በስምንተኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ የተገናኙት መከላከያ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታቸውን ያለምንም ግብ አጠናቀዋል ።
መከላከያ በሰባተኛው ሳምንት በሀድያ ሆሳዕና በነበረው ጨዋታ ላይ በቋሚ አሰላለፍ ከተካተቱት ተጫዋቾች አራት ቅያሪዎችን በማድረግ ቢንያም ላንቃሞ ፤ ዳዊት ወርቁ ፤ ብሩክ ሰሙ እና አቤል ነጋሽን ጨዋውን እንዲጀምሩ ሲያደርጉ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ በፋሲል ከተማ በሰፊ ውጤት በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አስራ አንድ በተመሳሳይ የአራት ተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ተጫዋቾቹም ጊት ጋትኩት ፤ መሀሪ መና ፤ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ዳዊት ተፈራ ናቸው ።

የጨዋታው የመጀመሪያው ኢጋማሽ ቀዝቃዝ ብሎ የተካሄደ የነበረ ሲሆን በአብዛኛው ደቂቃዎች ኳሶችን የመነጣጠቅ አባዜ በስፋት ያሳመለከተ ነበር ። ሁለቱም ክለቦች ኳሱን ይዘው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በሚገቡበት ጊዜ የሚያደርጓቸው ቅብብሎች የተሳኩ አለመሆን አጋማሹ በግቦች እና በግብ ሙከራዎች የታጀበ እንዳይሆን አድርጎታል ። በተለይም ከውሀ እረፍት በኋላ ሲዳማ ቡና በተሻለ በመንቀሳቀስ ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉበት ነበር ምንም እንኳን የመከላከያን የተከላካይ መስመር ሰብረው በመግባት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም ።

የጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የተደረገው በመከላከያ በኩል ሲሆን አቤል ነጋሽ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ቢንያም በላይ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ተመልሶበታል ። የሲዳማ ቡናዎቹ ፍሬው ሰለሞን ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ዳዊት ተፈራ በሚያደርጓቸው ጥሩ ቅብብሎች ወደ ግብ ክልል ለመድረስ በተደጋጋሚ ጥረቶችን ማድረግም ችለው ነበር ።
የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ያኩቡ መሀመድ ኳሱን ለቡድን አጋሮቹ ለማቀበል በሚጥርበት ጊዜ አቤል ነጋሽ ነጥቆት የግብ ሙከራ አድርጎ በተክለማርያም የተመለሰበት ሲሆን የተመለሰውንም ኳስ በድጋሚ ለመጠቀም ሲሞክር ጊት ጋትኩት ደርሶ የማዕዘን ምት አድርጎታል ።

በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡና ከፍተኛ የበላይነት በመውሰድ ጨዋታውን ያደረጉ ሲሆን በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ከቀኝ መስመር በቴዎድሮስ ታፈሰ አማካኝነት ወደ ግብ ክልል በሚሻገሩ የአየር ላይ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። በመከላከያ በኩል በሚነጠቁ ኳሶች ፈጣን እና ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም ጥረቶችን ያደረጉበት ሲሆን 65ኛ ደቂቃ ላይ መከላከያዎች በመሀል ላይ የነጠቁትን ኳስ ቢንያም በላይ ተቀይሮ ለገባው አኩየር ቻም በግሩም ሁኔታ ያደረሰው ሲሆን በሳጥን ውስጥ የነበረው ቻም ኳሱን ወደ ግብ ለመምታት በሚሞክርበት ጊዜ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጊት ጋትኩት ከኋላው መጥቶ ኳሱን ተንሸራቶ አውጥቶበታል ።

ጨዋታው ከ75ኛ ደቂቃ በኋላ ቀደም ብሎ ከነበረው በተሻለ ፍጥነት እና በተሻሉ የግብ ዕድሎች ተካሂዷል ። 78ኛ ደቂቃ ላይ በሲዳማ ቡና በኩል በግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት መሀሪ መና ተቀብሎ በፍጥነት ወደ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያደረገው የግብ ሙከራ በክሌመንት ቦዬ ተመልሷል ። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተለይም የአቤኔዘር አስፋው ተቀይሮ መግባትን ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ፊት ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉባቸውን አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር ። መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ እያለ ይገዙ ቦጋለ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ሞክሮ ክሌመንት ቦዬ ሲመልሰው በቅርብ የነበረው ፍሬው ሰለሞን ኳሱን ቢያገኘውም ተረጋግቶ ባለመምታቱ ኳሱ ወደ ውጪ ሊወጣበት ችሏል ። ጨዋታዉም ፍፃሜውን 0 ለ 0 አደረገ ።

ውጤቱን ተከትሎም መከላከያ ነጥቡን ወደ 11 በማድረስ ደረጃውን ወደ 7ኛ ከፍ ያደረገ ሲሆን ሲዳማ ቡና ደግሞ ነጥቡን 8 በማድረስ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ 12ኛ መምጣት ችሏል ።

አስተያየት ይስጡ