በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚዘጋጁ አመታዊ ውድድሮች መካከል ዋነኛው የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፕዮና ለ52ኛ ጊዜ ከማክሰኞ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ይደረጋል ።
ውድድሩ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የሚካሄድም ይሆናል ።
ይህ አገር አቀፍ ሻምፒዮና ብርቅዬና ጀግኖች አትሌቶችን ለማፍራት የተቻለበት፣ ሁሉንም የአትሌቲክስ የውድድር ተግባራትን አካቶና ደረጃውን ጠብቆ የሚካሄድ በመሆኑ ለአገሪቱ የአትሌቲክስ ስፖርት እድገት የጎላ ሚና የተጫወቱ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳድሮች፣ ክለቦች፣ ተቋማትና ማሰልጠኛ ማዕከላት ምርጥ አትሌቶቻቸውን ይዘው የሚሳተፉበት መድረክ ነው፡፡
ውድድሩ በዋነኝነት ሶስት አላማዎችን ይዞ የሚደረግ ሲሆን እ.ኤ.አ ከኦገስት 19-27/2023 በሃንጋሪ – ቡዳፔስት ለሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች አቋማቸውን እንዲለኩ እድል ለመፍጠር ፤ በክልሎች፣ በከተማ አስተዳድሮች፣ በክለቦችና በማሠልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል ።
- ማሰታውቂያ -
በውድድሩ ከ11 ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከ30 ክለቦች እና ተቋማት የተወጣጡ 1,270(743 ወንዶች እና 527 ሴቶች) አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ።
በውድድሩ ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከልም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በአለም መድረክ ከፍ ያደረጉ በርካታ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ። ከነዚህም መካከል ኃ/ማርያም አማረ ፣ አክሱማዋት እምባዬ፣ ሰለሞን ባረጋ ፣ ሰንበሬ ተፈሪ ፣ መቅደስ አበበ ፣ ሳሙኤል አባተ ፣ ሙክታር እንድሪስ ፣ ዳዊት ስዩም ፣ ኤርሚያስ ግርማ ፣ ወርቁውሃ ጌታቸው ፣ ጌትነት ዋለ ፣ ዘርፌ ወ/አገኝ ፣ በሪሁ አረጋዊ፣ ሀብታም አለሙ፣ ታደሰ ወርቁ ፣ ሂሩት መሸሻ ፣ ሐጐስ ገ/ሕይወት ፣ ፅጌ ገ/ሰላማ፣ ሞገስ ጥዑማይ ፣ ግርማዊት ገ/እግዛብሔር ፣ ለሜቻ ግርማ፣ ያለምዘርፍ የኋላው ፣ ቦኪ ድሪባ ፣ ብርቄ ኃየሎም ፣ ተሬሣ ቶሎሣ፣ ፎቴይን ተስፋይ እና ለተሰንበት ግደይ ተጠቃሾች ናቸው ።
ለውድድሩ 2,783,644.90 /ሁለት ሚሊየን ሰባት መቶ ሰማኒያ ሦስት ሺ ስድስት መቶ አርባ አራት ከ90/100 ብር/ ተመድቧል ።
ውድድሩን የሚመሩ በአለም አትሌቲክስ ደረጃ ኮርስ የወሰዱ 80 ዳኞችም ተመድበዋል ።