“የደረጃው ጨዋታ በማጫወቴ ቅር አላለኝም”
“የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የተለየ ነው”
“ኢትዮጵያዊ መሆኔ ኩራት እንዲሰማኝ ነው ያደረገኝ”
“ለኔ እያንዳንዱ ጨዋታ የዋንጫ ነው”
- ማሰታውቂያ -
“የዋንጫውን ጨዋታ ለማጫወት ተመኝቼ ነበር” ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ
አፍሪካ አሉኝ ብላ ከምትኮራባቸው የእግርኳስ ዋና ዳኞች አንዱ ነው ። በተደጋጋሚ አህጉራዊ ጨዋታዎችን በብቃት በመዳኘትም ከራሱ አልፎ ሀገሩን ያስጠራ ምስጉን ዳኛ ነው ። ዓለምአቀፍ ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ።
በካፍ ቻምፒየንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታዎችን እስከ መምራት የደረሰው ባምላክ ተሰማ በኮትዲቫር አስተናጋጅነት በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ አምስተኛ የመድረኩ ተሳትፎውን አድርጓል።
ባምላክ በውድድሩ ሶስት ጨዋታዎችን የመራም ሲሆን ሶስቱንም ጨዋታዎች በድንቅ ብቃት በመወጣት ከበርካቶች ሙገሳዎች ጎርፈውለታል።
ለስኬቱ ደጋግሞ የፈጣሪውን ስም በማንሳት የሚያመሰግነው ባምላክ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረገጽ ባልደረባ ሀብታሙ ምትኩ ጋር ከ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫው ቆይታ ጋር በተያያዘ ቃለ ምልልስ አድርጓል።
ባምላክ የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የተለየ ነው ብሎ እንደሚስማማ ከነምክንያቱ ይናገራል ፤ የሶስቱ ጨዋታዎች የነበሩ ሁነቶችንም ያብራራል ፤ ወደ ኮትዲቯር ሲያመራ ያጋጠመው ከበድ ያለ ነገርንም አንስቷል ፤ በወድድሩ ማራዶናን ስላስታወሰውና ተደብቆ ጠፍቶበት ስለነበረው ተጫዋችም ያለው አለ።
ከዓለም አቀፍ ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ሀትሪክ፦ በኮትዲቫር አስተናጋጅነት የተደረገውን 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ብዙዎች ምርጡ የአፍሪካ ዋንጫ ብለውታል። ምን ያህል ትሰማማበታለህ ? ምንስ የተለየ ነገር ተመለከትክበት?
ባምላክ ተሰማ ፦የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በዝግጅቱ በጣም የተለየ ነው። ከዚህም በላይ የተለየ የሚያደርገው የቡድኖች አጨዋወት ዘይቤ እንደገናም ውጤቱ በጣም ተቀራረቢ ነው።
ከምድብ ጨዋታዎች ጀምሮ ሁሉም ቡድኖች ይሄኛው ትልቅ ቡድን ነው ይሄኛው ትንሽ ቡድን ነው ተብሎ ድሮ በነበራቸው ታሪክ የማይታይበት ፤ በየደቂቃው ጨዋታዎች የሚቀየሩበት ፤ ከፍተኛ የሆነ ፍጥነት ያለበት ፤ ከፍተኛ የሆነ ፉክክር ያለበት እንዲሁም በትናንሽ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ውስጥ ውጤት የሚቀይር ነገር የሚታይበት በጣም ፉክክሩ ከፍተኛ የሆነ ውድድር ነበር። በዚህ ረገድ ይሄ የአፍሪካ ዋንጫ ፍፁም የተለየ ነው የሚለውን እጋራለሁ ።
ከዚህ ውጪ ስታድየሞቹ ጥራታቸውን የጠበቁ በተለይም የመጫወቻ ሜዳዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ ለማጫወትም ለመጫወትም የሚመቹ ሆነው ነው ያገኘዋቸው። በአጠቃላይ የአፍሪካ ዋንጫው ከዚህ ቀደም ከተዘጋጁት የአፍሪካ ዋንጫዎች የተለየ ነበር።
ሀትሪክ፦ ወደ ኮትዲቯር ከማምራታችሁ በፊት ስለ ኮትዲቯር አጠቃላይ ዝግጅት የሰማችሁትና ካመራችሁ በኋላ ያያችሁት ነገር ላይ ምን የሚመሳሰል ወይም ምን የተለየ ነገር ተመለከታችሁ ?
