በሀያ አንደኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ቀን ጨዋታ ቀትር ዘጠኝ ሰዓት ላይ በተደረገ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን 4ለ1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት እና የተጋጣሚ ቡድን የመሐል ክፍል ላይ ጫናዎችን በማሳደር በተለይ የመሐል ሜዳዉ ላይ የበላይ በመሆን ለመጫወት በሚሞክረዉ እና በተቃራኒው በፈጣን የመስመር ላይ የማጥቃት ሽግግሮች እና በመልሶ ማጥቃት ከሚገኙ እንቅስቃሴዎች ግብ ለማስቆጠር የሚሞክረዉ ድሬዳዋ ከተማ ባደረጉት የዕለቱ ጨዋታ የመጀመሪያ ሀያ ያህል ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴ ያስመለከቱን ሲሆን በሙከራ ረገድ ግን ቀዳሚ መሆን የቻሉት ብርቱካናማዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ናቸዉ።
- ማሰታውቂያ -
በዚህም በመጀመሪያዉ አጋማሽ እንየዉ ካሳሁን ከቀኝ የድሬዳዋ ማጥቃት በኩል አሻምቶት የነበረዉን ኳስ ሙህዲን ሙሳ ወደ ግብነት ለመቀየር ከጫፍ ደርሶ ሳይሳካለት ቀርቷል። በተጨማሪም ከደቂቃዎች በኋላ አማካዩ ኤሌያስ አህመድ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ወደ ግብ የሞከረዉ ኳስ ወደ ዉጭ ወጣበት እንጅ በብርቱካናማዎቹ በኩል በአጋማሹ የተደረገ ድንቅ ሙከራ ነበር ማለት ይቻላል።
በተመሳሳይ በጨዋታ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩት ቡናማዎቹ ደግሞ በመስፍን ታፈሰ ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እንዲሁም አጥቂዉ ብሩክ በየነ የግቡ አግዳሚ የመለሰበትን አጋጣሚ ጨምሮ ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም በመጀመሪያው አጋማሽ ግን ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ከዕረፍት መልስ በደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ግብ በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከዚች ግብ መቆጠር በኋላም ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቀጠሉት ቡናማዎቹ በ63ተኛዉ ደቀቃ ላይ መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ከፍ ያደረጉበትን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ድሬደዋ ከተማዎች ሳጥን ዉስጥ ጥፋት መስራታቸዉን ተከትሎ የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ሮቤል ተ/ሚካኤል ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ የቀጠሉት ቡናዎች በ73ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሶስተኛ ግብ አግኝተዋል። በዚህም መስፍን ታፈሰ ወደ ሳጥን ያሻማዉን ኳስ አንተነህ ተፈራ ወደ ጎልነት መቀየር ችሏል። በሁለተኛዉ አጋማሽ ብልጫ የተወሰደባቸዉ ድሬዳዋ ከተማዎች በ79ነኛዉ ደቂቃ ላይ አቤል ከበደ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻማውን ኳስ ተከላካዮች ሲጨርፉት ያገኘዉ ያሲን ጀማል ወደ ግብነት በመቀየር ድሬዎችን ወደ ጨዋታው መልሷል።
ጨዋታዉ በዚህ ዉጤት ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ ቡናማዎቹ በአምበሉ አማኑኤል አማካኝነት ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዉ ጨዋታው በቡናማዎቹ 4ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ዉጤቱን ተከትሎም ቡናማዎቹ በ30 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በተቃራኒው ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በ27 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።