በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በበናማዎቹ የ1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
አዲስ አበባ ከተማዎች በ11ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ ብቻ ያደረጉ ሲሆን እንዳለ ከበደን ወደ ተጠባባቂ ወንበር በማውረድ ቢንያም ጌታቸውን አሰልፈዋል ። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ ከአዳማ ከተማ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ አቤል እንዳለ እና እንዳለ ደባልቄን በዊልያም ሰለሞን እና አቡበከር ናስር ተክተው ገብተዋል ።
ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል ማድረግም ሆነ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው የነበሩት ቡናማዎቹ ለሁለት ጨዋታዎች አጥተውት የነበረውን ወሳኝ ተጫዋቻቸውን አቡበከር ናስርን ማግኘታቸው የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ቀደም ቡው ከነበሩት ጨዋታዎች የተሻለ አድርጎት ነበር ። በአዲስ አበባ ከተማ በኩል በተፈጠረባቸው ጫና ወደ ኋላ አፈግፍገው ለመጫወት የተገደዱ ሲሆን የመከላከል ክፍሉ ላይ በቁጥር በርከት ብለው የኢትዮጵያ ቡናን የማጥቃን ሂደት ለማቋረጥ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተመልክተናል ።
- ማሰታውቂያ -
በ11ኛው ደቂቃ ላይ የሮቤል ተክለሚካኤል የአሰራት ቱንጆ እና የአቡበከር ናስር ቅብብል ወደ ግብ ቀረብ ብሎ የነበረ ቢሆንም ኳሱን መጨረሻ ላይ የሞከረው ኡበበከር ናስር ለጥቂት ወደ ውጪ ወቶበታል ። ከውሀ እረፍት መልስ 33ኛ ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹ የመጀመሪያ ግባቸውን አስቆጥረዋል ። አስራት ቱንጆ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ሮቤል ተክለሚካኤል በጭንቅላት ከኋላው ለነበረው ዊልያም ሰለሞን ያቀበለው ሲሆንን ዊልያምም ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮታል ።
በጨዋታው በአንዳንድ አጋጣሚዎች ይታይ የነበረው የአስራት ቱንጆ እና የአቡበከር ናስር ምርጥ ጥምረት 45+1 ደቂቃ ላይ ወደ ግብ ክልል ደርሶ የነበረ ቢሆንም በአስራት የተመታው ኳስ ወደ ውጪ ሊወጣ ችሏል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በኢትዮጵያ ቡና መሪነት ተጠናቀቀ ።
ሁለተኛው ገና በመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተመለከትንበት ነበር ። ሪችሞንድ ኦዶንጎን እና እንዳለ ከበደን ቀይረው በማስገባት አጋማሹን የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ።
49ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን አዲሱ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ እንዳለ ከበደ በግንባር መግጨት ቢችልም ኳሱ ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከሳጥኑ ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። የተሻገረውን የማዕዘን ምት በመመለስ ወደ ፈጣን መልሶ ማጥቃት መቀየር የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጥሩ የግብ ዕድልን መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ። ታፈሰ ተስፋዬ ለአቡበከር አቀብሎት የነበረ ሲሆን አቡበከርም በፍጥነት እየሮጠ ለነበረው ዊልያም ሰለሞን አድርሶት የነበረ ቢሆንም ዊልያም ሳሙኤል ተስፋዬን በማለፍም ጭምር ለሮቤል ተክለሚካኤል ያቀበለው ኳስ በአዲስ አበባ ተከላካዮች ጥረት ሊወጣ ችሏል ።
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና የማጥቃት ፍላጎት በነበረው በዚህ ጨዋታ በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉበት አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉበት ነበር ። 54ኛ ደቂቃ ላይም ሳሙኤል ተስፋዬ ከቅጣት ወደ ግብ የመታወሰን ኢላማውን የጠበቀ ኳስ አቤል ማሞ ተቆጣጥሮታል ። በአጋማሹ በቡናማዎቹ በኩል የተደረገው የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 57ኛ ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን ዊልያም ሰለሞን ላን በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ታፈሰ ሰለሞን መቶት በግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ተመልሷል ።
በመስመሮች በኩል ዕድሎችን ለመፍጠር በመጣር ላይ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች 64ኛ ደቂቃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በሳሙኤል ተስፋዬ አማካኝነት ወደ ግብ ክልል መሬት ለመሬት ያሻገሩት ኳስ በፍፁም ጥላሁን ተጨርፎ ወደ ውጫ ወጥቷል ።
ቀስ በቀስ እየቀዘቀዘ የመጣው ጨዋታ ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር በአዲስ አበበሠ ከተማም ሆነ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በእንቅስቃሴም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ቀድሞ ከነበረው በተወሰነ መልኩ ቀንሶ ታይቷል ። ነገር ግን የጨዋታው መገባደጃ ጊዜያት ላይ ከሁለቱም በኩል አንድ አንድ ለግብ የቀረቡ የግብ ዕድሎች ተፈጥረው ነበር ።
86ኛ ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ግብ ጠንከር አድርጎ መቶት በአቤል ማሞ የተመለሰ ሲሆን የተመለሰውንም ኳስ ሪችሞንድ ኦዶንጎ በግነባር ወደ ግብ በድጋሚ ቢልከውም የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች አውጥተውታል ። በቡናማዎቹ በኩል ደግሞ የአስራት ቱንጆ እና አቡበከር ናስር ቅብብሎ ወደ ወደ ግብ ቀርቦ አስራት ወደ ግብ የቀነሰውን ኳስ አቡበከር ናስር ሳይደርስበት ቀርቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 18 በማድረስ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በ11 ነጥብ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቆየት ተገዷል ።
በ13ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ ሰበታ ከተማን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አርባምንጭ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።