የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ የካቲት 11 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ መርሃ ግብር በተደረጉ ጨዋታዎች አምስቱ በመሸናነፍ ቀሪ ሶስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ 16 ጎሎች በ15 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 41 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ የተመዘገበ ቀይ ካርድ የለም።
በሳምንቱ በሁለት ተጫዋቾች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ብርሃኑ በቀለ(ሲዳማ ቡና) እና እዬብ አለማየሁ(ሀዋሳ ከተማ) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቀቂያ የተመለከቱ ሲሆን ተጫዋቾቹ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል ።
- ማሰታውቂያ -
በሁለት ክለቦች ላይም ተመሳሳይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ከሀድያ ሆሳዕና ተጫዋቾች ሳሙኤል ዬሀንስ፣ ቃለዓብ ውብሸት፣ ብሩክ ማርቆስ፣ ያሬድ በቀለ እና ዳግም ንጉሴ እንዲሁም ከኢትዮጵያ መድን ተጫዋቾች ዮናስ ገረመው፣ ጆርጅ ደስታ፣ በርናንድ ኦቼንጌ፣ አቡበከር ኑራ እና መስፍን ዋሼ በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ሁለቱ ክለቦች የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