በሀያ አንደኛዉ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታቸዉን በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል።
በአምስት ነጥቦች ተበላልጠዉ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዉ ጨዋታቸዉን የጀመሩት ሁለቱ ክለቦች በጨዋታዉ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ተመጣጣኝ የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴን ቢያስመለክቱም በሙከራ ረገድ ግን የጣና ሞገዶቹ የተሻሉ ነበሩ ሲሆን ገና በጨዋታዉ መጀመሪያ 5ተኛዉ ደቂቃ ላይ ባህርዳር ከተማ ግብ አስቆጥሯል ፤ በዚህም ፋአድ ፈረጃ ያሻማዉን የቅጣት ምት ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በጭንቅላቱ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
በ22ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ባህርዳሮች በመከላከል ዞናቸዉ ላይ ያላፀዱትን ኳስ ባሲሩ ዑመር በቀጥታ ወደ ሳጥን አሻምቶ የነበረ ሲሆን ጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረዉ ሳይመን ፒተር በጭንቅላንቱ ወደ ጎልነት በመቀየርም ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ የማጥቃት ሀይላቸዉን አጠናክረዉ የቀጠሉት ባህርዳሮች በድጋሚ ጥሩ የግብ ዕድል ማግኘት ችለዉ ነበር በዚህም አለልኝ አዘነ ከቀኝ በኩል በቀጥታ ወደ ግብ ኳሷን ሲሞክር አቡበከር ኑሪ ሲመልስ በድጋሚ በአቅራቢያዉ የነበረዉ ሀብታሙ ሞክሮ አሁንም የገብ ዘቡ ኳሷን ተቆጣጥሯታል። በድጋሚ በ38ተኛዉ ደቂቃ ላይ ያብስራ ከቀኝ በኩል በቀጥታ ያገኛትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም በምሽቱ ድንቅ የነበረዉ አቡበከር ኑሪ ኳሷን አምክኗታል።
ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን ተሻሽለዉ ወደ ሜዳ የተመለሱት መድኖች አጋማሹ ከተጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ በዚህም ኪቲካ ጀማ ከግራ የመድን ማጥቃት ለሳይመን ፒተር ያቀበለዉን ኳስ የመስመር አጥቂዉ በቀጥታ ለሀቢብ ከማል አቀብሎት ሀቢብ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ የአቻነት ጎል ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የመድኞችን የግብ ክልል ቢያንኳኩም የመድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ ግን ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያከሽፍ ተስተውሏል።
ሳይመን ፒተር በተከላካዮች መሐል ያቀበለዉን ኳስ ኪቲካ ጀማ ወደ ፊት ገፍቶ ግብ ጠባቂዉን አታሎ ካለፈ በኋላ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወጥታለች። ከዚች ሙከራ በደቂቃዎች ልዩነት ባህርዳር ከተማዎች በ83ተኛዉ ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ በዚህም ከማዕዘን ምት የተሻማዉን ኳስ አደም አባስ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
በሁለቱም አጋማሾች ሁለት አይነት የጨዋታ እንቅስቃሴ ባስመለከተን የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ዉጤቱን ተከትሎም ባህርዳር ከተማ በ43 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ በ38 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።