በሊጉ የ24ኛ ሳምንት ሁለተኛ መርሀግብር ጥሩ አቋም ላይ የሚገኙትን አዳማ ከተማን ከባህርዳር ከተማ አገናኝቶ በባህርዳር ከተማ የ1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በ23ኛው ሳምንት ጨዋታ ከወላይታ ድቻ ነጥብ በተጋራው አዳማ ከተማ በኩል በጨዋታው ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦች ሲደረጉ አቡበከር ወንድሙ እና ቦና አሊ አዲስ ተስፋዬን እና አሜ መሀመድን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል ። በባህርዳር ከተማ በኩል በሳምንቱ ኢትዮጵያ ቡናን በረቱበት ጨዋታ ላይ በነበረው ምርጥ 11 ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የአሰልጣኝ ይታገሱው አዳማ ከተማ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ግብ ቀርቦ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻለ ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በባህርዳር ከተማ በኩል በተወሰደባቸው ብልጫ የመልሶ ማጥቃት ሂደቶች ለመጠቀም የተገደዱ ቢሆንም እንዚህ እንቅስቃሴዎች ያን ያህል ለአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ፈታኝ አልነበሩም ።
በ8ኛው ደቂቃ ላይ ቦና አሊ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ የመታው እና በፋሲል ገብረሚካኤል የተያዘው ኳስ የጨዋታው ቀዳሚ የግብ ሙከራ ነበር ።
በጨዋታው 12ኛ ደቂቃ ላይ አማኑኤል ጎበና ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በቢንያም አይተን ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል ።
በ14ኛው ደቂቃ ላይም ተቀይሮ በገባው ቢንያም አይተን ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ በጠንካራ ምት ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወጥቷል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ዮሴፍ ታረቀኝ በጨዋታ እንቅስቃሴ ከሳጥን ውጪ ያደረገው የግብ ሙከራ በፋሲል ገብረሚካኤል ተይዟል ።
በጣና ሞገዶቹ በኩል የሚደረጉት የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች አንድም ጠንካራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲሳናቸው በ21ኛው ደቂቃ ላይ በፍራኦል ተስፋዬ ከቅጣት ምት በተሞከረ ኢላማውን የጠበቀ ኳስ የመጀመሪያውን ሙከራ አድርገዋል ።
በቀጣዮቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ቀሪ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል ግብ ጠባቂዎቹን የፈተነ የግብ ሙከራ ሳይታይ ቢቆይም በመጨረሻ ላይ ፍፁም ጥላሁን ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ ምናልባትም የጣና ሞገዶቹን አጋማሹን በመሪነት ማጠናቀቅ የሚያስችል ነበር ።
ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም በኩል ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥረቶች የተደረጉበት ነበር ።
በአጋማሹ ቀዳሚው የግብ ሙከራም በአዳማ ከተማ በኩል ሲደረግ ቦና አሊ ያደረገውን ጠንከር ያለ የግብ ሙከራ በፋሲል እጆች ላይ አርፏል ።
በአዳማ ከተማም ሆነ በባህርዳር ከተማ ዘንድ የተደረጉት የግብ አጋጣሚዎች የማግኘት እንቅስቃሴዎች በግብ ሙከራዎች ሳይታጀቡ ቢቆዩም መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አስራ አንድ ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ጨዋታው ግብ ተቆጥሮበታል ። ባህርዳር ከተማ ! አደም አባስ !
በአጋማሹ ተቀይሮ የገባው አደም አባስ ከዱሬሳ ሹቢሳ የደረሰውን ኳስ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፎታል ።
በቀጣዮቹ የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ አዳማ ከተማዎች ተጭነው በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ጨዋታው በባህርዳር ከተማ የ1 – 0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 12(ቅዳሜ) ከ9:00 ጀምሮ አዳማ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ሲጫወት በተከታዩ ቀን በተመሳሳይ ሰዓት ባህርዳር ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታል ።