ከዕረፍት ሊጉ ሲመለስ ለከርሞው ለመሰንበት እየዳዳ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ በመቻል ላይ ወሳኝ ድልን ሲያሳካ 80 ደቂቃዎችን በጎዶሎ የተጫወተው ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስም አሸንፈዋል።

ከዕረፍት እና ከኢትዮጵያ ዋንጫ በ34ኛ ሳምንት በተመለሰው የሊጉ መርሀግብር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ አንድ ጨዋታ መደረግ የቻለ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ለ80 ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች በመጫወት ኢትዮጵያ ቡናን በደጋፊው ፊት 1ለ0 መርታት ችለዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ብሩክ በሰራው ተከታታይ ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ለማጣት የተገደዱት ሀዋሳ ከተማዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ወደ ቡናማዎቹ ሳጥን የተጣለን ኳስ ቢኒያም በላይ አግኝቶ ለማለፍ ጥረት ሲያደርግ ጋናዊው የግብ ዘብ ዳላንድ ኢብራሂም ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ በረከት ሳሙኤል ከመረብ የአሸናፊነት ጎሏን ማስቆጠር ችሏል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ በወራጅ ቀጠናው ላይ የተቀመጠውን ድሬዳዋ ከተማን በሁለቱ ወጣት ተጫዋቾች ጎል 2ለ1 ማሸነፍ ችሏል። በፈጣን ሽግግር ጨዋታውን የጀመሩት ፈረሰኞቹ 25ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ከቀኝ ወደ ውስጥ ቶሎሳ ንጉሴ የላከለትን ወጣቱ ተጫዋች ብሩክ አለማየሁ በቀላሉ መረቡ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን ቀዳሚ ቢያደርግም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ብርቱካናማዎቹ አቻ ሆነዋል።

27ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሜዳው ክፍል በረጅሙ ከቅጣት የተመታትን ኳስ ድልአዲስ ገብሬ ሞክሮ ኬኒያዊው ግብ ጠባቂ ሻኪሎ ፋሩክ ሲመልሰው አስራት ቶንጆ የተመለሰችውን ኳስ በማስቆጠር ጨዋታው 1ለ1 ሆኗል። ጨዋታው ቀጥሎ በተሻለ መነቃቃት የድሬዳዋን ደካማ መከላከል ለማስከፈት ይጥሩ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 35ኛው ደቂቃ ፍፁም ጥላሁን በጥሩ ዕይታ ወደ ውስጥ የሰጠውን ሀብታሙ ጉልላት ወደ መሪነት ያሸጋገረች ጎል ካደረጋት በኋላ ጨዋታው 2ለ1 መጠናቀቅ ችሏል።

ወራጅ እና ለዋንጫ የሚፎካከሩ ሁለት ቡድኖች በአዳማ ያገናኘው የአርባምንጭ ከተማ እና መቻል ጨዋታ በአዞዎቹ ድል መጠናቀቅ ችሏል። ከፍ ባለ ተነሳሽነት ጨዋታውን ለመጀመር ጥረት ያደረጉት አርባምንጮች 32ኛው ደቂቃ ከኤፍሬም ታምራት የደረሰውን ኳስ አሸናፊ ተገኝ ወደ ግብነት ለውጦ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል 47ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተነሳች ኳስን ዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርለስ ሙሴጌ ወደ ግብነት በመለወጥ መቻልን አቻ ያደረገ ቢሆንም 60ኛው ደቂቃ ወጣቱ ቴዎድሮስ በንቲ መረቡ ላይ ያስቀመጣት ኳስ አርባምንጭ ከተማ 2ለ1 ማሸነፍ እንዲችል ሆኗል።
አስተያየት ይስጡ