በ19ኛው ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት በተደረገው የአዳማ ከነማ እና የሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና 2 – 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል ።
አዳማ ከነማዎች በ18ኛው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ ዘካርያስ ከበደ እና ፀጋአብ ዮሴፍን በታደለ መንገሻን እና ዮሴፍ ዮሀንሰን ምትክ ሲያስገቡ በሀድያ ሆሳዕና በኩል በሳምንቱ ከአርባምንጭ ከነማ 4 – 4 በተለያዩበት ጨዋታ በነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ባዬ ገዛኸኝን በቃልአብ ውብሸት ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረ እና በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር ። በአዳማ ከነማ በኩል በውድድር አመቱ ብዙም በመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ ያልተመለከትናቸውን ዘካርያስ ከበደን እና ፀጋአብን ጨዋታውን መጀመር የቻሉበትም ነበር ።
ከፊት መስመር ላይ ዳዌ ሆቴሳን እና አብዲሳ ጀማልን ያሰለፉት አዳማ ከነማዎች የሀድያ ሆሳዕናን የኋላ ክፍል በቀላሉ አልፈው ለመግባት ተቸግረው ነበር ።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል ኡመድ ኡክሪን ኢላማ ያደረጉ ኳሶች በተደጋጋሚ ወደ ፊት መስመር የሚላኩ ሲሆን የመሀል ክፍሉም ለአጥቂው ኳሶችን በማድረስ እና በተጨማሪም የአዳማ ከነማን እንቅስቃሴ በቀላሉ በመግታት ኳሶቹን ወደ ማጥቃቱ ዞን በማድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል ።
በ5ኛው ደቂቃ ላይ ኡመድ ኡክሪ ከኢያሱ ታምሩ የደረሰውን ኳስ በግራ እግሩ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ሲመልስበት በ17ኛው ደቂቃ ላይም በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ አበባየሁ ዮሐንነስ ያቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ልኮት ጀማል በድጋሚ አድኖበታል ።
ምንም እንኳን በሁለቱም በኩል ኳሱን በመቆጣጠር ያን ያህል ብዙም ልዩነት ያልነበረ ቢሆንም ወደ ግብ ክልል በመድረስ ረገድ አዳማ ከነማዎች ከተጋጣሚያቸው አንፃር ደከም ብለው ነበር ። በ19ኛው ደቂቃ ላይ አብዲሳ ጀማል በረጅም የደረሰውን ኳስ ከሀድያ ሆሳዕና ተከላካዮች ጀርባ ሆኖ በማግኘት ወደ ፊት እየገፋ ሄዶ የነበረ ቢሆንም ከኋላው የደረሰው የፍሬዘር ካሳ ጫና ተጨምሮበት ኳሱን ከግቡ አናት በላይ ልኮታል ።
ከውሀ እረፍት መልስ በሰከንዶች ውስጥ የጨዋታው የመጀመሪያ ግብ ተቆጥሯል ። ሄኖክ አርፊጮ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ በግንባር ሲገጨው አዲስ ተስፋዬ እና ጀማል ጣሰው ባለመግባባት የፈጠሩትን ክፍተት ተጠቅሞ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ኡመድ ኡክሪ ግብ አድርጎታል ።
በ34ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ በቀለ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በጀማል የተያዘ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽም በሃድያ ሆሳዕና የ1 – 0 መሪነት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከነማ የተጫዋቾች እና የጨዋታ አሰላለፍ ለውጥ አድርጎ የጀመረ ሲሆን በዚህም ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ሀድያ ሆሳዕና የግብ ክልል መድረስ ችለዋል ።
ምንም እንኳን አዳማ ከነማዎች ተነቃቅተው የተሻለ በመንቀሳቀስ ወደ ፊት መድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ሀድያ ሆሳዕናዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ግባቸው በመድረስ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል ። በ47ኛው ደቂቃ ላይ ጀማል ጣሰው ከግቡ ወጥቶ የሰራውን ሰህተት ተጠቅሞ ግብ ጠባቂው በሌለበት አበባየሁ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ቶማስ ስምረቱ ከግቡ አፋፍ ላይ ሲያወጣው ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ፍቅረየሱስ ተክለብርሀን ከመስመር ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ተስፋዬ አለባቸው አግኝቶ ወደ ግብ ቢሞክረውም ሚሊዮን ሰለሞን በግንባር ገጭቶ አውጥቶበታል ።
በ59ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከነማዎች የአቻነቱን ግብ አግኝተዋል ። ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ጀሚል ያዕቆብ ወደ ግብ ክልል የላከውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ ለመከላከል ሲሞክር ተመቻችቶለት ያገኘው ተቀይሮ የገባው አሜ መሀመድ አክርሮ በመምታት በያሬድ በቀለ መረብ ላይ አሳርፏል ።
በግቡ የተነቃቁት አዳማ ከነማዎች ጫና ፈጥረው ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ሲያደርጉ የነበረው ጥረት በማጥቃቱ ሶስተኛ ክፍል ላይ በነበራቸው ድክመት ሳይሳካ ቀርቷል ።
በ81ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው እና በግቅ ጠባቂው ያሬድ ከተያዘው ኳስ ውጪ ሌላ የግብ ዕድል መፍጠርም አልቻሉም ነበር ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ሊጠናቀቅ ሶስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ የሀድያ ሆሳዕና ቅያሪ ግብ አስገኝቷል ። ተቀይሮ የገባው ራምኬል ሎክ ከኡመድ የተቀበለውን ኳስ ሌላው ተቀይሮ ለገባው ኤፍሬም አቀብሎ መልሶ የደረሰውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቷል ። በመጨረሻም ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታውን 2 – 1 በማሸነፍ የሶስት ነጥቡ ባለቤት ሆኗል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 25 በማድረስ ከ11ኛ ወደ 7ኛ ከፍ ሲል አዳማ ከነማ ደግሞ ወደ 9ኛ ደረጃ ተንሸራቷል ።
የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አዳማ ከነማ በመጪው ሰኞ ቀን 9 ሰዓት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከነማ ጋር ሲጫወት ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ በማግስቱ ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ ሀዋሳ ከነማን ይገጥማል ።
አስተያየት ይስጡ