምቱ ጥረቱን የጀመረው ክለቡ ልምድ ያላቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች ከፕሪምየር ሊግ እና ከታችኞቹ የሊግ ዕርከኖች በድምሩ 13 ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን መገንባት ችሏል። አማካዩ ሙሉቀን አዲሱን ከወላይታ ድቻ ፣ ተከላካዩ ጊት ጋትኩትን ከመቐለ 70 እንደርታ ፣ አጥቂው ፍፁም ጥላሁንን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ የመስመር አጥቂው ጫላ ተሺታን ከሀድያ ሆሳዕና ፣ አጥቂው አቤል ማሙሽ ከምድረገነት ሽረ ፣ አማካዩ እዮብ ተስፋዬ ከወላይታ ድቻ ፣ አማካዩ አናንያ ጌታቸው ከባህርዳር ከተማ ከአንደኛ ሊግ ተከላካዩ ፉዓድ እድሪስ እና አጥቂው ሌዊ ሎኛ ከፉሪ ክ/ከተማ እንዲሁም በረከት ከቢሾፍቱ እና አጥቂው የአንደኛ ሊጉ ኮከብ ጎል አግቢ መስፍን አየለ ደግሞ ከቦሌ ክፍለከተማ ከውጪ ተከላካዩ ዴቪድ ኦፖንግ ከሀገሩ ጋና ህርትስ ኦፎክ እና ሴራሊዮናዊው አማካይ ሰይዱ ካማራ ደግሞ ቢኦ ሬኖጀርስ የፈረሙ አዳዲስ ፈራሚዎች ሲሆኑ ኤፍሬም ሌጋሞ ፣ አዲሱ መገርሳ ፣ ሳምሶን ቹቹ ፣ አብዱላዚዝ መሐመድ ፣ ብሩክ ብፁአምላክ ፣ ዮናስ ለገሠ ፣ ተስፋዬ ታምራት ፣ ቢኒያም ካሳሁን ፣ ዘላለም አበበ አማኑኤል ደስታ ፣ ዮሐንስ ኪዳኔ እና ዩጋንዳዊው አጥቂ ሳይመን ፒተር በክለቡ ውል የታደሰላቸው ነባር 12 ተጫዋቾች ናቸው።
በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ቡድኑ እየተመራ ከነሀሴ 15/2018 አንስቶ አዳማ ከተማ ላይ የልምምድ ጊዜያቸውን ያሳለፉት ሀምራዊ ለባሾቹ በወዳጅነት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን 3ለ2 ሲረቱ በባህርዳር ከተማ 2ለ1 በኢትዮጵያ መድን 1ለ0 ሲሸነፍ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1ለ1 የአዳማ ከተማ የስብስብ ቡድንን 4ለ0 በማሸነፍ የልምምድ ጊዜያቸውን አገባደው በቀጣዩ ዕሁድ በሀዋሳ በሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ሲዳማ ቡናን ከሜዳቸው ውጪ ተጉዘው በመግጠም አመቱን ይጀምራሉ።
አስተያየት ይስጡ