ከስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ባሳለፍነዉ ሳምንት ባለ ሜዳዉን አዳማ ከተማ ሁለት ለዜሮ በሆነ ዉጤት በመርታት ለዛሬው የአስራ ዘጠነኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጨዋታ የበቃዉ የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን ሀዋሳ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 3ለ2 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ከጨዋታው የሚገኘዉ ውጤት ለሁለቱም ወሳኝነቱ ከፍ ያለ በነበረው ጨዋታም ሀዋሳ ከተማ በ433 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገባ በተመሳሳይ የአሰልጣኝ ገ/ክርስቶስ ቢራራዉ ወልቂጤ ከተማም በ433 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምሯል። ተመጣጣኝ የሚባል የጨዋታ ፉክክር ባስመለከተዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ሀዋሳ ከተማ በ4ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሳሙኤል አስፈሪ ራሱ መረብ ላይ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን የቻለበትን አጋጣሚ መፍጠር ችሏል።
ከዚች ግብ መቆጠር ከ27 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አጥቃዉ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ያሻማዉን ኳስ ብዙየአሁ ሰይፈ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ በማድረግ ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል። ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ባስመለከተን የሁለቱ ክለቦች ተጠባቂ ጨዋታም የመጀመሪያው አጋማሽ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾችን ቀይረዉ በማስገባት የበላይነት ለመውሰድ ሲጥሩ የተስተዋለ ቢሆንም በጨዋታው ተደጋጋሚ ሙከራን ማድረግ ችሎ የነበረዉ አጥቂዉ ሙጅብ ቃሲም በ70ኛዉ ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥሮ ሀዋሳ ከተማ ሁለት ለአንድ እንዲመራ ማድረግ ችሏል።
ሁለተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ክትፎቹ በ77ተኛዉ ደቂቃ በአምበላቸዉ ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ ውጭ አስደናቂ የሚባል ጎል አስቆጥሮላቸዉ ወደ ጨዋታው መልሷቸዋል።
አቻ ከሆኑ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች አሸናፊ የሚያደርጋቸውን ጎል ለማግኘነት በሚጥሩበት የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃም ሀዋሳ ከተማዎች አሸናፊ የሆኑበትን ጎል ማግኘት ችለዋል። በዚህም ከመሐል ሜዳ አካባቢ የተሻገረዉን ኳስ የወልቂጤ ከተማዉ ተከላካይ ሳሙኤል አስፈሪ በራሱ ግብ ላይ በጨዋታው ለሁለተኛ ጊዜ አስቆጥሯል። መደበኛዉ ዘጠና ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት ላይም የወልቂጤ ተከማዉ አማካይ ቡዙአየሁ ሰይፈ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጨዋታውንም ሀዋሳ ከተማ 3ለ2 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 31 ከፍ በማድረግ የአራተኝነት ደረጃውን ማስጠበቅ ችሏል።