መነሻ ገጽ ሲዳማ ቡና “የዋልያዎቹን ጥሪ ብዙም አልጠበኩትም ነበር “ፍሬው ሰለሞን(ጣቁሩ) /ሲዳማ ቡና/
ሲዳማ ቡናቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግዋልያዎቹዜናዎች

“የዋልያዎቹን ጥሪ ብዙም አልጠበኩትም ነበር “ፍሬው ሰለሞን(ጣቁሩ) /ሲዳማ ቡና/

አጋራ
አጋራ

👉”የዋልያዎቹን ጥሪ ብዙም አልጠበኩትም ነበር “

👉 “የግል ችግሮች ነበሩብኝ እና እነዚህን ነገሮች አስተካክዬ ወደራሴ በመመለስ ሙሉ ትኩረቴን ለእግር ኳስ እና ለእግር ኳስ ብቻ አድርጌያለሁ” ፍሬው ሰለሞን(ጣቁሩ) /ሲዳማ ቡና/

 

ከዚህ ቀደም በመከላከያ በሀዋሳ ከተማ እና በወልቂጤ ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል በዚህ የውድድር ዓመት ደግሞ በሲዳማ ቡና ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት ላይ ይገኛል ። ከክለብ ባለፈ በብሄራዊ ቡድንም ተመርጦ በተለያዩ ጊዜያት ሀገሩን ማገልገል ችሏል ።

ለተወሰኑ ጊዜያት ከብሄራዊ ቡድን ስብስብ መራቅ በኋላ በ2022 ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና እና ዚምባብዌ ጋር ቀሪ ጨዋታዎችን ለሚያደረገው የዋልያዎቹ ስብስብ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለተጫዋቾቹ ጥሪ ሲያደረግ በቡድኑ ውስጥ መካተት ችሏል …….ፍሬው ሰለሞን ( ጣቁሩ )

በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ስለመካተቱ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከሀትሪክ ስፖርት ድህረ-ገፅ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል ።


ሀትሪክ – ጣቁሩ የሚለው ቅፅል ስም እንዴት ሊወጣልክ ቻለ ?

ፍሬው – ስሜ የወጣው በሰፈር ኳስ ስንጫወት የጥቁር ሰው ተቃራኒ ለማለት ፈልገው ነው በልጅነታችን ሰፈር አዋራ ላይ ምናምን ስንጫወት በዛ መሰለኝ ጣቁሩ ያሉኝ ።

ሀትሪክ – ከዚህ ቀደም በተለያዩ ክለቦች ተጫውተህ አሳልፈሀል ጥሩ ጊዜን አሳልፌበታለሁ የምትለው የትኛውን ነው ?

ፍሬው – በውጤት ደረጃ መከላከያ ነው ከመከላከያ ጋር በተደጋጋሚ የጥሎ ማለፉን እና የአሸናፊዎች አሸናፊን ዋንጫ አሸንፌያለሁ ጥሩ በመጫወት ደግሞ አሪፍ ጊዜን ያሳለፍኩት በሀዋሳ ከተማ ነው ።

ሀትሪክ – ከብዙ ጊዜ በኋላ ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ዳግም መመለስ ችለሀል ጥሪው ሲደርስክ ምን አይነት ስሜት ነበር የተሰማክ ?

ፍሬው – ጥሪውን ብዙም አልጠበኩትም ነበር ምክንያቱም ረጅም ጊዜ ሆኖኛል በብሄራዊ ቡድን ከወጣው ቢያንስ አንድ ሁለት አመት አልፎኛል ግን በቃ ብዙ ጊዜ ተስፋ ቆርጬ ነበር አሁን ግን ከብዙ አመት በኋላ ስጠራ በጣም ነው ደስ ያለኝ ።

ሀትሪክ – ጥሪውን አልጠበክም ነበር ማለት ነው ?

ፍሬው – አዎ አልጠበኩም ነበር መጀመሪያ ሌላ ሰው ነው ሚዲያ ላይ አይቶ ነው የነገረኝ እኔም ሳየው ገረመኝ ስላልጠበኩት ።

ሀትሪክ – ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያቶች በብሄራዊ ቡድን ተመርጠህ ተጫውተህ ነበር በማን በማን የአሰልጣኝነት ጊዜ ነበር የተጫወተክው ?