ባምላክ ተሰማ ፦ ወደ ኮትዲቯር ከመሔዳችን በፊት የሰማነው እና ያየነው አንድ አይነት ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው። ወደዛ ከመሄዳችን በፊት እጅግ የተለየ የአፍሪካ ዋንጫ እንደሚሆን የሚወጡ ዜናዎችን እንሰማ ነበር። ከሄድን በኋላም በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያየነው ይህንኑ ነው።
ፍፁም አንድ የሆነብኝ ነገር ምንድነው ዝግጅቱ በጣም ጥሩ ነው የስታድየሞቹ ጥራት ጥሩ መሆናቸው ፤ የመጫወቻ ሜዳዎቹ ጥሩ መሆናቸው ፤ ከዛም ባሻገር ደግሞ ከዝግጅቱ ባሻገር ቡድኖች ያሳዩት ፉክክር ከፍተኛ እንደሚሆንም ግምቶች ነበሩ። ይሄን በጣም በትክክለኛው መንገድ አይቼዋለሁኝ ከዚህ ውጪ በአብዛኛው በልዩነት ያየውት ነገር የለም እንደተጠበቀው ነው ያገኘነው።
ግን የአየር ንብረቱ መሞቁ እና ርጥበት አዘል አየር መኖሩ ያልጠበቅነው ነበር ።አየሩ ከፍተኛ የሆነ ወበቅ ነበረው ሰውነት አቅም የማሳጣት ነገሮች ሁሉ ነበሩት። በዚህም ሁሉም ጨዋታዎች ላይ የመቀዝቀዣ ጊዜ እንዲኖረ ያስገደደ ነበር። ያልጠበቁት ነገር ቢኖር ይሄ ነበር።
ሀትሪክ፦በወድድሩ ላይ በአጠቃላይ ወደ 68 የሚደርሱ ዳኞች ተመርጠው ነበር። የምርጫው ሂደት ምን ይመስል ነበር ? ከተመረጣችሁ በኋላስ ምን ምን ሒደቶችን አሳለፋችሁ ?
ባምላክ ተሰማ ፦ ለዚህ ውድድር ዳኝነት ለመመረጥ ከአንድ አመት በፊት የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ካሉት ዳኞች ውስጥ መርጦ ነበር። ከዛን ጊዜ ጀምሮ የምናጫውታቸው የክለብና የብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታዎች ይታዩ ነበረ። እነዚህ ታይተው በተለያየ ጊዜ በዌቢናር እንዲሁም በግል ግምገማዎችና ከትትሎች ይደረጉ ነበር።
ከዛን በኋላ ውድድሩ ሊጀመር ሶስት ወራት ሲቀረው ሁለት ጊዜ በግብፅ አንድ ጊዜ ደግሞ በኮትዲቯር የዝግጅት ጊዜያቶች ፤ ከ”VAR” ጋር ያሉንን ልምዶች ማየት ፤ በየወሩ የአካል ብቃት ፈተና ፤ የቪዲዮ ፈተና ፤ የህክምና ምርመራ ፤ በአጠቃላይ በየወሩ ያለን የህግ ችሎታ ሊገምገም በሚያስችል መልኩ ፤ የአካል ብቃት ሊገመገም በሚችል መልኩ ፤ ህክምናችን ሊገመገም በሚችል መልኩ ፈተናዎችን እያደረግን በአንድ ላይ ልምምድ እያደረግን ነበር የቆየነው።
ስለዚህ እንደዚህ አይነት ዝግጅቶች ለመጨረሻው ምርጫ ለመብቃት ከፍተኛ ፈተናዎች ነበሩ። ከዛ ባሻገር ደግሞ የሚደረጉ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግና የአፍሪካ ሱፐር ሊግም የተካተቱበት ነበር። እነዚህ ደግሞ ከ”VAR” ጋር የሚደረጉ ናቸው።
በእነዚህ ጨዋታዎች የሚታዩ ግምገማዎች የሚታዩ ነበሩ ። ወደ አፍሪካ ዋንጫ ከመምጣትክ በፊት የምታጫውታቸው ጨዋታዎች ለመምጣትና ላለመምጣት ወሳኝ የነበሩ ናቸው። እኔ በአጋጣሚ ዕድለኛ ነበርኩ። የመጨረሻው ጨዋታ የደረሰኝ የግብፁ ፒራሚድ እና የሞሪታንያው ማዲቡ ነበር።
