መነሻ ገጽ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ዘገባ | ቡናማዎቹ ከመመራት ተነስተው አሸንፈዋል
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባድሬዳዋ ከተማ

የጨዋታ ዘገባ | ቡናማዎቹ ከመመራት ተነስተው አሸንፈዋል

አጋራ
አጋራ

በሊጉ የ22ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ በሁለተኛ መርሀግብር ኢትዮጵያ ቡናን ከድሬዳዋ ከተማ አገናኝቶ ብርቱካናማዎቹ በሄኖክ አየለ ግብ መምራት ችለው የነበረ ቢሆንም ኡበበከር ናስር በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠራቸው ግቦች ቡናማዎቹን ባለ ድል አድርገዋል ።

ኢትዮጵያ ቡና በ21ኛው ሳምንት በመከላከያ በሰፊ ውጤት በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አራት ለውጦችን በማድረግ ኡበበከር ናስርን ጨምሮ ዊልያም ሰለሞንን ፤ አብነት ደምሴን እና ያብቃል ፈረጃን በእንዳለ ደባልቄ ፤ ሚኪያስ ሰለሞን ፤ ሮቤል ተክለሚካኤል እና ቴዎድሮስ በቀለ ምትክ ሲያሰልፉ በድሬዳዋ ከተማ በኩል በሳምንቱ ሰበታ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ በተመሳሳይ አራት ለውጦችን በማድረግ በያሲን ጀማል ፤ መጣባቸው ሙሉ ፤ አቤል አሰበ እና አቤል ከበደ ምትክ እንየው ካሳሁን ፤ ብሩክ ቃልቦሬ ፤ ዳንኤል ደምሴን እና ሱራፌል አስማማውን በጨዋታው ላይ ማሰለፍ ችለዋል።በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለመደው አጨዋወታቸው ኳስን ከግብ ክልላቸው መስርተው ለመውጣት ሲያደርጉት የነበረው ጥረት በድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች ጫና ምክንያት በተደጋጋሚ ይነጠቁ የነበረ ሲሆን በዚህም በ11ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስተናግዱ ችለዋል ።

አብነት ደምሴ አስራት ቱንጆ ያቀበለውን ኳስ በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል በቀረበት ጊዜ ሱራፌል ጌታቸው ኳሱን አግኝቶ እየገፋ በመሄድ ለማስቆጠር ሲሞክር ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ከግቡ ወጥቶ ቢመልሰውም የተመለሰውን ኳስ ሄኖክ አየለ ከሱራፌል ተቀብሎ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ድሬዳዋ ከተማን መሪ አድርጓል ።ከግቡ በኋላ ቡናማዎቹ በተወሰነ መልኩ ቀደም ብሎ ከነበረው በተሻለ ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ለመድረስ ችለው ነበር ።

በ24ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከታፈሰ ሰለሞን የደረሰውን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ለመሞከር ያደረገው ሙከራ ኳሱ ኢላማውን ባለመጠበቁ ሳይሳካ ቀርቷል ።

ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ከቀኝ መስመር የተሻገረው ኳስ በአቡበከር ናስር በኩል ለአስራት ቱንጆ ደርሶ አስራት ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በፍሬው ጌታሁን ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። ከማዕዘን ምት የተነሳውን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን ከፍ አድርጎ ያደረሰው ኡበበከር ናስር ኳሱን ደረቱ ላይ አብርዶ ወደ ግብ በመላክ ኢትዮጵያ ቡናን አቻ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ።ከአቻነቱ ግብ በኋላ ቡናማዎቹ አቡበከር ናስርን ኢላማ ባደረጉ ኳሶች የድሬዳዋ ከተማን የኋላ ክፍል ለመፈተን ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ በኩል ኳሶችን በሚነጥቁበት ጊዜ በፈጣን ሽግግር ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ ሲታትሩ ቆይተዋል ።

42ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር በግራ የሳጥኑ አቅጣጫ አስራት ቱንጆ ያደረሰውን ኳስ ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ኳሱ ኢላማውን ባለመጠበቁ ሳይሳካ ቀርቷል ።

ዳንኤል ደምሴ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በ45+3 ደቂቃ ላይ በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮት በበረከት አማረ ከተመለሰበት በኋላ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ የፊሽካ ድምፅ ተሰምቷል ።በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች የቡናማዎቹን የኳስ ቅብብል ሂደት በማቋረጥ በተለይም በቀኝ መስመር በኩል የማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የሞከሩ ቢሆንም ጠንከር ያለ የግብ ሙከራ ከማድረጋቸው አስቀድሞ ግብ ሊያስተናግዱ ችለዋል ። አቡበከር ናስር በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ ለያብቃል ፈረጃ አቀብሎት 27 ቁጥር ለባሹ ወደ ግብ የመታው ኳስ በአውዱ ናፊዪ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ኡበበከር ናስር በ53ኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠር ቡናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል ።በ59ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ቃልቦሬ ከሄኖክ አየለ የተሻገረለትን ኳስ ግብ ለማድረግ ያደረገው ጠንከር ያለ ሙከራ በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት ሲሆን ብርቱካናማዎቹ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ የተሻለ እንቅስቃሴን በማድረግ በቡናማዎቹ የሜዳ ክፍል ላይ መቆየት የቻሉ ቢሆንም በረከት አማረን የፈተነ የግቡ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ነበር ።

በአንፃሩ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች ጥለው የሚሄዱትን ክፍተት ለመጠቀም ሲያርገጉ የነበረው ጥረት ያን ያህል ብርቱካናማዎቹን የፈተነ አልነበረም ።የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ቡናማዎቹ ኳሱን መልሰው በመቆጣጠር ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ሲጥሩ የነበረበት ነበር ።

በ81ኛው ደቂቃ በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ይዘው የሄዱትን ኳስ አስራት ቱንጆ ለአቡበከር ናስር አቀብሎት የነበረ ቢሆንም ከኡበበከር ወደ ግብ የተላከው ኳስ በፍሬው ጌታሁን ተይዟል ።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል 84ኛው ደቂቃ ላይ ሙኽዲን ሙሳ በግራ አቅጣጫ የተሻረለትን ኳስ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ኳሱ ኢላማውን የጠበቀ ባለመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል ።መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ አቡበከር ናስር ከተከላካዮች ጀርባ የደረሰውን ኳስ እየገፋ ሄዶ አስቆጠረው ተብሎ ቢጠበቅም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል ። አቡበከር ግቡን ማስቆጠር ችሎ ቢሆን ኖሮ በጨዋታው ሀትሪክ ሰርቶ መውጣት ይችል ነበር ።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ቡና 2 – 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል ።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 31 በማድረስ ከ8ኛ ደረጃ ወደ 6ኛ ከፍ ማለት ሲችል ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በነበረበት 13ኛ ደረጃ እና 24 ነጥብ ለመቆየት ተገዷል ።

በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 3 ( ረቡዕ ) ረፋድ 4 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን ሲገጥም በቀጣዩ ቀን ( ሐሙስ ) 10 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...