በስምንተኛው ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ቀን ጨዋታ ባህርዳር ከተማ የተመስገን ዳናዉን ኢትዮጵያ ቡና 3ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በአንድ ነጥብ ብቻ ተበላልጠው አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩት ሁለቱ ክለቦች በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክር ሲያደርጉ የተስተዋለ ቢሆንም በሙከራ ረገድ ግን የጣና ሞገዶቹ የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል።
በዚህም በጨዋታዉ የመጀመሪያ 15 ያህል ደቂቃዎች በዱሬሳ ሹቤሳ ፣ ፍፁም ጥላሁን እና ኦሴ ማውሊ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት ባህርዳር ከተማዎች በ22ኛዉ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህም የመስመር ተጫዋቹ ዱሬሳ ሹቤሳ በግራ መስመር በኩል ኳሷን ገፍቶ ወደ ሳጥን ዉስጥ ሲገባ ጥፉት ቢሰራበትም ኳሷን ኦሴ ማዉሊ በፍጥነት ለፋአድ ፈረጃ አቀብሎት ፉአድ ከሳጥን ዉጭ በቀጥታ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የተረጋጋ የጨዋታ መንገድን የመረጡት ባህርዳር ከተማዎች በድጋሚ መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ከፍ ማድረጉ የሚችሉበን ዕድል ማግኘት ችለዉ የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዚህም በ35ኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል የተቀበለዉን ኳስ ፉአድ ፈረጃ ከርቀት ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ እንደምንም አዉጥቶበታል።
በተቃራኒዉ ቡናማዎቹ ምንም እንኳን በሂደት የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመዉሰድ ጥሩ መንቀሳቀስ ቢችሉም ይህ ነዉ ተብሎ የሚጠቀስ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጠኑም ቢሆን ተሻሽለው ወደ ሜዳ ቢመለሱም በተከላካዮች ስህተት ሁለተኛ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል።
በዚህም በ49ኛዉ ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተሻገረዉን ኳስ የቡናዉ ተከላካይ ወልደአማኑኤል ጌቱ መቆጣጠር ባለመቻሉ ምክንያት አጠገቡ ይገኝ የነበረዉ ፍፁሙ ኳሷን ገፍቶ ሳጥን ዉስጥ ከገባ በኋላ ወደ ግብነት በመቀየር የባህርዳር ከተማን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።
በተጨማሪም በ62ኛዉ ደቂቃ ላይ ክዋኩ ዱሬሳ ሹቤሳ ላይ የሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ፍፁም ጥላሁን ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በጥቂቱም ቢሆን ጫና መፍጠር ችለዉ የነበሩት ቡናማዎቹ በ70ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የጣና ሞገዶቹ ተከላካይ ፈቱዲን ጀማል ጫላ ተሽታ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ኤርትራዊው አማካይ ሮቤል ተ/ሚካኤል ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎቹን ወደ ጨዋታ መልሷል።
በተቃራኒዉ በ73ኛዉ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረዉን ኳስ የቡና ተከላካዮች ለመከላከል በሚጥሩበት ወቅት ኳሷ ተጨራርፋ ወደ ራሳቸዉ ግብ ብትቆጠርም ጥፋት ተሰርቷል በሚል ጎሉ ተሽሯል።
መደበኛዉ የጨዋታ ደቂቃ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቀማዎች ሲቀሩት ግን ባህርዳር ከተማዎች ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም በ88ኛዉ ደቂቃ ላይ ርቤል ተ/ሚካኤል ፋሲል አስማማዉ ላይ የሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ያሬድ ባየ ወደ ግብነት ቀይሮ የጣና ሞገዶቹን የግብ መጠን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሎ ጨዋታዉም በባህርዳር ከተማ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።