ጨዋታዉ ሞሪታንያ ላይ ነበር ። የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን የዳኞች ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ እኔን ለመከታተል በድብቅ ቦታው ድረስ በመምጣት ግምገማቸውን አድርገዋል።
እና በዚህ ግምገማ መሰረት የአፍሪካ ዋንጫን እንድቀላቀል ሆኗል። ስለዚህ እነዚህ ክትትሎች እና ሂደቶች ከሌላው ጊዜ የተለዩና በጣም ከበድ ያሉ ናቸው ለማለት እችላለሁ ።
ሀትሪክ፦በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ አዳዲስ ዳኞችን ተመልክተናል በብቃት ሲዳኙ የነበሩ ነባሮቹም በተመሳሳይ ፤ በውድድሩ የነበረክ አጠቃላይ የዳኝነት ግምገማ ምን ይመስላል?
ባምላክ ተሰማ ፦በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ምርጫ ውስጥ ለመግባት ከአንድ አመት በፊት የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ካወጣቸው የዳኞች ዝርዝር ውስጥ ከነባሮች ባሻገር አዲሶችም ነበሩ።
አዳዲስ ዳኞች በአብዛኛው የተተኩበት ፤ ከዚህ በፊት የአፍሪካን የእግርኳስ ውድድር በከፍተኛ ደረጃ የሚመሩ ዳኞች በተለያየ ምክንያት በተለይም ከዓለም ዋንጫ በኋላ ራሳቸውን ያገለሉበትም ጊዜ ነበር።ከዛን በኋላ በጣም ወጣት አዳዲስ ወጣቶች እንዲተኩ ተደርጎ ከዛ በፊትም ያሉት ሆነው አንድ ላይ በጋራ ነው የነበረው ።
እንዳየከው እንግዲህ የእግርኳስ ዳኝነት ፉክክር ይጠይቃል ። አንድ ዳኛ ሀገሩን ነው የሚወክለው ሀገሩን ሲወክል ደግሞ በስፖርት ሁልጊዜ አሸናፊ ሁልጊዜ ባለክብረወሰን መሆን አይቻልም ። መፎካከር ግን ይቻላል ።ስለዚህ መፎካከርና መወዳደር ይጠይቃል ።
እኔ በጣም እድለኛ ነኝ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን ፈጣሪ በጣም ይረዳኛል። ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር በመሆን ለዚህ ውድድርና ፉክክር እንድበቃ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ከብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ጋር ያለውን እቅድ በመነጋገር ለዚህ ፉክክር ለመብቃት ተዘጋጅቼ ነበር። እና እንዳልኩህ እግዚአብሔር ይረዳኛል። በዚህም ይህንን ፉክክር ለማሳካት ችያለሁ።
ነባርም አዲስም ዳኞች መኖራቸው ጥሩ ስብጥር ነው ለማለት ያስችላል ። ስፖርት የመተካካት ነው ዳኝነት ደግሞ ሁሌ የምትማረው ነው። ከታላቅህ ትማራለህ ከታናሽህም ትማራለህ። እንደኔ አይነቱ ነባር ዳኛ ከታናሾቼ ብዙ ነገር የተማርኩበት እኔ ደሞ ካለኝ ብቃትና ልምድ እነሱ የተማሩበት ነበር።
ካሉት ነባር ዳኞች ጋር አዲስ የተካተቱ አሉ። ስለዚህ ልምድ ካላቸው ዳኞች ዝርዝር ውስጥ በመሆኔ ኩራትና ክብር ይሰማኛል። መሰላል ላይ መውጣት ቀላል ነው ዋናው ነገር መቆየት ነው። ይሄ ነው ቁልፉ እና የመድኃኒዓለም እናቱ እመብርሃን ስሟ የተመሰገነ ይሁን በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ሀትሪክ፦ በውድድሩ በሶስት ጨዋታዎች ላይ በዋና ዳኝነት መርተካል ። ጨዋታዎቹ እንዴት ነበሩ?
