ተሰናባቹ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ክለቡ ያቀረበለትን በስምምነት እንለያይ ጥያቄ ውድቅ አደረገ።
ከደቂቃዎች በፊት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እንደተናገረው” ከኢትዮጵያ ቡና የቀረበልኝ በስምምነት የመለያየት ጥያቄን ብቀበለውም የስምምነቱ ይዘት ላይ ጥያቄ በማንሳት የስንብት ደብዳቤውን ሳልቀበል ወጥቻለሁ ውሉ ላይ ከመጀመሪያ ዙር 30 ጨዋታ 75 በመቶ ወይም ከ1-3 ማሳካት ይላል በ15ቱ ጨዋታ ላይ ባላሳካም ከ1-3 የሚለውን አሳካለሁ ብልም አልተቀበሉኝም እኔም በስምምነት የሚለውን ጥቅማ ጥቅሜና ደመወዜ ላይ ያለውን ባለመቀበሌ የሰጡኝን ደብዳቤ ሳልወስድ ወጥቻለሁ” ብሏል። አሰልጣኙ እንዳለው ” በውል መቋረጡ ላይ ፍቃደኛ ነኝ ነገር ግን በውሌ መሠረት ያለኝ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም ዙሪያ ላይ ከጠበቃዬ ጋር ተነጋግሬ አሳውቃለሁ” ብሏል። አሰልጣኙ ግን ደብዳቤውን ተቀብሎ ምላሽ መስጠት እየቻለ አልቀበልም ማለቱ ለሌላ ውዝግብ በር እንዳይከፍት ስጋት ፈጥሯል።
በጉዳዩ ዙሪያ የተጠየቁት የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ግን ” በውላችን መሠረት አሰናብተነዋል። ውሉ ከጨዋታው 75 በመቶ ድል ማሳካት አለበለዚያ ከ1-3 መውጣት ከሚለው አንዱን ካላሳካ የማሰናበት መብት አለን ለዚህም ነው ያሰናበትነው” ሲሉ ገልጸዋል። ዋና ስራ አስኪያጁ እንደተናገሩት “በውሉ መሠረት ከሁለቱ ተዋዋዮች አንዱ ውል ማቋረጥ ከፈለገ ከአንድ ወር በፊት አሳውቆ ውሉን ማቋረጥ ይችላል ይላል እኛም በውላችን መሠረት ከታህሳስ 30/2015 ጀምሮ ውላችንን አቋርጠናል ብለን ነግረነዋል ደመወዙን ይከፈለዋል ቡድኑ ጋር መሄድ ግን አይችልም” በማለት የክለቡን አቋም አሳውቀዋል።
ኢትዮጵያ ቡና በሀድያ ሆሳዕና የደረሰበት የ1ለ0 ሽንፈት የአሰልጣኙን ስንብት ያረጋገጠ ሲሆን በያዘው 14 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው ከመሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ መድን በ8 ነጥብ አንሶ መገኘቱ አመራሮቹን ያበሳጨ ይመስላል።