ለቀጣዩ የ2019 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አመራሮች ሜዳዎችን በየሀገሩ ምልከታን ማድረግ ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የያዝነው የ2018 የውድድር ዘመን ከመቋጨቱ አስቀድሞ የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና የውድድር እና ስነ ስርዓት ሰብሳቢው ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ መሪነት በቀጣዩ አመት ለሚደረገው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለውድድር የሚሆኑ ስታዲየሞችን ለመምረጥ ከአሁኑ በቡድን ተከፋፍለው በየሀገሩ የሚገኙ ስታዲየሞችን ፣ የልምምድ ሜዳዎችን እና ሆቴሎችን ምልከታ ማድረግ ከትላንት በስቲያ አንስቶ እየተመለከቱ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
የቦርድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ከውድድር ከራቀ አራት አመታት ያስቆጠረውን የባህርዳር ስታዲየምን ወደ ውድድር ለመመለስ በዛሬው ዕለት ከከተማው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ማድረግ የቻሉ ሲሆን ግዙፉን ስታዲየም ጨምሮ የልምምድ ሜዳ እና መሠረት ልማቶችን የተመለከቱ ሲሆን በቀጣይም የጎንደር እና ስታዲየም እና በከተማው ያሉ የመጫወቻ እና የመለማመጃ ሜዳዎችን ይመለከታሉ ተብሎ ይጠበቃል። በውድድር እና ስነ ስርዓት ሰብሳቢ በሆኑት ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ በበኩላቸው ትላንት አዲስ አዳጊው ጋሞ ጨንቻ ለመወዳደር ያቀረበውን የአርባምንጭ ስታዲየም የተመለከቱ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ወላይታ ድቻ እና ሀላባ ከተማ ከተማ ለመጫወት የወሰኑትን የሀላባ ስታዲየም መመልከት ችለዋል።
በነገው ዕለት እና በቀጣዮቹ ቀናትም የሀድያ ሆሳዕናውን አብዩ ኤርሳሞ ስታዲየም ፣ የሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ መለማመጃ እና የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሜዳዎችን ፣ የነገሌ አርሲ ፣ የአዳማ ከተማ እንዲሁም በመጨረሻም በአዲስ አበባ ያሉ ስታዲየሞችን በመመልከት የግምገማ ሪፖርቶችን በመሰብሰብ የቀጣዩን አመት ሜዳዎች ይፋ እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን ምቹ የመጫወቻ ሜዳ ፣ በቂ የልምምድ ሜዳዎች እና ቢያንስ ሁለት የኮከብነት ደረጃ ያላቸው አንድ ውድድር አደርጋለሁ የሚል ክለብ ሊኖረው ግድ እንደሚልም መመሪያው ይደነግጋል።
የሊግ አክሲዮን ማህበሩ ለክለቦች መጠይቆችን በማዘጋጀት የበተነ ሲሆን የውድድር ይዘቱ በምን መልኩ ይሁን ባለበት ይቀጥል ወይንስ ከሜዳ እና ከሜዳ ውጪ በሚል ይከወን የሚለውን ጉዳይ በመጠይቅ እየሰበሰበ እንዳለም መረጃዎች ጨምረው አመላክተዋል።
አስተያየት ይስጡ