ባምላክ ተሰማ ፦በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ሶስት በዋና ዳኝነት ሁለት በተጠባባቂነት በአጠቃላይ በአምስት የዳኝነት ስራዎች ላይ ተሳትፌያለሁ። መጀመሪያ የተሳተፍኩበት የዋና ዳኝነት የዲሞክራቲክ ኮንጎና የዛምቢያ ጨዋታ ነው።
በነገራችን ላይ የዚህ የአፍሪካ ዋንጫ እያንዳንዱ ጨዋታ የዋንጫ ነው ማለት ይቻላል ። አንደኛ ቡድኖች በእኩል ደረጃ ነው የሚፎካከሩት ስም ያለውም አዲሶችም ብሔራዊ ቡድኖች ጠንካራ ናቸው። በዚህ ደረጃ ነው የሚንቀሳቀሱት ስለዚህ ዳኝነቱም በዛ ደረጃ መንቀሳቀስን ይጠይቃል ።
እኔ ደግሞ ከተሰጡኝ ረዳት ዳኞች ጋር በመሆን ራሴን ከ”VAR” ጋር አላምጄ ጨዋታዎችን ለማጫወት በቂ ዝግጅት አድርጌያለሁ። በየቀኑ ስልጠና ፤ ትምህርት ፤ ግምገማ ፤ የአካል ብቃት ልምምድ ፤ የ”VAR” ልምምድ እንደገና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የክላስ ትምህርት ይሰጣሉ ከዛ በኋላ ግምገማ ያካሂዳሉ። በአጠቃላይ ዛምብያንና ዲሞክራቲክ ኮንጎን ያጫወትኩበት የመጀመሪያ ጨዋታዬ ጥሩ ግምገማ የሚያሳይ ነበር።
በመቀጠል ያጫወትኩት የካሜሩን እና የዛምቢያ ጨዋታ በጣም ፍጥነት ያለው፤ በመጨረሻዎቹ ሰከንዶች ውስጥ ጎሎች የሚቆጠሩበት፤ ማን እንደሚያሸንፍ እስከመጨረሻው ሰከንድ የማይታወቅበትና ወደሚቀጥለው ዙር ለማለፍ የተደረገ ከፍተኛ ፍልሚያ ነበር።
ይህ ጨዋታ ወደ 14.3 ኪሎ ሜትር የሮጥኩበት ጨዋታ ነው ። ስለዚህ ይህ ጨዋታ ከፍተኛ የሆነ አቅም ይጠይቅ ነበር። ከሁሉም ረዳት ዳኞች ጋር የነበረኝ ጥምረት ጥሩ ነበር። የመጨረሻው ግምገማም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
ወደ መጨረሻ ጨዋታዎች ለመመደብ በነባሮቹም በአዲሶቹም ዳኞች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ነበር ። እንግዲህ እኔን የመጨረሻ ሶስት ጨዋታ ካጫወቱ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ ለመግባት የድንግል ማርያም ልጅ ረድቶኝ ሶስተኛ ጨዋታ ለማግኘት ችያለሁ ያም የደረጃ ጨዋታ ነው።
ያን ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ሶስተኛ ጨዋታ ለማግኝት ከፍተኛ ፉክክር የነበረበት ወቅት ነበር እግዚአብሔር ይመስገን ተሳክቶልኝ የደረጃውን ጨዋታ ላጫውት ችያለሁ።
ይሄም ቢሆን ቀላል ጨዋታ አይደለም። እያንዳንዱ ጨዋታ ቅድም እንዳልኩህ የዋንጫ ነው።በአጠቃላይ የሚያሳዩት ግምገማ ጥሩ ነው። ባሉት አስተማሪዎች እዚህ ባሉት አሰልጣኞች ጥሩ ነው የታየው እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን በጣም ደስተኛ ነኝ በዚህ በኩል።
ሀትሪክ፦ እኔን ጨምሮ በርካቶች በወድድሩ ላይ የፍፃሜውን ጨዋታ ትመራለክ የሚል ግምቶች ነበሩን። ግን የደረጃውን ጨዋታ ነበር የመምራት እድል ያገኘከው ። የፍፃሜውን ጨዋታ ባለመዳኘትክ ምን ተሰማክ?
ባምላክ ተሰማ ፦እንደሚታወቀው ሁሉ ስፖርት የፉክክር መድረክ ነው። ዳኝነትም በዛ ውስጥ የሚጠቃለል ነገር ነው። እያንዳንዱ ጨዋታ የዋንጫ ነው ለኔ። እያንዳንዱን ጨዋታ በምመደብበት ጊዜ በትኩረትና በተግባቦት ለመስራት እጥራለሁ። ስለዚህ በዚህ ተሳክቶልኝ ሶስት ጨዋታዎችን ካጫወቱ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችያለሁ።
በወድድሩ ከፍተኛ ጨዋታን ያጫወተው ዳኛ ሶስት ነው። ስለዚህ ይሄንን አሳክቻለሁ። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። እስከመጨረሻው ድረስ ፉክክሬን ቀጥዬ ነበር። ካፍ አንድ ጨዋታ መደበኝ ማለት የዋንጫ ነው ለኔ።
ከዛ ባሻገር ግን ጨዋታዎቹ ወደ መጨረሻ ሲደርሱ የፍፃሜውን ለማጫወት ትጓጓለህ ትፎካከራለህ ትሄዳለህ ።እኔ በዚህ ዓመት የዋንጫውን ጨዋታ ለማጫወት ተመኝቼ ነበር። እግዚአብሔር አልፈቀደም። እግዚአብሔር የፈቀደው ሆኗል ደስተኛ ነኝ።
ስለዚህ ይሄ ለኔ ቀላል ነገር አይደለም። ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፤ እኔን ላሳደጉኝ የኢትዮጵያ ክለቦችና የስፖርት ቤተሰብ ከፍተኛ ምግባር ለሰጡኝና ለዚህ ላበቁኝ ፤ እውነት ነው የምልህ ምግባርና ዕምነት ለዳኝነት ያስፈልጋል ። ምግባርና ዕምነት ሰጥተው ለዚህ ላደረሱኝ ምስጋና ይግባና በዚህ አንደኛ እንደሆንኩ ተነግሮኛል።
ይሄ ለኔም ለሀገሬም ትልቅ ክብር ነው። ላሳደጉኝ ለምሰራበት መስሪያ ቤት አርማውሰን ሪሰርች ኢንስቲትዩቱ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ስፖርት ተመልካች ትልቅ ነገር ነው።
ስለዚህ እኔ በዚህ ደረጃ እንድታወቅ በዚህ ደረጃ እንድሰራ ላደረጉኝ የስፖርት ቤተሰብ ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፣ ለክለቦች ፣ ለምሰራበት መስሪያ ቤት ትልቅ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። ከዛ ውጪ የሶስተኛ ደረጃን በማጫወቴም አልከፋኝም ደስተኛ ነኝ።
ሀትሪክ፦ ባምላክ በወድድድሩ ከመራካቸው ሶስት ጨዋታዎች መካከል ጋምቢያ ከካሜሩን ሲጫወቱ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ አንድ የጋምቢያ ተጫዋች በእጁ ጎል አስቆጥሮ ከዛን በኋላ የተፈጠረ ገጠመኝ ነበር ። እስኪ ስለዛች አጋጣሚ አስታውሰኝ ምን ነበር በሰአቱ የተፈጠረው ?
