በ24ተኛዉ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በወራጅ ቀጠናዉ ላይ የሚገኘዉን ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ለ0 በሆነ ጠባብ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ዘጠነኛ ላይ የተቀመጠዉ የአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬው ኢትዮጵያ ቡና እና በወራጅ ቀጠናው አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠዉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባደረጉት የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታም ሁለቱም ክለቦች በሜዳዉ የመሐል ክፍል ላይ የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ ቢሆንም በሙከራ ረገድ ግን ቡናማዎቹ የተሻሉ ሁነዉ ተስተውሏል።
በዚህም ጨዋታዉ ከጀመረበት ደቂቃ አንስቶ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ቡናማዎቹ በ12ተኛዉ ደቂቃ ላይ በወጣቱ የቀኝ መስመር ተመላላሽ ቃልአብ አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም ተከላካዩ ተስፋ በቀለ መልሶበታል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከግብ ጠባቂዉ የተሻገረለትን ኳስ አጥቂዉ መሐመድኑር ናስር ከኤሌትሪክ ተከላካዮች ጋር ታግሎ ሞከሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ በግቡ አናት ላይ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም የተሻለ ብልጫ መውሰድ የቻለዉ ኢትዮጵያ ቡና በ35ተኛዉ ደቂቃ ግብ ለማሰቆጠር ተቃርቦ ነበር ፤ በዚህም አጥቂዉ ጫላ ተሽታ ለአማኑኤል ያቀበለዉን ኳስ መሐመድኑር ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥታለች።
ጥሩ ጥሩ የሚባሉ የግብ ዕድሎችን ማግኘት የቻለዉ ጫላ በ34ተኛዉ ደቂቃ አስቆጪ የሚባል ሙከራን ካደረገ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በድጋሚ ጫላ ተሽታ ከሮቤል የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላቱ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በመጀመሪያው ኢጋማሽ ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገር የተስተዋለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአጋማሹ በአብዛኛው ሀይልን የቀላቀለ የጨዋታ መንገድ እና አልፎ አልፎ በሚገኙ አጋጣሚዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ወደ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ተስተውሏል።
ከዕረፍት መልስ መልስ ሁለቱም ቡድኖች ተሻሽለዉ ወደ ሜዳ ሲመለሱ በ54ተኛዉ ደቂቃ ላይም ቡናማዎቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ በዚህም የኤሌትሪኩ የመሐል ተከላካይ ተስፋየ በቀለ ሳጥን ውስጥ ኳስን በእጁ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሮቤል ተክለሚካኤል ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ በሙከራ ረገድ እምብዛም ባልነበረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ቡናማዎቹ በመሐመድኑር እና እነተነህ ተፈራ አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ግን ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁለተኛዉ አጋማሽም ሙከራዎችን ለማድረግ ሲቸገሩ የተስተዋሉት ኤሌትሪኮች በ77ተኛዉ ደቂቃ ላይ አማካዩ አብነት ደምሴ ከሳጥን ውጭ ካደረገዉ ሙከራ ውጭ በሙሉ ዘጠና ደቂቃ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዉ በኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 በሆነ ዉጤት ተሸንፈዋል።
ዉጤቱን ተከትሎም ድል የቀናዉ ኢትዮጵያ ቡና በ34 ነጥብ ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችል ፤ በተቃራኒው ኤሌክትሪክ በ11 ነጥቦች አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።