በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በቀዳሚነት ከረፋድ 4:00 ጀምሮ የተደረገው የጅማ አባጅፋር እና የሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ ዳዊት እስጢፋኖስ በድንቅ ሁኔታ ባስቆጠረው ግብ ጅማ አባጅፋር 1 – 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል ።
ጅማ አባጅፋር በ25ኛው ሳምንት ከአዲስ አበባ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ስድስት ለውጦችን በማድረግ አላዛር ማርቆስ ፤ በላይ ዓባይነህ ፤ አካሉ አትሞ ፤ ተስፋዬ መላኩ ፤ አስጨናቂ ፀጋዬ ፤ ዳዊት እስጢፋኖስ እና አድናን ረሻድን በወንድማገኝ ማርቆስ ፤ የአብስራ ሙሉጌታ ፤ ኢዳላሚን ናስር ፤ ሱራፌል ዐወል ፤ ሙሴ ከበላ እና ዱላ ሙላቱ ምትክ ሲያሰልፉ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከወልቂጤ ከተማ አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ሶስት ለውጦቶችን በማድረግ በፍሬዘር ካሳ ፤ ተስፋዬ አለባቸው እና ራምኬል ሎክ ምትክ ቃልአብ ውብሸት ፤ ኡመድ ኡክሪ እና ባዬ ገዛኸኝን ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጅማ አባጅፋሮች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ሆነው መጀመር ቢችሉም ሀድያ ሆሳዕናዎች ብዙም ሳይቆዩ ወደ ጨዋታው በመመለስ የተሻለ እንቅስቃሴን ማድረግ ችለዋል ።

ጅማ አባጅፋሮች 5ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ ሊሆኑ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠርም ችለው ነበር ። መስዑድ መሀመድ ከተነጠቀ ኳስ ያገኘውን አጋጣሚ በቀጥታ ከርቀት የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ወደ ግብ ልኮት የነበረውን ኳስ መሳይ አያኖ ለጥቂት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ተሽለው የቀረቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም የጅማ አባጅፋርን የመከላከል መስመር አልፈው ለመግባት ተቸግረው ነበር ።
በ13ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ አላዛር ማርቆስ ሲመልሰው ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሳምሶን ጥላሁን በተመሳሳይ ከርቀት
ያደረገውን ሙከራ በግብ ጠባቂው በድጋሚ ተመልሷል ። በተከታታይ ጥቃት የሰነዘሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በ20ኛው ደቂቃ ላይም የግብ ዕድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን ባዬ ገዛኸኝ በግራው የሳጥኑ አቅጣጫ ከሀብታሙ ታደሰ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ የግብ ዘቡ አላዛር ማርቆስ በድጋሚ አድኖታል ።

በተወሰደባቸው ጫና ወደ ኋላ ለማፈግፈግ የተገደዱት ጅማ አባጅፋሮች በ23ኛው ደቂቃ ላይ የግብ አጋጣሚን መፍርረ ችለው ነበር ። አስጨናቂ ፀጋዬ ለመሀመድ ኑር ያሻገረውን ኳስ ግርማ በቀለ በግንባር ገጭቶ ወደ ኋላ አልፎ የነበረ ቢሆንም መሳይ አያኖ እንደምንም ብሎ የማዕዘን ምት አድርጎታል ። ከውሀ እረፍት መልስ ጥሩ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ጅማ አባጅፋች በአንድ ሁለት ቅብብሎች የሀድያ ሆሳዕና ተከላካዮች አልፈው ለመግባት ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ። በዚህም 35ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ላይ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ መሳይ አያኖ በድጋሚ ግብ ከመሆን አድኖበታል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል ።
የሁለተኛው አጋማሽን ሀድያ ሆሳዕናዎች በጥሩ እንቅስቃሴ መጀመር ቢችሉም በ52ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ግብ አስተናግደዋል ። ጅማ አባጅፋሮች ከሳጥኑ ቅርብ ርቀት ያገኙትን የቅጣት ምት 10 ቁጥር ለባሹ ዳዊት እስጢፋኖስ በግሩም ሁኔት ከመረብ አዋህዶታል ።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በሙሉጌታ ምህረት የሚመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ጥረቶችን አድርገዋል ። ነገር ግን አላዛርን የፈተነ የግብ ሙከራ ለድረግ ደቂቃዎች መጠበቅ የግድ ብሏቸው ነበር ።
በ68ኛው ደቂቃ ሳምሶን ጥላሁን ከሳጥን ውጪ ሳይታሰብ የመታውን ኳስ አላዛር ማርቆስ በጥሩ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖታል ። ቀጣዩ የግብ ሙከራም 84ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን ባዬ ገዛኸኝ በግሩም ሁኔታ ሁለት የጅማ አባጅፋር ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራን አላዛር ማርቆስ በድጋሚ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ያስቆጠሩትን ግብ አስጠብቀው ለመውጣት ወደ ኋላ በማፈግፈግ የኋላ ክፍላቸውን አጠናክረው የጨዋታውን ቀሪ ደቂቃዎች የተጫወቱት ጅማ አባጅፋሮች በመጨረሻም ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር ነጥቡን 23 ሲያደርስ በደረጃው ላይ ለውጥ አላደረገም ። በአንፅሩ ሀድያ ሆሳዕና በ33 ነጥብ ወደ በነበረበት 8ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።

በ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 12 ( ዕሁድ ) 10:00 ላይ ጅማ አባጅፋር ሲዳማ ቡናን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ሰኔ 13 ( ሰኞ ) 7:00 ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከሰበታ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