“ሀበሻ ቢራ እኛን ስፖንሰር ያደረገው
የአይናችን ከለር ስላማረው አይደለም”
አቶ ገዛኧኝ ወልዴ
/ የኢት.ቡና ዋና ስራ አሰኪያጅ/
” ክለቡ ደጋፊውን የሚመጥን ውጤት ካመጣ 10 ሚሊዮን ብር እንሸልማለን ደጋፊውን የሚመጥነው ደግሞ ሻምፒዮንነት ብቻ ነው”
አቶ ኢዮብ ሃይሉ
/የሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ማርኬቲንግ ዳይሬክተር/
“ይህን ምርጥ ቡድን የአፍሪካ ሻምፒዮን የማድረግ ስራዎች እንሰራለን”
አቶ ሮቤል ሰይዶ
/ አዲሱ የኢትዮጵያ ቡና ማርኬቲንግ አማካሪ /
- ማሰታውቂያ -
ከ2004 ጀምሮ በ1ሚሊዮን ብር ስፖንሰርሺፕ በማድረግ በተጀመረውና ለ12 አመታት በቀጠለው ጥምረታቸው የሚታወቁት ኢትዮጵያ ቡናና ሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ውላቸውን እስከ 2018 ድረስ ዳግም ማደሳቸውን ይፋ አደረጉ።
ዛሬ ከቀትር በኌላ በቤስት ዌስተርን ሆቴል በተካሄደ የፊርማ ስምምነት መሰረት እስከ 2018 ባለው ውል በየአመቱ 22,ሚሊዮን 200 ሺህ ብር ክለቡ እንደሚያገኝ ታውቋል። ሁለቱ ወገኖች ውላቸውን ለአምስት አመት ካደሱ ገና ሁለት አመቱ ሲሆን በመጀመሪያ ስምምነት ወቅት 2 አመት ሲሞላው ዳግም ለመነጋገር በወሰኑት መሰረት ቁጭ ብለው በመወያየት እስከ 2018 ውሉን ማደሳቸውን አስታውቀዋል።
በውሉ መሰረት ኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ከሆነ ሀበሻ ቢራ 10 ሚሊዮን ብር የሚሸልም ሲሆን አሁን ባለው የገበያ ዋጋ አዲስ ሰርቪስ ለመግዛት ሀበሻ ቢራ 20 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር እንደሚከፍል ተገልጿል። ከሁለት አመት በፊት 12.2 ሚሊዮን ብር የነበረው የሰርቪሱ ዋጋ ሀገሪቱ ላይ በተከሰተው የዋጋ ግሽበት ሂሳቡ ወደ 8 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል።
በስምምነቱ መሰረት ክለቡ ራሱን በፋይናንስ እንዲያጠናክርና ተጨማሪ ገቢ እንዲኖረው ለሚሰራው ስራ 5.8 ሚሊዮን ብር ሀበሻ ቢራ የሚመድብ ይሆናል ።
በአዲሱ ውል መሠረት በወንዶችና በሴት ቡድኖቹ በማሊያው ፊት ለፊት ሀበሻ ሎጎን የሚያደርግ ሲሆን በሀገሪቱ ህግና በፌዴሬሽኑ ደንብ መሠረት ከ21
አመት በታች ያሉ ታዳጊዎች አልኮል ያለባቸውን መጠጦች እንዳያስተዋውቁ ስለሚከለክል በታዳጊ ቡድኑ ንጉስ ቢራ ያለበትን ማሊያ እንደሚለብሱ የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኧኝ ወልዴ ተናግረዋል።
” የኢትዮጵያ እግርኳስ ቢዝነስ አይደሉም እንደዚያም ሆነው ሀሳቡን ሰብረው ገብተው ኳሱን እያገዙ ላሉ ተቋማት ምስጋና ይገባቸዋል ከ2 ክለቦች ውጪ አብዛኞቹ ክለቦች በመንግስት የሚደገፉ በመሆናቸው ብዙም የማርኬቲንግ ስራ ላይሰሩ ይችላሉ ለኛ ግን ዋና ጉዳያችን ነው” ያሉት አቶ ገዛኧኝ ” በፕሪሚየር ሊጉ በሜዳችንም ከሜዳችንም ውጪ ስንጫወት የሀበሻ ሎጎን እንጠቀማለን አብዛኞቹ ክለቦች በብዛት የሚያስተዋውቁት ነገር ስለሌለ በሁለቱም የመጠቀም እድል አለን በሜዳችን ስንጫወት 8 ታፔላ የምንጠቀም ከሆነ ከሜዳ ውጪ 4 ሊሆን ይችላል ይሄ በሊግ ኩባንያው በስታንዳርድ የተቀመጠ ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ማብራሪያ ” ውል የገባነው ከሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ጋር እንጂ ከሀበሻ ቢራዎቹ ጋር አይደለም ያም ሆኖ ግን ምርቶቹን እናስተዋውቃለን ሀበሻ ቢራ እኛን ስፖንሰር ያደረገው የአይናችን ከለር ስላማረውም አይደለም በደጋፊ ማህበሩ አማካይነት ደጋፊዎች የሀበሻ ምርትን እንዲጠቀሙ አልኮል የማይጠጡ ደግሞ የሀበሻ ቢራ ምርት የሆነውን ንጉስን እንዲጠጡ እንሰራለን በውሉ ውስጥ የተካተቱትን ጥቅሞቹንም ለማስከበር እንጥራለን ከ50-60 ሺህ ደጋፊዎች የሚሮጡበትን የሩጫ ውድድሮችን ጨምሮ የተለያዩ ኢቨንቶች ሲኖሩ ከሀበሻ ቢራ ጋር በጥምረት እንሰራለን” ሲሉ አብራርተዋል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ቡና ማርኬቲንግ አማካሪ የሆኑት አቶ ሮቤል ሰይዶ ” 120 ሚሊዮን ህዝብ ባለበት ሀገር የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ቁጥር 6 ሚሊዮን ብቻ ነው ብዬ አልገምትም ….. የደጋፊውን ቁጥር 10 ሚሊዮን አድርሰን ከአፍሪካ ምርጥ 10 ክለቦች መሃል አንዱ ማድረግ እንችላለን የቡና ደጋፊ በመላው አለምን አለ በአሜሪካ በሚካሄደው የኢትዮጵያዊያን ውድድር ላይ 50 በመቶ የኢትዮጵያ ቡናን ማሊያ ያደረገ ነው ወደ አውሮፓ ብትሄዱ ደጋፊው ብዙ ስለሆነ ውድድሩ የኢትዮጵያ ቡና ይመስላል ይህን ደጋፊ ለማምጣት በፕላን የሚሰራ ስትራቴጂ ይዘናል አሀንም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሊሰሩ የታሰቡ ለጊዜው በምስጢር የያዝናቸው ስትራቴጂዎች አሉ በእኛ በኩል ይህን ምርጥ ቡድን የአፍሪካ ሻምፒዮን የማድረግ ስራ እንሰራለን” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ኢዮብ ሃይሉ በበኩላቸው ” ምርት ሳይጀምር ክለብን ስፖንሰር ያደረገ ተቋም ከእኛ ውጪ አላየሁም በተቋማችን ደረጃ እኔ አራተኛ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር ነኝ ከእኔ በፊት የነበሩት ሁሉ በወቅቱ ውሉን የተፈራረሙት ጥናት አድርገው ነው ኢትዮጵያ ቡና ለሀበሻ ቢራ ስትራቴጂካዊ አጋር ነው ክለቡ አሁን ካለው ደረጃ የተሻለ ምርጥ ሆኖ ደጋፊውን በውጤት እስከሚያስደስት ድረስ ድጋፋችን ይቀጥላል” ሲሉ ተናግረዋል።
” በሀገር ደረጃ ፖሊሲ ሲቀየር ፖዘቲቭም ሆነ ኔጌቲቭ የሆነ ተጽዕኖ ይኖረዋል እንደ ሀገር የሚወጡ ፖሊሲዎችን እናከብራለን ነገር ግን እንደ ሀበሻ ቢራ ከተዘጉ በሮች ይልቅ የተከፈተውን በር ማየትን እንመርጣለን” ያሉት አቶ ኢዮብ ” ክለቡ ደጋፊውን የሚመጥን ውጤት ካመጣ 10 ሚሊዮን ብር እንሸልማለን ደጋፊውን የሚመጥነው ደግሞ ሻምፒዮንነት ብቻ ነው” ሲሉ የክለቡን አባላት የሚያነሳሳ አስተያየት ሰጥተዋል።
እስከ 2018 ድረስ የሚዘልቀውን የውል ስምምነት
የኢትዮጵያ ቡና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኧኝ ወልዴና
የሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ኢዮብ ሃይሉ ተፈራርመዋል።