አስገራሚ የጨዋታ እንቅስቃሴ በታየበት የምሽቱ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ሀድያ ሆሳዕናን ከኋላ ተነስቶ 2 – 1 አሸንፏል ። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው የእርስ በርስ የሜዳ ላይ ፉክክር ብዙ መልኮች የነበሩት ነው ።
በጨዋታው በፋሲል ከነማ በኩል ሀዋሳ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ ምርጥ አስራአንድ ላይ ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከለገጣፎ ለገዳዲ አቻ በተለያዩበት ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ በፀጋዬ ብርሀኑ እና ራምኬል ሎክ ምትክ ዳግም ንጉሴን እና ተመስገን ብርሀኑን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሀድያ ሆሳዕናዎች በተሻለ የበላይነት መንቀሳቀስ የቻሉበት ነበር ። ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ማግኘት ቢችሉም ሳይጠቀሙባው ለረጅም ደቂቃዎች ቆይተዋል ።
በ20ኛው ደቂቃ ላየ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ ተመልሶ ወቷል ።
- ማሰታውቂያ -
በፋሲል ከነማ በኩል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ከመድረስ እና የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር ይህ ነው ሊባል የሚችል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለማሳየት ተቸግረው ቆይተዋል ።
በጨዋታው 32ኛው ደቂቃ ላይ የስታድየሙ መብራት መጥፋቱም ተከትሎ ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንዲቋረጥም አድርጓል ።
የስታድየሙ መብራት ተመልሶ ጨዋታው በቀጠለበት አጋጣሚ አፄዎቹ ቀደም ብሎ ከነበራቸው የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ለመሳየት ችለውም ነበር ። በዚህም በ34ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ኦሴ ማውሊ ከመስመር ተሻግሮለት በግንባር የገጨው ኳስ በፔፔ ሰይዶ ግብ ከመሆን ድኗል ።
አጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ግን ሀድያ ሆሳዕናዎች መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ። የሀድያ ሆሳዕናው አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ያገኘውን ኳስ ለመጠቀም ሲሞክር በሳማኪ ሚካኤል ጥፋት ተሰርቶበት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ራሱ ባዬ ገዛኸኝ ከመረብ አሳርፎታል ።
ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እጅግ በርካታ ትዕይንቶች የተስተናገዱበት ነበር ። በአጋማሹ ፋሲል ከነማዎች ይበልጥ የተሻለ ሆነው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር ።
በተለይም ልክ አጋማሹ በተጀመረ ሰከንዶች ውስጥ አለምብርሀን ይግዛው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ድንቅ ሙከራ በፔፔ ሰይዶ ግብ ከመሆን ድኗል ።
በ51ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ከሳጥን ውጪ ያደረገው እና በሳማኪ ሚካኤል የተመለሰው ሙከራ በአጋማሹ ለሀድያ ሆሳዕና የመጀመሪያም የመጨረሻም የግብ ሙከራ ሆኗል ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ዱላ ሙላተለ ከታፈሰ ሰለሞን የደረሰውን ግሩም ኳስ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም በግብ ጠባቂው ተመልሷል ።
በአፄዎቹ በኩል በተለይም የሽመክት ጉግሳ እና የሱራፌል ዳኛቸው ተቀይረው ወደ ሜዳ መግባታቸው የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር ግልፅ አጋጣሚዎች ማግኘት ችለዋል ።
በዚህም ከሁለቱ ተጫዋቾች እግር በተነሱ ኳሶቸሰ ግቦች ተቆጥረዋል ።
ሱራፌል ዳኛቸው ተቀይሮ በገባበት አጋጣሚ በመጀመሪያ የኳስ ንክኪው ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ተመልሷል ።
በ74ኛው ደቂቃ ላይም ኦሴ ማውሊ ከሽመክት ጉግሳ የደረሰውን አስደናቂ ኳስ ከመረብ በማሳረፍ የጨዋታውን ውጤት ወደ 1 – 1 ቀይሯል ።
ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላ በተለይም አፄዎቹ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው ለማሸነፍ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ጥረቶች የተደረጉበት እና ከጨዋታ ላይ እንቅስቃሴ ባለፈም የተጫዋቾች የእርስ በርስ ሹክቻ በተደጋጋሚ የታየበት ነበር ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይም አፄዎቹ ከመመራት ተነስተው ድል ያደረጉበትን ግብ አስቆጥረዋል ።
ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ በግንባር ገጭቶት በፔፔ ሰይዶ ሲመለስ በቅርበት የነበረው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
በመጨረሻም አፄዎቹ በ2 – 1 ድል ሶስት ነጥቦችን ማሳካት ችለዋል ።