ቅዱስ ጊዮርጊስ በአራት የቀድሞ ተጫዋቾች ቀርቦበት በነበረው ክስ በፊፋ ጥሎበት የነበረው የተጫዋቾች የዝውውር ዕግድ በጊዜያዊነት ተነስቷል፡፡

ክለቡ የቅጣት መክፈያ ገንዘቡን ከሚድሮክ የበላይ ሀላፊ ከአቶ ጀማል አህመድ በስጦታ ባገኘው ገንዘብ በሁለት ቀናት ውስጥ ለአራቱ ከሳሽ ተጫዋቾች ሙሉ ክፍያን ከቅጣት ጋር ከፍሎ ቢያጠናቅቅም መሀመድ ላሚን ኮኔ ለፊፋ ያስገባው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ትክክል ባለመሆኑ ምክንያት ገንዘቡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተመላሽ ተደርጓል፡፡ ተጫዋቹ እስከ አሁን ባለመላኩ ምክንያትም ዕገዳው ሳይነሳ ለሳምንታት ቆይተዋል፡፡
ክለቡም የተጠየቀውን ሁሉንም ህጋዊ ሁኔታዎች ማሟላቱንና የኮኔ ገንዘብም ያልተከፈለው በተጫዋቹ የራሱ ችግር መሆኑን ገልፆ ለፊፋ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ፊፋ የቅዱስ ጊዮርጊስን ጥያቄ በመቀበል ኮኔ ትክክለኛውን የባንክ ሂሳብ ቁጥሩን እንዲልክና ክለባችንም የኮኔን ክፍያ እስከሚከፍል ድረስ ተጥሎበት የነበረው ዕግድ በጊዜያዊነት እንዲነሳ ወስኗል፡፡ የኮኔ ክፍያ በቀጣይ ጥቂት ቀናት ሲጠናቀቅ ክለቡ በቋሚነት ከዕግድ ነጻ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

የዝውውር ዕገዳው በጊዜያዊነት መነሳቱን ተከትሎ ክለቡ ለውድድሩ የሚሆኑትን የሀገር ውስጥ እና የውጪ ተጨዋቾች ለማስፈረም ወደ ገበያ የሚገባ ይሆናል፡፡
ክለቡ በእነዚህ አራት ተጫዋቾች ቀርቦበት የነበረውን ከፍተኛ ክፍያ በመፈጸም ክለቡን ከእገዳ ነጻ እንዲሆን ያደረጉት የክለቡን ዋነኛ ደጋፊ እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ናቸው ሲል ይፋ ማድረግ ችሏል፡፡
አስተያየት ይስጡ