በአቤኔዘር አበበ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ያደረገው ሀላባ ከተማ በመጨረሻው የጭማሪ ደቂቃ በወልዋሎ የተቆጠረበት ግብ 1ለ1 እንዲጠናቀቅ ሆኗል።

ወደ ሊጉ ባደገበት አመት አዲስ ባስመረቀው ሜዳ ላይ የ2019 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን ያደረገው ሀላባ ከተማ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀሩት ያስተናገደው ጎል አንድ ነጥብን እንዲጋራ ዳርጎታል። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ወልዋሎዎች በማጥቃት አደረጃጀት እና በግብ ዕድል ፈጠራው የተሻለውን እንቅስቃሴ አሳይተዋል።
13ኛው ደቂቃ ሠመረ ሀፍታይ ከጌቱ ሀይለማርያም የደረሰውን ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት በአንድ ሁለት ቅብብል ሠመረ ፣ እዮብ እና በየነ ነካክተው ካርሎስ ወደ ጎል ሞክሮ አግዳሚ ብረት ያወጣበት እንዲሁም ካርሎስ በድጋሚ ያመከናት አስቆጪ ሙከራ በወልዋሎ በኩል በሀላባ በኩል ዮናታን ሐይሉ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አክሮ መቶ ሴኔጋላዊው ግብ ጠባቂ አማር ፎል ያወጣት ኳስ ጠጣሯ ሙከራቸው ነበረች።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሀላባ ከተማ ከቆመ ኳስ ጎል አስቆጥሯል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግራ ከተገኘው ቅጣት ምት ያሬድ መሐመድ ሲያሻማ ሽመክት ጉግሳ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር የሀላባ ከተማን የመጀመሪውን ጎልም አስገኝቷል። ጎል ካስቆጠሩም በኋላ በይበልጥ የመጨረሻው ሜዳ ላይ ብልጫውን ሀላባ ከተማዎች ወስደው የነበረ ቢሆን የሽመክት እና ፍሬው ተቀይሮ መውጣት ቡድኑን አቀዝቅዞት ተስተውሏል።
ጨዋታው ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ሲደርስ ወደ ጨዋታ ቅኝት የገቡት ወልዋሎዎች ከበየነ ባንጃው አግዳሚ ብረት ከገጨችዋ ኳስ በኋላ በመጨረሻም ተሳክቶላቸው የአቻነት ግብን አግኝተዋል። 90+4 ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ ሴኔጋላዊው የሀላባ ተጫዋች ሳንባ ሴክ በእጅ ኳስን በመንካቱ በረዳት ዳኛው ሰለሞን ተስፋዬ ጥቆማ የተገኘችን የፍፁም ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠው ከመረብ አዋውዶ ጨዋታው በመጨረሻም 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።
አስተያየት ይስጡ