ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ዕለት ሰርቪያዊውን አሰልጣኝ ሰርዲ ሚሊቲን ሚቾን ለሦስተኛ ጊዜ በሦስት አመት እየታየ በሚጨመር ተጨማሪ የሁለት አመት ኮንትራት በዋና አሰልጣኝነት ሲሾም ኢንስትራክተር ስዩም ከበደን ደግሞ በቴክኒክ ዳይሬክተርነት እንዲሁም ቢሾፍቱ የሚገኘውን የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚን በስራ አስኪያጅነት እንዲመሩ በሁለት አመት ውል በይፋ ሾሟል።


በቀጣዩ ሳምንት ወደ ዝግጅት የሚገባው ክለቡ ከቤልጅየም ረዳት አሰልጣኝ የፒኤስጂ ደግሞ የአካል ብቃት አሰልጣኝ እንዲሁም ደግሞ የቴራፒ ባለሙያን በተመሳሳይ ከሀገር ውጪ እንደሚያስመጣ ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል በነበረው ስነ ስርአት ላይ ያሳወቀ ሲሆን በዝግጅት ወቅት ከምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይም እንደሚሳተፍ ታውቋል።
በርካታ የክለቡ የቀድሞው እና አዳዲስ ተጫዋቾች የክለቡ አመራሮች አባላትና ጋዜጠኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሸራተን አዲስ ሆቴል በነበረው የፊርማ ስነስርዓት ተገኝተዋል። ክለቡ በቀጣይ ስለሚሰራቸው ስራዎች ማብራራት እና ገለፃ ከተደረገ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን በተጠናቀቀው አመት በማሰልጠን ስኬታማ ቆይታን ማድረግ የቻሉት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የግማሽ ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
አስተያየት ይስጡ