በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22 ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብር የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታ የአሰልጣኝ ፀጋየ ኪዳነ ማርያሙ ቡድን ወላይታ ዲቻ ለገጣፎ ለገዳዲን 2ለ0 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል።
በዉጤት ደረጃ ለሁለቱም ክለቦች እጅግ አስፈላጊ በነበረዉ የዕለቱ ጨዋታም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ 25 ያህል ደቂቃዎች የጦና ንቦቹ የጨዋታውን የበላይነት ወስደዉ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን ነገር በነዚህ አጋጣሚዎች ደግሞ እምብዛም በርከት ያሉ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ሲሞክሩ አልተመለከትንም።
በነዚህ ደቂቃዎች ዉስጥ የበላይነታቸዉ ከፍ ያለ የነበሩት ዲቻዎች ግብ አያስቆጥሩ እንጅ ተጠቃሽ የሚባል ሙከራዎችን ግን በዘላለም አባተ ስንታየሁ መንግስቱ እና አበባየሁ ሀጂሶ አማካኝነት ሲያደርጉም ተስተውሏል። በተለይ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በመጣ ቁጥር ጫናቸዉን አጠንክረው የቀጠሉ የሚመስሉት ዲቻዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በ37ተኛዉ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትንም ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የዲቻዉ ግብ ጠባቂ ቢኒያም ገነቱ በረጅሙ የላከዉን ኳስ የለገጣፎ ተከላካዮች በሚገባ ባለማፅዳታቸዉ ምክንያት የተገኘችዉን ዕድል ተጠቅሞ ስንታየሁ መንግስቱ ከርቀት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማደድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ምንም እንኳን በጨዋታው የመጀመሪያ 35 ያህል ደቂቃዎች ብልጫ ተወስዶባቸዉ ግብ ያስተናገዱት ለገጣፎች የመጀመሪያዉ አጋማሽ ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን በመጠኑም ቢሆን ወደ ጨዋታው ገብተዉ ሙከራዎችን ለማድረግ ሲጥሩ የነበረ ቢሆንም ዉጥናቸዉ ሰምሮ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ የመጀመሪያዉ አጋማሽ በዲቻዎች 1ለ0 መሪነት ተገባዷል።
ከዕረፍት መልስም በመጀመሪያዉ አጋማሽ የነበራቸዉን የበላይነት ማስቀጠል የቻሉት ዲቻዎች በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ከዲቻ የቀኝ ማጥቃት በኩል ያሻማዉን ኳስ በረከት በግንባሩ ለአበባየሁ አቀብሎት አበባየሁ በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ግቦነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።
በሁለተኛዉ አጋማሽም የበላይነታቸዉ ከፍ ያሉ የነበሩት ዲቻዎች ሁለተኛ ግብ ካስቆጠሩ በኋላም የጨዋታው ሂደት በተወሰነ መልኩም ቢሆን አቀዝቅዘዉ የመሐል ሜዳውን የበላይነት በመቆጣጠር ደቂቃዎችን ለመግፋት ሲጥሩ በተቃራኒው በብዙ ረገድ በጨዋታዉ የወረደ እንቅስቃሴ ያደረጉት ለገጣፎች በአጥቂዉ ኢብሳ በፍቃዱ እና አማኑኤል አረቦ አማካኝነት አንድ ሁለት ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ በጨዋታው ሁለት ለዜሮ ተሸንፈዋል። ዉጤቱን ተከትሎ ወላይታ ዲቻ በ30 ነጥብ በነበረበት ዘጠኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በተቃራኒው በጨዋታው ሽንፈት ያስተናገደዉ የአሰልጣኝ ዘማርያም ቡድን ለገጣፎ ለገዳዲ ደግሞ በ11 ነጥቦች የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።