የ2014 ዓ.ም የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ጅማሮዋቸውን ሲያደርጉ በቅድሚያ የተደረገው በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው የሰበታ ከተማ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ የ3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ15ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ምርጥ 11 ስምንት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በቻርለስ ሉክዋጎ ፣ ደስታ ደሙ ፣ ሱሌማን ሀሚድ ፣ ሻሂዱ ሙስጠፋ ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ አዲስ ግደይ ፣ በረከት ወልዴ እና እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ ምትክ ባህሩ ነጋሸ ፣ ሄኖክ አዱኛ ፣ ምኞት ደበበ ፣ ያሬድ ታደሰ ፣ ሀይደር ሸረፋ ፣ አቤል ያለው ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ቸርነት ጉግሳ ጨዋታውን መጀመረ ሲችሉ ሰበታ ከተማዎች በሳምንቱ ከአርባ ምንጭ ከተማ አቻ ሲለያየለ ከነበረው ምርጥ 11 ላይ 2 ቅያሪዎችን በማድረግ በረከት ሳሙኤልን እና ቢስማርክ አፒያን በወልደአማኑኤል ጌቱ እና አንተነህ ናደው ምትክ በጨዋታው ላይ አሰልፈዋል ።ጨዋታውን በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመሩት ፈረሰኞቹ ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው አምሰት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበር ። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር አቅጣጫ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ሄኖክ አዱኛ ወደ ግብ ሲያሻግረው የመሀል ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ የሰበታ ከተማው ግብ ጠባቂ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል ። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ካገኙ በኋላም በፈጣን እና በቆሙ ኳሶች አማካኝነት ሁለተኛ ግብ ለማከል ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
በ15ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በረጅም የደረሰውን ኳስ አረጋግቶ ለአማኑኤል ገብረሚካኤል ያቀበለው ሲሆን አማኑኤል ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ። ሰበታ ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ በተለይም በግራ መስመር በዱሬሳ ሹቢሳ አማካኝነት በተደጋጋሚ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ለመግባት ጥረቶችን ቢያደርጉም ስኬታማ መሆን አልቻሉም ነበር ።
36ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር ። አቤል ያለው ከሄኖክ አዱኛ የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ የሰበታ ከተማ ተከላካዮች በማታለል ጭምር አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ በግብ ጠባቂው ሰለሞን ደምሴ ተመልሶበታል ።በ39ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት ሳሙኤል ሳሊሶ ሲያሻግረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች በአግባቡ ከግብ ክልላለቸው ለማራቅ በተቸገሩበት ወቅት ኳሱ የደረሰው በረከት ወልደዮሀንስ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሯል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በአንድ እኩል ውጤት ተጠናቀቀ ።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ። በ55ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ከያብስራ ተስፋዬ ጥሩ ኳስ ደርሶት የነበረ ቢሆንም ቸርነት ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡን ሁለቱን ቋሚዎች ለትሞ ሊወጣ ችሏል ።ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሀይደር ሸረፋ ከራሱ የግብ ክልል በረጅም ለአማኑኤል ገብረሚካኤል የላከለት ኳስ በረከት ወልደዮሀንስን ሲያልፍ የግብ ጠባቂውን መውጣት የተመለከተው አማኑኤል ኳሱን ከፍ አድርጎ ወደ ግብ በመላክ ፈረሰኞቹን ዳግም መሪ ማድረግ ችሏል ። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ የቀጠለ ሲሆን በሁለቱም በኩል በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ አቅጣጫ ለመድረስ የሚያደርጓቸው ጥረቶች ለረጅም ደቂቃዎች በግብ ሙከራ ሳይታጀቡ ቆይተዋል ።በ80ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ተቀይሮ በገባ ገና በ40ኛው ሰከንድ ላይ በመጀመሪያ ንክኪው ሌላኛው የሰለሞን ደምሴን ስህቸት ተጠቅሞ 3ኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል ።በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሰበታ ከተማዎች ኳሱን ይዘው ወደ ፊት ለማለፍ የሚያደርጓቸው ጥረቶች በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች እየተነጠቁ ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ ሲያደርጋቸው ነበር ። በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ሰበታ ከተማ 1 ሆኖ ጨዋታ ተጠናቋል ።
ውጤቱት ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 34 በማድረስ መሪነቱን ሲያጠናክር ሰበታ ከተማ ደግሞ በ9 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ17ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ማክሰኞ ቀን 9 ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥም በዕለቱ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ደግሞ ሰበታ ከተማ ከመከላከያ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል ።