የመውረድ ስጋት ውሰጥ ያሉት ሁለቱ ክለቦች አመሻሽ 12 ሰዓት ጀምሮ ያደረጉት ጨዋታ ገና ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴዎች የተጀመረ ነበር ። በድሬዳዋ ከተማም ሆነ በሰበታ ከተማ በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎችንም መፍጠር ችለዋል ።
በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 15ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን ሙከራውም ወደ ግብነት መቀየር የቻለ ነበር ። አቤል አሰበ ከሳጥኑ ውጪ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላከው ኳስ በምንተስኖት አሎ መረብ ላይ አርፎ ብርቱካናማዎቹን ቀዳሚ አድርጓል ።
ከግቡ በኋላ ሰበታ ከተማዎች በጨዋታው ላይ ብልጫ ወስደው በመጫወት የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ጥረቶችን አድርገዋል ። በተለይም 17ኛው ደቂቃ ላይ ዴሪክ ንስምባቢ ያገኘውን ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል በፍሬው ጌታሁን ተመልሶበታል ። በ22ኛው ደቂቃ ላይ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ማማዱ ሲዲቤ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሄኖክ አየለ በግንባር መግጨት ቢችልም ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅለት ቀርቷል ።
በቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ሰበታ ከተማዎች በተሻለ ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ይህ ነው ሊባል የሚችል ጠንካራ የግብ ሙከራን ማድረግ ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች የማጥቃት ኃይላቸውን በተጫዋቾች ቅያሪ በማጠናከር የፍሬው ጌታሁንን መረብ ለመድፈር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በሰበታ ከተማ በኩል በተደጋጋሚ የሚነሳው የፊት መስመር ክፍተት በዚህ ጨዋታም ቀጥሎ የታየ ነበር ።የድሬዳዋ ከተማው ተከላካይ ያሲን ጀማል በበሀይሉ ግርማ ለይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል ።
የድሬዳዋ ከተማን በቁጥር መጉደል ለመጠቀም በቁጥር በዛ በለው በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ላይ መገኘት የቻሉት ሰበታ ከተማዎች ኳስ እና መረብን የሚያዋህድላቸው ተጫዋች ለማግኘት ግን አልቻሉም ነበር ።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል በመከላከሉ ተጠምደው በመቆየት በተወሰኑ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ሌላ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ሙከራ በ86ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶላቸዋል ። ሄኖክ አየለ ከግራ የሳጥኑ አቅጣጫ ከመሀመድ አብዱለጢፍ የደረሰውን ኳስ በሰበታ ከተማ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን 2 – 0 እንዲመራ ማድረግ ችሏል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ የ2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
አስተያየት ይስጡ