ከቀናቶች በፊት አዲስ አሰልጣኝ የሾመው ኢትዮጵያ ቡና በስካይ ላይት ሆቴል እየሰጠ ባለው መግለጫ አሰልጣኙን በይፋዊ ፊርማ ቀጥሯል።
ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ ቡናን ለማሰልጠን የተስማሙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ መድን እንዲሁም በርካታ ክለቦችን ያሰለጠኑት አሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ በዛሬው ዕለት ለሁለት አመት በሚቆይ ውል ፊርማቸውን ለኢትዮጵያ ቡና አስፈርመዋል። ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብን ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሸጋገር አንዱ መርሀግብር የሆነው የአሰልጣኝ ቅጥር ነው ያሉት የክለቡ ፕሬዚዳንት ዶ/ር እስራኤል ደገፋ ኢትዮጵያ ቡና እንደ ሀገር እግር ኳሱ እንዲነቃቃ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር በተያዘው አመት ቡና እንደ ሀገር አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል ያሉ ሲሆን ከ1976 ጀምሮ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ክለቡ እንዲጠናከር ሲሰራ መቆየቱን አውስተው ኢትዮጵያ ቡና በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን በአፍሪካ ደረጃ ምሳሌ የሚሆን ክለብ ለማድረግ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ፅኑ ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል።
ከ16 አመት በኋላ በድጋሜ ወደ ኢትዮጵያ ቡና መመለሳቸውን የተናገሩት የክለቡ አዲሱ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ ዕድሉን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ክለቡ የጣለባቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡና ለተሻለ ክብር እንደሚያበቁት ተናግረዋል። አሰልጣኙ በክለቡ ውል ያላቸው ስምንት ተጫዋቾች መኖራቸውን ገልፀው በዝውውር ቡድኑን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ከክለቡ አካላት ንግግሮች በኋላ በአሁኑ ሰዓት የሚዲያ አካላት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተሰጠበት ይገኛል።
አስተያየት ይስጡ