ባምላክ ተሰማ ፦ ነብሱን በአፀደ ገነት ያኑረው እና ዲዬጎ አርማንዶ ማራዶናን ነው ያስታወሰኝ። እንዳየከው ኳሱ ከማዕዘን የመጣ ኳስ ነበረ። ከዛ በፊት የግንኙነት መስመር ነበረኝ። በምንነጋገርበት ጊዜ ተጫዋቹ ኳሱን ቶሎ መታው ትኩረት አላደረኩም ነበር። የመጨረሻ ደቂቃ ነው ። ተጫዋቹ ኳሱን በእጁ ኳሱን ያስገባል ። የእግዜር እጅ እንደሚባለው ማለት ነው። በእጁ ማስቆጠሩን ትኩረት በማጣቴ አላየሁትም ፤ በጣም ፈጣን ነበር ኳሱ።
ከዛም ጎሉን ካፀደቅን በኋላ “VAR” በድጋሜ እንዳየው እድሉን ሰጠኝ። እድሉን ሲሰጠኝ በጣም ነው የተገረምኩት ። ምክንያቱም በጭንቅላት ይምታው በእጁ ይምታው ለመለየት ከባድ ነበር። እኔም ትኩረት አጥቼ ነበር ከዛም በላይ በጣም ፈጣን ኳስ ነበረ።
ስለዚህ ከዛ በኋላ ያንን አድል በማግኘቴ “VAR”ን አመሰግናለሁ ማለት እፈልጋለሁ ። ምክንያቱም በእግርኳስ እንደዚህ አይነት ውጤት ቀያሪ በጣም አንገብጋቢ የሆኑ ሰውኛ ስህተቶች ልትሰራ ትችላለህ ። እንደዚህ የሚያግዝህ ነገር ሲኖር ደግሞ ደስ ይላል።
እውነት ይሄ በህይወቴ የማልረሳው ነው ። ከዛ በኋላ ይሄንን ልጅ በምፈልግበት ጊዜ ያረገውን ያውቅ ሰሰለነበር ተደብቆ ነበረ ። በኋላም በመግባባት እንደዚህ እንዳያደርግ ነግሬ የቢጫ ካርድ ሰጥቼ ግቡን ልሽር ችያለሁ። እና በዚህ አጋጣሚ እኛን ዳኞች የቡድኖችን ላብና ድካም የማይቀንስ ነገር እንድንሰራ የረዳንን ቴክኖሎጂ ለፈጠሩት ትልቅ ክብር አለኝ። እናም ያቺ አጋጣሚ በጣም ደስ የምትልና አዝናኝ የነበረች ናት።
ሀትሪክ፦በብቃት ከመራሀቸው ሶስቱ ጨዋታዎች በኋላ ብዙዎች በተለያዩ አማራጮች በተለይም በማህበራዊ ገፆች እያሞገሱህ ነበር ። እነዚህን አስተያየቶች ተመልክተሀችው ይሆን? አይተሀቸው ከሆነ የፈጠረብክን ስሜት አጋራኝ?
ባምላክ ተሰማ ፦ እውነት ለመናገር አብዛኞቹን አላየዋቸውም ፤ ሰዎች ግን ደውለው ነግረውኛል። ያላየሁበት ምክንያት ምንድነው ወደዚህ አፍሪካ ዋንጫ ስመጣ ያሉኝን የማህበራዊ ትስስር ገፆች ግቼያቸው ነበር። ትኩረት አድርጌ መስራት ስለፈለኩ ብዙም አልጠቀምም ነበር። ምክንያቱም የልምምድ ጫናው ከፍተኛ ነው። ያለውን ጫና ለመቋቋም ማረፍ ያስፈልጋል። በየቀኑ በአግባቡ ካልሰራክ ደግሞ የጨዋታ ምደባ አታገኝም ።
በእያንዳንዱ ነገሮች ተወዳዳሪ መሆን አለብህ እንደነዚህ አይነት ነገሮች ስለነበሩ በዛ ላይ ነበር ትኩረቴ ፤ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን አንዳንድ ሰዎች ደውለው ነግረውኛል። ይህ ለኔ በጣም ትልቅ ነገር ነው ። ፈጣሪ ይወደኛል እግዚአብሔር በጣም ታላቅ ነው። ክብሩን እርሱ ቢወስድ በጣም ደስ ይለኛል።
ምክንያቱም እኔ የተለየ ነገር የለኝም ። የእግርኳስ ዳኝነት የቡድን ስራ ነው ።በዛ ውስጥ ደግሞ ስለሚያስደስተኝና ስለሚያዝናናኝ በፍቅር የምሰራው ስራ ስለሆነ ትኩረት ሰጥቼ የመስራት ነገር አለኝ ። የማቀው ነገር ይሄንን ነው ።
አንዳንዴ እንደዚህ አይነት ነገር ሰትሰማ ግን ደስ ይልካል። አንዳንዴም ደሞ እዚህ አከባቢ የሚያገኙኝ ሰዎች አድናቆታቸውን ሲነግሩኝ በጣም ልዩ ነገር ይስማኛል።ከምንም በላይ ግን ባደኩበት ማህበረሰብ ባደኩበት የስፖርት ከባቢ ለተሰጠኝ ምግባር እና እምነት በጣም አመሰግናለሁ ።
ይሄ ነገርም በደንብ የተንፀባረቀ ይመስለኛል ። ይህም ኢትዮጵያዊ መሆኔ ኩራት እንዲሰማኝ ነው ያደረገኝ እውነት ለመናገር ። እኔ በጣም የምታወቅበት ነገር እንደ ፌንጣ እንጠጥ እንጠጥ እላለሁ ሰዎች በአብዛኛው በዚህ ስለሚያውቁኝ በማህበራዊ ገፅ ይህን ይገልፁልኛል።
ከዚህ ውጪ ግን ዳኝነት የእምነትና የተግባር ስራ ነው። እና በዚህ ውስጥ ደግሞ ተሳታፊ በመሆኔና በአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን የዳኞች ስብሰባ ላይ በዚህ ነገር ስሜ በመጠራቱ ኩራት ይሰማኛል። ለዚህም ክብርና ኩራት ፌዴሬሽኑን ፣ ክለቦችን ፣ ያሳደገኝን ማህበረሰብን ፣ ያስተማሩኝ መምህራን አና ጓደኞቼን ላበረከቱልኝ አስተዋጽኦ ባመሰግናቸው ደስ ይለኛል።
ሀትሪክ ፦ የጨዋታ ምደባዎችን ለማግኘት የነበረው ፉክክርስ ምን ይመስል ነበር ?
ባምላክ ተሰማ ፦ የተሰጡን ፈተናዎች ከባድ የነበሩበት ፤ እነዛን ፈተናዎች ካለፍን በኋላ ደግሞ እዛ ያሉ እያንዳንዱ ልምምዶች የምትመደበውን የጨዋታ ምድባ የምትወስንበት ነው።
ልምምድ ላይ በምታሳየው ብቃት ፤ በምትወስደው ፈተና እንዲሁም በምትታመጣው ውጤት እንጂ ከዚህ በፊት ባለህ ስም ፣ የስራ ሁኔታ ወይም ባለህ ዕውቅና አይደለም ጨዋታ የምትመደበው።
ሰርተህ ተወዳድረህ ምደባዎችን የምታገኝበት እና ከፍተኛ የሆነ ትኩረት የሚጠይቅ እያንዳንዱን ጨዋታ እዛ ለመቆየት ወሳኝ የሆነበት ነው ማለት ይቻላል ።
ሀትሪክ ፦ ከካፍ አመራሮች እና ከጨዋታ ገምጋሚዎች የተሰጡህ ግብረ መልሶችስ እንዴት ነበሩ?
ባምላክ ተሰማ ፦ እኔ የተለየ አሯሯጥ ነው ያለኝ እና እንደ ፌንጣ ስለምሮጥ ለይተው ያውቁኛል። እናም ብዙዎች ስለኔ ይነግሩኛል ። ከዚህ ውጪ ይሄንን የዳኝነት ውጤት ጥሩ እንደሰራን በተለያዩ ሚዲያዎች ፤ በተለያዩ ገለልተኛ ተቋማት ወይም ታዋቂ ግለሰቦች የተገለፀበት ነው ።
የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ከአመት በፊት ጠንክሮ በመስራቱ ከዛም በኋላ በተከታታይ ሶስት ወራት ስልጠና በመስጠት ፤ ከፍተኛ የሆኑ ፈተናዎችን በማዘጋጀትና ከፍተኛ የሆነ ክትትል በማድረግ ይሄንን ውጤት ሊያመጣ ችሏል ።
ከዚህ ውጪ በገረመኝ መልኩ እኔ ለአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ያለኝን ምግባር እና ሀላፊነት በዚሁ እንድቀጥል ለሌሎች አርአያ መሆኔን የተገለፀበት በዚህ ሁኔታ እኔንም ሀገሬንም የሚያስደስት ሆኖ ያገኘውበትና በጣም የተደሰትኩበት ነው። በህይወቴ ውስጥ እስካሁን ከተሳተፍኩባቸው ጨዋታዎች የአፍሪካ ዋንጫዎች በዝግጅቱም በሁሉም ነገር ከፍተኛ የነበረበትና እኔም እንደ እግዚአብሔር ቸርነት በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የመሆን እድሉን በማግኘቴ በጣም የተደሰትኩበት ነው ማለት እችላለሁ ።
ሀትሪክ ፦ በአንድ ልምምድ ወቅት በርካታ ሴት ተጫዋቾች ከበውክ አብረውክ ፎቶ ተነስተው ተመልክቼ ነበር ። እሱን አጋጣሚ አንሳልኝ እስኪ?
ባምላክ ተሰማ ፦ የቅድመ ጨዋታ ልምምዶችን በምንሰራበት ጊዜ የሚዲያ ቀን የሚባል አለ። በዚህ የሚዲያ ቀን አጠቃላይ የዳኝነቱ ሁኔታና ምን እየተሰራ እንደሆነ ከምድብ ጨዋታ ጀምሮ ምልከታ አለ ።
እኔ ከጨዋታ ቀጥሎ እረፍት ነበር የምሆነው ካፍ ይሄንን ፕሮግራም መካፈል ስላለብን የዛን ቀን እረፍት የነበርን ዳኞችን በሙሉ ወደ ልምምድ እንድንሄድ ያደርጋል። በዛን ወቅት ልምምዶችን እዛ ሰራን ።
ከዛን ያለውን ዝግጅት አጠቃላይ የዳኝነት ዝግጅት የስልጠና ሁኔታ ለሚዲያ አካላት ከገለፅን በኋላ ልምምዴን ጨርሼ ለመውጣት በምዘጋጅበት ሰአት የአሴክ ሚሞሳስ ክለብ ሴት ተጫዋቾች ልምምድ በምንሰራበት ሜዳ በኩል ያልፉ ነበር ።
ባልጠበኩት መልኩም ወደኔ መተው ደስታቸውን ፣ ያላቸውን ክብርና አድናቆት አሳይተውኛል ። ጨዋታዎችን ይመለከታሉ በዛም አጋጣሚ ዳኝነቱን በሚገባ ያዩታልና ከዛ የተነሳ ነበር ።
በውድድሩ ካሰሰገረሙኝና ካስደነገጡኝ አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ነው ።
ሀትሪክ፦ ቫር በአፍሪካ ዋንጫውን በሚገባ ተተግበሯል ። ከቫር ጋር ያለውስ ቁርኝተ መላመዱ እንዴት ይገለፃል?
ባምላክ ተሰማ ፦VAR በሀገራችን ውስጥ ስለማይደረግ በእንደነዚህ አይነት ውድድሮች ውስጥ ስመጣ ከ”VAR” ጋር ራሴን ለማላመድ ቀን ከለሊት ነው የምሰራው ። VARን መላመድ ያስፈልጋል። አዲስ መሳሪያ ነው ዳኝነትን ከቴክኖሎጂ ጋር አጣምረህ የምሰራበት ነው።
ለዚህ መሳካት ደግሞ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ በጥሩ ባለሙያዎች ነበር ትምህርቱን የሚሰጠን። በአብዛኛው ተሳክቶልኛል ማለት እችላለሁ በዚህ ደረጃ ሳየው ራሴንም ከVAR ጋር ለማላመድ ጊዜ አልወሰደብኝም።
ሀትሪክ፦ አመሰግናለሁ ።
ባምላክ ተሰማ:- አመሰግናለሁ ።