በርከት ባሉ የእግርኳሱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የክብር እንግዶች እና በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ፊሽካ በጀመረዉ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን እያስመለከቱን ነገር ግን ያን ያህል ተጠቃሽ ሙከራዎችን ሁለቱም ክለቦች ሳያስመለክቱን ቀጥለዋል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ ምንም እንኳን አደገኛ የሚባሉ ኢላማቸዉን የጠበቁ ሙከራዎችን እምብዛም መመልከት ባንችልም ነገር ግን አማኑኤል ዮሐንስ እና አብዱልከሪም ወርቁ በቡናማዎቹ በኩል እንዲሁም አበባየሁ ሀጂሶ እና ቢኒያም ፍቅሬ ደግሞ በጦና ንቦቹ በኩል ዕድሎችን ቢያገኙም ነገር ግን በመጠቀሙ ረገድ ደካማ ሁነዉ ተስተውሏል።
ከዕረፍት መልስ ለተወሰኑ ያክል ደቂቃዎች ጨዋታዉ በተመሳሳይ ሁነት ቀጠለ በኋላ በ51ኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል የተሻገረዉን ኳስ አጥቂዉ ቢኒያም ፍቅሬ ከተቆጣጠረ በኋላ ለአበባየሁ ሀጂሶ አቀብሎት ተጫዋቹም ሳጥን ውስጥ ገፍቶ በመግባት ድንቅ ጎል አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በ65ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ በተለየ መነሳሳት ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን ግብ ለማግኘት መጣር የቀጠሉት ቡናማዎቹ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም በተጠቀሰዉ ደቂቃ አማኑኤል ዮሐንስ ላይ ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ተከላካዩ ዋሳዋ ጂኦፍሬ አስቆጥሮ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
መደበኛዉ ዘጠና ደቂቃ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ጨዋታዉ ወደ ጭማሪ ሰላሳ ደቂቃ አምርቶ የነበረ ሲሆን በዚህም ጭማሪዉ ደቂቃ አብቅቶ ክለቦቹ ወደ መለያ ምት ሊያመሩ አምስት ያክል ደቂቃዎች ብቻ በቀሯቸዉ ወቅት ግን የወላይታ ዲቻ ሳጥን ውስጥ ኳስ በዕጅ መነካቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ዋሳዋ ጂኦፍሪ ዳግም አስቆጥሮ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ለስድስተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል።
ከጨዋታዉ መጠናቀቅ በኋላ ቡናማዎቹ የዋንጫ ክብራቸዉን ከዕለቱ የክብር እንግዶች ዕጅ መቀበል ሲችሉ ፤ በቀጣዩ የውድድር አመትም ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ኮንፍደሬሽን ካፕ ተሳታፊ የሚሆኑ ይሆናል። በተቃራኒው በጨዋታዉ መገባደጃ ወቅት በተሰጠዉ ፍፁም ቅጣት ምት ዙሪያ በዳኞነቱ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ የነበራቸዉ ወላይታ ዲቻዎች የብር ሜዳልያ ሽልማታቸዉን ሳይቀበሉ ቀርተዋል።