በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናን ከወልቂጤ ከተማ አገናኝቶ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመሩት ወልቂጤ ከተማዎች ለረጅም ደቂቃዎች ሲመሩ ቢቆዩም በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ በተቆጠረባቸው ግብ አቻ ለመውጣት ተገደዋል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በ24ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን በረቱበት ጨዋታ ላይ በነበረው አሰላለፍ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የገቡ ሲሆን በወልቂጤ ከተማ በኩል ግን በሳምንቱ በሰበታ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ ዮናስ በርታን እና ኤዲ ኤሞሞ ንጎይን በተስፋዬ ነጋሽ እና አክሊሉ ዋለልኝ ምትክ አሰልፈዋል ።
ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው የቀትር ሰባት ሰዓቱ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ የጀመሩት ነበር ።
በጨዋታው ቀዳሚ የግብ ሙከራ ብርሀኑ በቀለ ከሀብታሙ ገዛኸኝ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ የግቡ አግዳሚን ለትሞ ወጥቷል ። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ግን የጨዋታው የመጀመሪያ ግብ የተቆጠረ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ መሪ መሆን ችሏል ።
- ማሰታውቂያ -
18ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ በርታ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጀርባውን ለግብ ሰጥቶ በደረቱ የተቆጣጠረው ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ የመታው ኳስ በመሳይ አያኖ መረብ ላይ አርፏል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይም የተሻሉ ሆነው መቀጠል ችለው ነበር ። በ29ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ተመልሷል ።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች በራምኬል ሎክ እና ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን አማካኝነት ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በግብ ጠባቂው እና በግቡ ቋሚ ተመልሰዋል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በወልቂጤ ከተማ መሪነት ተጠናቋል ።
ሁለተኛውን አጋማሽ ባዬ ገዛኸኝን እና ኡመድ ኡክሪ
በሚካኤል ጆርጅን እና ራምኬል ሎክ ተክተው የገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከቀዳሚው አጋማሽም በተሻለ በወልቂጤ ከተማ ላይ ጫና አሳድረው በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ። በተለይም በቀኝ መስመር ባደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሀድያ ሆሳዕናን የኋላ መስመር ደጋግመው መፈተን ችለዋል ።
በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ላይም ለሳጥኑ በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው ያገኟቸውን የቅጣት ምቶች በሁለቱ ተቀያሪዎች ወደ ግብ ለመሞከር ቢጥሩም በሀድያ ሆሳዕና ተጫዋቾች በሰሩት የመከላከል አጥር ተመልሷል ።
በወልቂጤ ከተማ በኩል በአጋማሹ በቁጥር በርከት ብለው ከኳስ ጀርባ በመገኘት ከተጋጣሚያቸው በሚነጥቁበት ወቀት ጌታነህ ከበደ ኢላማ ያደረጉ ኳሶችን በጥቂት አጋጣሚዎች ወደ ፊት ለማደረስ ሞክረዋል ።
በ53ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ወደ ግብ የመታው ኳስ ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በላይ ወጥቷል ።
ከአንድ ደቂቃ በኋላ ሀድያ ሆሳዕናዎች ጥሩ የማግባት ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ። ባዬ ገዛኸኝ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ከተስፋዬ አለባቸው የደረሰውን ኳስ ግቡን ለቆ የወጣውን ሰይድ ሀብታሙን አልፎ ለዑመድ ኡክሪ ቢያቀብለውም የዑመድ ኳስ ከግቡ አናት በርቀት ወጥቷል ።
ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ባዬ ገዛኸኝ ከፍቅረየሱስ ተክለብርሀን በተከላካዮች መካከል የደረሰውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብ ቢልከውም የግቡ ቋሚ መልሶበታል ።
የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች የግብ ዕድል ለፍፈጠር የሚያደርጓቸው ሙከራዎች በሰይድ ሀብታሙ እና በተከላካዮች ሲከሽፉባቸው ደቂቃዎች ተቆጥረዋል ።
በ73ኛው ደቂቃ ላይ ዑመድ ኡክሪ ከሳጥን ውጪ ያደረው ሙከራ በግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ በቀላሉ ተመልሷል ። በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ላይ ወልቂጤ ከተማዎች ቀድሞ ከነበራቸው በተሻለ ወደ ሀድያ ሆሳዕና የግብ ክልል ለመድረስ ችለው ነበር ። በዚህም 89ኛ ደቂቃ ላይ ያሬድ ሀሰን ሳጥኑ መግቢያ ላይ ያገኘውን ኳስ መሞከር ቢችልም ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሀብታሙ ታደሰ ከፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በተከላካዮች መካከል የደረሰውን ኳስ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ላይ አግኝቶ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ መልሶበታል ። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሩ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ወልቂጤ ከተማዎችን አንገት ያስደፋ ግብ አስቆጥረዋል ። ከማዕዘን የተነሳው ኳስ በፍሬዘር ካሳ ተገጭቶ የደረሰው ተስፋዬ አለባቸው ኳስ እና መረብን በማገናኘት ሀድያ ሆሳዕናን ከሽንፈት የታደገ ግብ አስቆጥሯል ።
ውጤቱም ተከትሎ ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 33 ያደረሰ ሲሆን ደረጃው ግን በነበረበት 7ኛ ላይ የሚቀጥል ሲሆን ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ ነጥቡን 30 በማድረስ ወደ 11ኛ ከፍ ማለት ችሏል ።
በ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 4 ( ቅዳሜ ) 10:00 ላይ ወልቂጤ ከተማ መከላከያን ሲገጥም ሰኔ 6 ( ሰኞ ) ረፋድ 4:00 ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከጅማ አባጅፋር ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል ።