ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 21ኛ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች አምስት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሶስት ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 20 ጎሎች ተቆጥረዋል። የጎሎቹ አገባብም 18 በጨዋታ አንድ በፍፁም ቅጣት ምት እና አንድ በራስ ላይ የተቆጠሩ ናቸው። በሳምንቱ 30 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ የተመዘገበ ቀይ ካርድ የለም።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ አርብ ሚያዝያ 20 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋች እና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች በተጫዋቾች ያሬድ ዳዊት(ወላይታ ድቻ) እና አለልኝ አዘነ(ባህርዳር ከተማ) የተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ሲወሰን በአሰልጣኞች ፀጋዬ ኪዳነ ማሪያም(ወላይታ ድቻ) እና ስምኦን አባይ(ኢትዮ ኤሌትሪክ) የተለያዩ 3 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ የተመለከቱ ሲሆን የቡድን አመራሮቹ ለፈፀሙት ጥፋት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱ ና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ወስኗል ።