ፍሬው – ከዚህ በፊት በሰውነት ቢሻው ፤ በማሪያኖ ባሬቶ ፤ በዮሐንስ ሳህሌ እና በአሸናፊ በቀለ ።

ሀትሪክ – ለመጨረሻ ጊዜ በብሄራዊ ቡድኑ የተጫወትከው መቼ ነበር ?

ፍሬው – ለመጨረሻ ጊዜ በአሸናፊ በቀለ ጊዜ በሴካፋ ውድድር ላይ ነበር ኬንያ ላይ በተዘጋጀው ።

ሀትሪክ – ከዛ በኋላ እንግዲህ ለብሄራዊ ቡድኑ ሳትጠራ የቀረህበት ምክንያት ባንተ ዕምነት ከወቅታዊ ብቃትህ የተነሳ ነው ወይስ በአሰልጣኞቹ ምክንያት ነው ?

ፍሬው – አዎ ከወቅታዊ ብቃት ጋር ነው ። በዛን ሰአት የነበርኩበት ነገር ያንን ሁለት ዓመት በኳስ ጥሩ ጊዜን አላሳለፍኩም ያው ቀድሞ የነበረኝ አቋም ላይ አልነበርኩም የግል ጉዳይም አንዳንድ ነገሮችም ተደራርበው ብዙም ጥሩ የሚባል ጊዜ ስላላሳለፍኩኝ አልጠብኩም አልጠብቅምም ነበር ።

ሀትሪክ – በፊት በነበርክበት ብሄራዊ ቡድን ላይ እና ያሁኑ ብሄራዊ ቡድን ላይ ምን አይነት ልዩነቶችን አሉ ?

ፍሬው – የዛኔ እና የነበረው ብዙም ልዩነት ባይኖረውም በአጨዋወት ላይ የዛኔ ኳሶችን በፈለክበት አካሄድ ይዘህ ትሄዳለህ በረጅምም ምናምን ማለት ነው በዚህ ብሄራዊ ቡድን ያየሁት ኳስን ከኋላ መስርተህ ነው ከበረኛው ጀምረህ ነው የምትሄደው እና ከዚህ በፊት ከነበረው አጨዋወት በተቃራኒው ምቹ የሆነ አጨዋወት ነው።

በፊት ስንጫወት የነበረው ረጅምም ሆነ አጭር እየቀላቀልን ግን አሁን ላይ ከኋላ መስርተህ መጫወት ጠቀሜታ አለው ምክንያቱም የሰውነት ተክለ ቁመናችን ከሌሎቹ ሀገራት ጋር አይመጣጠንም አሁን በረጅም እየጣልን እንጫወት ብንል ማለት ነው ። ኳስን መሰረት አድርገን እንጫወት ብንል ደሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ችሎታው ያላቸው ተጫዋቾች ስላሉ ያን መምረጡ እና ለዛ የሚሆን አሰልጣኝ መሆኑ ጥሩ ነገር አለው ብዬ አስባለሁ ለዚህ ማረጋገጫም ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ትልቅ ምስክር ነው ።

ሀትሪክ – አሁን ብቃትህ ጥሩ ለመሆኑ እና ለብሄራዊ ቡድን እስከመጠራት ያደረሰህ ምክንያቱ ምንድነው ማለት ይቻላል ?

ፍሬው – የግል ችግሮች ነበሩብኝ እና እነዚህን ነገሮች አስተካክዬ ወደራሴ በመመለስ ሙሉ ትኩረቴን ለእግር ኳስ እና ለእግር ኳስ ብቻ አድርጌያለሁ እግር ኳስ ህይወቴም ቤተሰቤንም የማስተዳድርበት ስለሆነ የነበሩትን ነገሮችም ዕርግፍ አድርጌ በመጨራረስ ቀድሞ ወደ ነበረኝ አቋሜ ለመመለስ እየጣርኩ ነው ከዚህ በኋላም ደሞ በደንብ በፊት ወደነበረው አቋሜ እመለሳለሁ ።

ሀትሪክ – ስለዚህ ፍሬውን በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ እንጠብቅው ?

ፍሬው – አዎ ። ከዚህ በኋላም ጥሩ ነገር ስለምሰራ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከቡድኑ ጋር እጓዛለሁ ለዛም ጠንክሬ እና ተግቼ እሰራለሁ ።

ሀትሪክ – እስኪ ከብሄራዊ ቡድኑ ወጣ እንበል እና ስለዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምን ማለት ይቻላል ? እንዴት ነው አጀማመሩ ?

