የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ፋሲል ከተማን ከሀድያ ሆሳዕና አገናኝቶ ከእረፍት በኋላ በተቆጠሩ ግቦች አንድ አቻ ተጠናቋል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በ15ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት ምርጥ 11 አምሰት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በመሳይ አያኖ ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ ፣ ኡመድ አክሪ እና ባዬ ገዛኸኝ ምትክ ሶሆሆ ሜንሳህ ፣ ሄኖክ አርፊጮ ፣ እያሱ ታምሩ ፣ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን እና አበባየሁ ዮሀንስን ሲያሰልፉ ፋሲል ከተማዎች ደግሞ በሳምንቱ ድሬዳዋ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በአልጄሪያው ክለብ ጄኤስ ካቢሌ ያልተሳካ ጊዜ አሳልፎ ወደ ቡድኑ የተመለሰውን ሙጂብ ቃሲምን በማሰለፍ ይሁን እንደሻውን አሳርፈዋል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀድያ ሆሳዕናዎች የተሻለ ሆነው መንቀሳቀስ ችለው ነበር ። በአንፃሩ ፋሲል ከተማዎች ሁለቱን ግዙፍ አጥቂዎች ሙጂብ ቃሲምን እና ኦኪኪ አፎላቢን ከፊት መስመር ማሰለፍ ቢችሉም ለሁለቱ ተጫዋቾች በተገቢ መልኩ የሚደርሱ ኳሶች አለመኖራቸውነ የተጠበቀውን ያህል መንቀሳቀስ እንዳይቸሉ አድርጓቸዋል ።
በተሻለ ወደ ፊት መጓዝ ችለው የነበረ ቢሆንም የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ደከም ብለው የታዩ ሲሆን የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለመድረግ 19 ደቂቃዎች መጠበቅ የግድ ብሏቸው ነበር ።
ሀብታሙ ታደሰ ከአስቻለው ታመነ የነጠቀውን ኳስ በቀኝ መስመር በኩል ገብቶ ለማስቆጠር ያደረገወሰ ጥረት በግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ተመልሶበታል ።
- ማሰታውቂያ -
ከውሀ እረፍት መልስ አፄዎቹ በተወሰነ መልኩ የቸሻለ ወደ ፊት ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉ ቢሆንም ያን ያህል ለግብ የቀረበ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችለለ ቀርተዋል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከተማዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረቶችን ያደረጉ ቢሆንም የሀድያ ሆሳዕና የመከላከል አጥር በቀላሉ የሚሰበር አልነበረም ።
አጋማሹን ሱራፌል ዳኛቸውን እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን ቀይረው በማስገባት ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ያደረጓቸው ጥረቶች እምብዛም ውጤታማ ያልነበሩ ሲሆን በተወሰነ መልኩ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ64ኛው ደቂቃ ላይ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ብርሀኑ በቀለ በቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ለሀብታሙ ታደሰ አቀብሎት ሀብታሙ ግብ ቢያደርገውም የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጪ በሚል የሻሩት ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በተቃራኒ አቅጣጫ ፋሲል ከተማዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋሎ ። ከማዕዘን የተሻገረ ኳስ በሀድያ ሆሳዕና ተከላካይ ተገጭቶ ሲመለስ ያገኘው በዛብህ መለዮ በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳሰ 66ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አርፏል ።
በሜዳቸው በቁጥር በዝተው ይገኙ የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲያደርጓቸው የነበሩ ሙከራዎች በቀላሉ በአፄዎቹ ተከላካዮች ይመለሱ ነበር ። በ76ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አርፊቹ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ነፃ የነበረው ቃልአብ ውብሸት በግሩም ሁኔታ በግንባር ገጭቶ ያስቆጠረው ግብ የሙሉጌቴ ምህረትን ቡድን አቻ ማድረግ ችሏል ።በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ላይ ፋሲል ከተማዎች ሁለተኛ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ቢያደርጉም በቀላሉ ወደ ሀድያ ሆሳዕና ሳጥን ለመድረስ የተቸገሩ ሲሆን በአንፃሩ ሀድያ ሆሳዕናዎች ጨዋታውን በማቀዝቀዝ አንድ ነጥብ ይዘው ከሜዳ ለመውጣት ችለዋል ። በጨዋታው 82ኛ ደቂቃ ላይ የሀድያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ ባጋጠመው ጉዳት በመሳይ አያኖ ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል ።
ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከተማ ነጥቡን 27 በማድረስ በጊዜያዊነት ደረጃውን ወደ 3ኛ ከፍ ሲያደርግ ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ነጥቡን 18 ማድረስ ቢችልም በነበረበት 12ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ17ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ረቡዕ ቀን 9 ሰዓት ላይ ፋሲል ከተማ ወልቂጤ ከተማን ሲገጥም በዕለቱ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ደግሞ ሀድያ ሆሳዕና ከባህርዳር ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል ።