በሊጉ የ22ኛ ሳምንት ሶስተኛ መርሀግብር ባህርዳር ከተማን ከአርባምንጭ ከተማ አገናኝቶ 2 – 2 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በጨዋታው በሁለቱም ክለቦች በኩል ካለፈው ሳምንት ጨዋታዎቻቸው አንድ አንድ ለውጦችን አድርገዋል ።
በባህርዳር ከተማ በኩል ከኢትዮጵያ መድኅን አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ በአምስተኛ ቢጫ ምክንያት ባልተሰለፈው አለልኝ አዘነ ምትክ ፍቅረሚካኤል አለሙ ሲሰለፍ በአርባምንጭ ከተማ በኩል በሳምንቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ እንዳልካቸው መስፍንን በአቡበከር ሻሚል ተክተው ገብተዋል ።
የዘጠኝ ሰዓቱ ጨዋታ ገና በጊዜ ነበር በሁለቱም በኩል ግቦች የተስተናገዱበት ነበር ። በሶስተኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ በፍራኦል መንግስቱ አማካኝነት ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ከግቡ በርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት የግራ መስመሩ ተከላካይ ፍራኦል መንግስቱ ወደ አርባምንጭ ከተማ የግብ ክልል ሲያሻግረው የአርባምንጭ ከተማው ግብ ጠባቂ የሰአት አጠባበቅ ስህትት ታክሎበት ኳስ እና መረብ ተገናኝተዋል ።
በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመሩት አርባምንጭ ከተማዎች ከአፍታ በኋላ መልስ የሰጡበትን ግብ አግኝተዋል ። አማካዩ እንዳልካቸው መስፍን ከግራ መስመር አቅጣጫ የተገኘውን የቅጣት ምት ልክ እንደ ፍራኦል ሁሉ ለቡድን አጋሮቹ ያሻገረው ኳስ በ5ኛው ደቂቃ ከመረብ አርፏል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ጨዋታው ልክ እንደ አጀማመሩ መቀጠል አልቻለም ።
ሁለቱም ክለቦች እየተፈራረቁ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ቢጥሩም ሌላ ግብ ለማከል ሳይችሉ አጋማሹን ለማጠናቀቅ ተገደዋል ።
በ16ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ፉአድ ፈረጃ ማግኘት ችሎ የነበረ ቢሆንም ወደ ግብ የመታው ኳስ ጠንካራ ባለመሆኑ በቀላሉ በግብ ጠባቂው ተይዟል ።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል በተለይም በቀኝ መስመር በኩል በሚሻገሩ ኳሶች ኳስ እና መረብን ለማገናኘት የተደረጉ ጥረቶች ስኬታማ አልነበሩም ።
ቀድመው ከተቆጠሩት ግቦች በኋላም ሌላ ጠንካራ የግብ ሙከራም ሆነ ግብ ሳይታይ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል ።
በጨዋታው የሁለተኛ አጋማሽ በማጥቃቱ ላይ አደም አባስን በዱሬሳ ሹቢሳ ተክተው የገቡት ባህርዳር ከተማዎች የተሻለ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ችለዋል ።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም በፊት መስመር ለሚገኘው አህመድ ሁሴን ኳሶችን በማድረስ የግብ ዕድል ለመፍጠር በተወሰኑ አጋጣሚዎች ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ57ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ አገኘሁ በረጅም ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ በአደም አባስ እና ፉአድ ፈረጃ በኩል አልፎ ለሀብታሙ ታደሰ የደረሰውን ኳስ አጥቂው ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም የጣና ሞገዶቹ እጅግ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ መፍጠር ቢችሉም በማይታመን መልኩ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ። በፈጣን መልሶ ማጥቃት ይዘው የሄዱትን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ሆኖ ለአደም አባስ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም ከግቡ በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ሆኖ ከመኮንን መርዶክዮስ የተፋጠጠው አደም አባስ ኳሱን ከግቡ አናት በላይ ልኮታል ።
በአጋማሹ በተለይም ሀብታሙ ታደሰ ወደ ኋላ ተመልሶ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በሚያደርገው አንድ ሁለት ቅብብል ለሌሎች ተጫዋቾች የግብ ዕድሎች ለማመቻቸት ሲጥር ተተስተውሏል ።
በ68ኛው ደቂቃ ላይም ባህርዳር ከተማዎች ዳግም መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። አሸናፊ ፊዳ በሀብታሙ ታደሰ በተደረገበት ጫና ወደ ኋላ መልሶ ለመኮንን መርዶክዮስ ያደረሰውን ኳስ መኮንን መልሶ ለአሸናፊ ለማቀበል በሚያደርገው ጥረት ወቅት ሀብታሙ ኳሱን አግኝቶ ለፉአድ ፈረጃ አቀብሎት 10 ቁጥር ለባሹ ፉአድ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ተቆጥሮባቸው አቻ ለመሆን ብዙ ደቂቃ ያልወሰደባቸው አዞዎቹ በዚህኛው አጋጣሚም ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ዳግም አቻ ሆነዋል ። የፊት አጥቂው አህመድ ሁሴን ከበላይ ገዛኸኝ በግሩም ዕይታ የደረሰውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት በታፔ አልዛየር መረብ ላይ አሳርፎታል ።
በቀጣዮቹ የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች በተለይም በባህርዳር ከተማ በኩል ተጭነው በመጫወት ሌላ ግብ ለማግኘት ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ፉአድ ፈረጃ ከሳጥኑ ጫፍ ላይ ሆኖ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ተመልሷል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በ2 – 2 ውጤት ተጠናቋል ።
በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 1(ማክሰኞ) ከቀኑ 9:00 ጀምሮ ባህርዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ሲጫወት በዕለቱ ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ አርባምንጭ ከተማ ከፋሲል ከነማ ይጫወታሉ ።