ፍሬው – አሁን እንዲህ የምለው ነገር የለም አንደኛ ነገር ጨዋታው ገና ሶስተኛ ሳምንት መሆኑ ነው ሁለተኛ ነገር ሁሉም ቡድኖች ከዝግጅት እኩል አቅም ይዘው ነው የመጡት በዛ ላይ የሜዳው ምቹ አለመሆን ደሞ ቡድኖችን እንዲህ ነው ብሎ ለመገመት በማያስችል ሁኔታ ነው ያለው ። ለዛም በዚህ ሰዓት ገምግመህ ይሄ የተሻለ ነው ይሄ እንዲህ ነው በዚህ አመት ይሄ ቡድን ተሻሽሏል ብለህ ለመገመት የሚከብድ ነው ።

ሌላው ደሞ ምንድነው ውድድሩ በአንድ ከተማ ላይ መሆኑ ባሁኑም ደግሞ ደጋፊዎችም ወደ ስታድየም መመለሳቸው ትልቅ ነገር አለው ። በዲኤስቲቪ የቀጥታ ስርጭት ማግኘቱ ለተጫዋቾቹ ትልቅ ግብዓት ነው መነሳሳትንም የሚፈጥር ነው ቡድኖቹም ደግሞ በቁጥር ጨምረው ወደ 16 ማደጋቸው ለሊጉ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ ።

ሀትሪክ – በክለብህ ሲዳማ ቡና በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎች 4 ነጥቦችን መሰብሰብ ችላቹሀል ። በዚህ የውድድር አመት ሲዳማ ቡና እስከምን እንጠብቀው ? ከውድድሩ መጀመር በፊትስ ምን ነበር አቅዳቹ የተነሳቹት ?

ፍሬው – በአመቱ መጀመሪያ ላይ ከአሰልጣኞች ስታፍ ከተጫዋቾችም ጋር አንድ ላይ ስንነጋገር የነበረው ዘንድሮ ሲዳማ ቡና ከዚህ በፊት የነበረው ታሪኩን ሁለተኛ ሶስተኛ አካባቢ ይዞ ነው የሚያጠናቅቀውን ባሁኑ ግን የአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ ወይም የኮንፌዴሬሽን ካፕ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ደረጃ ይዘን ማጠናቀቅን አቅደን ነው የተነሳነው ከአመራሩም የተሰጠን ይህንን እንድናሳካ ነው ።

ሀትሪክ – ከዚህ ቀደም በነበርክባቸው ክለቦች ካደረካቸው በርካታ ጨዋታዎች የማትረሳው እና በጣም የተደሰትክበት ጨዋታ የትኛው ነው ?

ፍሬው – ደስተኛ የሆንኩበት በሀዋሳ ከተማ እያለሁ ቅዱስ ጊዮርጊስን 4 ለ 1 ያሸነፍንበት ጨዋታ መቼም አይረሳኝም ።

ሀትሪክ – በሊጉ በተቃራኒ ስተግጥመው ላንተ የሚከብድህ ተጫዋች ማነው ?

ፍሬው – እስካሁን ብዙም በዚህ ረገድ የከበደኝ ብዬ የምለው ተጫዋች የለም ምክንያቱም እኔ ብዙ ጊዜ የምጫወተው ከቅልጥፍና ጋር የተያያዘ ጨዋታ ስለምጫወት ብዙም ለእንደዚህ አይነት ነገር የዳረገኝ ተጫዋች የለም ።

ሀትሪክ – አብረኸው ስትጫወት ምቾት የሚሰጥህ ተጫዋች ማነው ?

ፍሬው – ታፈሰ ሰለሞን ነው ። ከታፈሰ ጋር ስጫወት በጣም ደስ ይለኝ ነበር ጥሩ ጊዜ ነበር ያኔ በሀዋሳ ያሳለፍነው ።

ሀትሪክ – ከእግር ኳስ ውጪ ያለውን ጊዜህን በምን ታሳልፋለህ ?

ፍሬው – ብዙ ጊዜ ከልጆቼ እና ከጓደኞቼ ጋር ነው የማሳልፈው ።

ሀትሪክ – በጣም አመሰግናለሁ

ፍሬው – እኔም አመሰግናለሁ

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

በ5 ሳምንታት 39 ጨዋታዎች፣ 72 ጎሎችና ከ22.6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተመዘገበ!

በአቤኔዘር አበበ በ2019 ዓ.ም የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያዎቹ አምስት የውድድር ሳምንታት...