ሲዳማ ቡና ከፊቱ ለሚጠብቀው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ጀምሯል
የተጠናቀቀውን የ2018 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን መሆን የቻለው ሲዳማ ቡና ከፊቱ ለሚጠብቀው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ መርሀግብር እና ለ2019 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በዛሬው ዕለት ጀምሯል። በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው የሊጉ ሻምፒዮን ማረፊያውን በሀዋሳ እንጆሪ ሆቴል በማድረግ አመሻሹን በደቡብ ኢትዮጵያ ኮሌጅ የልምምድ ሜዳ ላይ ክለቡን ልምምዱን በዛሬው ዕለት ሲጀምር ሀትሪክ ስፖርት በስፍራው በመገኘት መታዘብ ችሏል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ውላቸው የተጠናቀቁ እና በአሰልጣኙ የሚፈለጉ ተጫዋቾች ውላቸውን መራዘም የቻለ ሲሆን ቢኒያም በላይን ከሀዋሳ ከተማ ፣ ኤፍሬም ታምራትን ከአርባምንጭ ከተማ ፣ ውብሸት ክፍሌን ደግሞ ከወላይታ ድቻ ወደ ስብስቡ ያካተተው ክለቡ በቀጣይ ቀናትም ተጨማሪ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በሂደት ላይ መሆኑንም ጭምር አረጋግጠናል።
ሲዳማ ቡና በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከቡሩንዲው ኤግሌ ኖይር እና ከሱዳኑ አልሂላል አሸናፊ ጋር መደልደሉ ይታወሳል
አስተያየት ይስጡ