መነሻ ገጽ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ዘገባ | ተመስገን ዳና በወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግወልቂጤ ከተማዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባጅማ አባጅፋር

የጨዋታ ዘገባ | ተመስገን ዳና በወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል

አጋራ
አጋራ

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጨረሻ ቀን ውሎ ቀን 10:00 ጀምሮ የተደረገው ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ 3 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቋል ።

ጅማ አባጅፋሮች በ13ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን ሲረቱ በተጠቀሙት ምርጥ 11 ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የገቡ ሲሆን በተመሳሳይ ወልቂጤ ከተማም በሳምንቱ ከሲዳማ ቡና አቻ ሲለያዩ የነበረውን ቋሚ አሰላለፍ ላይ ለውጥ ሳያደርጉ ገብተዋል ።የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በአመዛኙ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በሁለቱም በኩል ወደ ግብ ደርሰው የግብ ሙከራዎችን በማድረጉ ረገድ ደከም ብለው የታዩበት ነበር ።

በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ 7ኛው ደቂቃ ላይ በአብዱልከሪም ወርቁ የተደረገ ሲሆን ከጌታነህ ከበደ የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው አላዛር ሽመልስ አድኖበታል ። በአንፃራዊነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ጅማ አባጅፋሮች ሲሆኑ ቀዳሚ የግብ ሙከራቸውን ለማድረግ ግን 28 ያህል ደቂቃዎችን ጠብቀዋል ። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ከሳጥን ቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ተጨርፎ የግቡ አግዳሚ መልሶታል ።38ኛው ደቂቃ ላይ የወልቂጤ ከተማው የቀኝ መስመር ተከላካይ ተስፋዬ ነጋሽ እየገፋ ይዞ የሄደውን ኳስ ከርቀት ወደ ግብ በመምታት ያስቆጠረው ሲሆን የአላዛር ሽመልስ ግቡን ለቆ መውጣት ለግቡ አስተዋጽኦ አበርክቷል ። ከሶሰት ደቂቃዎች በኋላም በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ከቅጣት ምት ወደ ግብ የላኩት ኳስ በአላዛር ተይዟል ።

ቀደም ብሎ ጥሩ የግብ ሙከራ አድርጎ የነበረው ዳዊት እስጢፋኖስ ከተመሳሳይ ቦታ ላይ 41ኛው ደቂቃ ላይ ያደረገው የግብ ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። የመጀመሪያው አጋማሽም  በወልቂጤ መሪነት ተጠናቋል ።

ሁለተኛው የጨዋታው አጋማሽ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የደርሱበት በርካታ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት እና ከነዛም ውስጥ አምስቱ ወደ ግብነት የተቀየሩበት ነበር ።

በአጋማሹ የነበረው የመጀመሪያ ሙከራ በወልቂጤ ከተማ በኩል የተደረገ ሲሆን ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ተይዞበታል ።
የማጥቃት ክፍላቸውን ለማጠናከር ሶሰት ያህል ቅያሪዎችን አድርገው የገቡት ጅማ አባጅፋሮች በቀኝ መስመር በኩል በሚነሱ ኳሶች በተደጋጋሚ የወልቂጤ ከተማን የተከላካይ ክፍል መረበሽ ችለዋል ።

47ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ምስጋናው መላኩ ለመሱድ መሀመድ ጥሩ ኳስ ቀንሶለት የነበረ ቢሆንም መሱድ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን አልፎ ሊቆጠር ሲል ተስፋዬ ነጋሽ አውጥቶታል ። ጅማ አባጅፋሮች ወደፊት ገፍተው በሚወጡበት ጊዜ ከኋላ የሚተዋቸው ክፍት ቦታዎች በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለማግኘት እየሞከሩ ለነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ጥሩ አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ነበሩ ።

በ61ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ተከላካይ እያሱ ኳስ ለማቀበል ሲሞክር ኳሱን ያገኘው ጫላ ተሺታ የግብ ጠባቂውን መውጣት በመመልከት ከፍ አድርጎ ወደ ግብ የላከው ኳስ በአላዛር አናት ላይ አልፎ ግብ ሆኗል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ጅማ አባጅፋሮች ከቀኝ መስመር በተነሳ ኳስ በምስጋናው መላኩ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት በሰይድ ሀብታሙ ተመልሷል ።

በ69ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤ ከተማዎች በግራ መስመር ወደ ሳጥን ይዘው የገቡት ኳስ በጫላ ተሺታ እና ጌታነህ ከበደ በኩል አልፎ በያሬድ ታደሰ አማካኝነት ግብ ሆኗል ። በሶስት ጎል ልዩነት እየተመሩ የነበሩት ጅማ አባጅፋሮች ከግቡ መቆጠር ደቂቃዎች በኋላ በፈጣኑ አጥቂያቸው በመሀመድኑር ናስር ያደረጉት የግብ ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሷል ።

84ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ከዱላ ሙላቱ የደረሰውን ኳስ ከመረብ በማዋሀድ ጅማ አባጅፋሮችን በተወሰነ መልኩ ያነቀቃ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ 90+1 ላይ ሲደርስም መሀመድኑር ናስር ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጅማ አባጅፋር ሁለተኛ ግብ ሆኗል ። በቀሩት ደቂቃዎች ጅማ አባጅፋሮች ሌላ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው ተፈፅሟል ።ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን 20 በማድረስ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ጅማ አባጅፋር በበኩሉ በ10 ነጥብ በነበረበት 15ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።

በ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጅማ አባጅፋር መከላከያን ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ወላይታ ድቻን የሚገጥሙ ይሆናል ።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...