በሊጉ የስምንተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 አሸንፏል ።
ድሬዳዋ ከተማዎች በሰባተኛው ሳምንት ከመቻል አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ ያደረጉ ሲሆን ብሩክ ቃልቦሬን በአቤል አሰበ ምትክ አሰልፈዋል ። በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሳምንቱ በኢትዮጵያ መድኅን በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ በአላዛር ሽመልስ እና ኢብራሂም ከድር ምትክ ማታይ ሉል እና ልደቱ ለማ ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጨዋታውኝ ለመቆጣጠር ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በዚህም የተሻሉ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በዘጠነኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል ። የድሬዳዋ ከተማን የኳስ ምስረታ በማቋረጥ ያገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም ናትናኤል ሰለሞን ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ድሬዳዋ ከተማዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ተጭነው ለመጫወት ጥረቶችን አድርገዋል ። የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ግን የድሬዳዋ ከተማን የማጥቃት ሂደት የተሳለጠ እንዲሆን የፈቀዱ አልነበሩም ።
ይህንን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት በመጣልም ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል ።
ከግብ ሙከራ የራቀው የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያው ላይ ምናልባትም የኢትዮ ኤሌክትሪክን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርግ የሚችል አጋጣሚን አስመልክቶናል ። አጥቂው ልደቱ ለማ የድሬዳዋ ከተማ ተከላካይ የሆነውይ የአሳንቴ ጎድፍሬድን ስህትት ተጠቅሞ ወደ ግብ የመታው ኳስ በዳንኤል ተሾመ ግብ ከመሆን ድኗል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጫና ፈጥረው በመጫወት ወደ ድሬዳዋ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ችለው ነበር ።
በዚህም በ49ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ ወለጬ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ገብቶ ወደ ግብ ያደረገው ጠንካራ የግብ ሙከራ በዳንኤል ተሾመ ተመልሷል ።
ድሬዳዋ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለማድረስ ጥረቶችን በማድረግ የጀመሩት የጨዋታ ሂደት ቀስ በቀስ በማሻሻል ከተጋጣሚያቸው የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል ።
ነገር ግን የግብ ዕድል ለመፍጠር እስከ 66ኛው ደቂቄ ለመጠበቅ ተገደው ነበር ። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ መሀመድ አብዱለጢፍ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ አሳንቴ ጎድፍሬድ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
ድሬዳዋ ከተማዎች በአመዛኙ በግራ መስመር በኩል ጫና ሲፈጥሩ ቆይተው በ74ኛው ደቂቃ ከዚሁ አቅጣጫ በተነሳ ኳስ የኢትዮ ኤሌክትሪክን መረብ ማግኘት ችለዋል ። ሙኸዲን ሙሳ በግራ መስመር ይዞ ወደ ሳጥን የገባውን ኳስ አሻምቶ ቢንያም ጌታቸው በግንባር በመግጨት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
ከአቻነቱ ግብ በኋላ የተነቃቁት ድሬዳዋ ከተማዎች በ88ኛው ደቂቃ ላይ ከመመራት ወደ መምራት የተሸጋገሩበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ቻርለስ ሙሴጌ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች መዘናጋትን ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት በዘሪሁን መረብ ላይ አሳርፏል ።
በመጨረሻም ድሬዳዋ ከተማ በ2 ለ 1 ድል ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል ።