ከአራት ወራት በፊት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን እና ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ መካከል የተደረገው ስምምነት በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፣ የቡና ባንክ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ብርሀኑ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በተገኙበት በሞናርክ ፓርክ ቪዉ ሆቴል ይፋ ተደርጓል።

በዋናነት የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ላይ ባተኮረው ስምምነት ላይ ከተነሱት አንኳር አንኳር ነጥቦች መካከልም:-
ስምምነቱ ለሶስት አመታት የሚቆይ ሲሆን በየአመቱ የሚታደስ ይሆናል ያሉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የገንዘቡን መጠን ከመግለፅ ቢቆጠቡም ዋልያዎቹን በአንደኛ ደረጃ ስፖንሰር ከሚያደርገው ዋልያ ቢራ ጋር የሚስተካከል የገንዘብ መጠን ቡና ባንክ እንደሚከፍል የተጠቆመ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ብሔራዊ ቡድኑ በሚያሳየው አቋም እንዲሁም ባንኩን promote በሚያደርገው መጠን የገንዘንብ መጠኑም ሆነ ጥቅማጥቅሞቹ ከፍ እያሉ እንደሚሄዱ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዋልያዎቹ የነጥብ ጨዋታ ባሸነፋ ቁጥር ቡና ባንክ 300 ሺ ብር የሚከፍል ይሆናል ያሉት አቶ ኢሳያስ ከባንኩ ጋር ከተፈራረሙ በኋላ ብሔራዊ ቡድኑ አንድ ጨዋታ አሸንፎ ክፍያዉን ባንኩ መፈፀሙንም ገልፀዋል። ከባንኩ ጋር በፈፀሙት ስምምነት እጅግ ደስተኞች እንደሆኑ የተናገሩ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽንም ለመሰል የስፖንሰርሺፕ የስምምነት በሩ ክፍት መሆኑንም አያይዘዉ ጠቁመዋል።
ቡና ባንክ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን ስፖንሰር በማድረጉ በጣም ደስተኞች ነን ያሉት የቡና ባንክ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ብርሀኑ ኢትዮጵያን በሚያስጠሩ እንዲሁም የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ በሚያደርጉ ሁነቶች ላይ መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለፁ ሲሆን ከፌዴሬሽኑ ጋር ስለተፈራረሙት ስምምነትም ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል:-

” ብሔራዊ ቡድኑን መደገፍ ሃላፊነታችን ነዉ ቡና ባንክ እግርኳሱ እንዲያድግ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ፤ ለዚህም ማሳያ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የፈፀምነው ስምምነት አሁን ደግሞ ከአራት ወራት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የተፈራረምነው ስምምነት ማሳያ ነዉ። ”
” የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከባንክ ጋር ተያይዞ የሚያስፈልገውን እንቅስቃሴ በቡና ባንክ የሚያደርግ ይሆናል። የሰራተኞችንም ሆነ የዉጭ ምንዛሬን የመሳሰሉ ከባንክ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች በቡና ባንክ የሚፈፅም ይሆናል። የኛ ዋነኛው ሀሳብ በጋራ ማድግ ነዉ ። ምንም እንኳን ስምምነቱን ከፈፀምን አራት ወራት ቢቆጠሩም በሀገራችን ባለዉ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ይፋ ሳናደርግ ቆይተናል። ”

ከዚህ በተጨማሪም ፌደሬሽኑ በሚኖረው ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ የቡና ባንክ አርማ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን አርማ ጋር አብሮ እንደሚቀመጥ የገለፁት አቶ መላኩ ሀሳባቸውን በዚሁ አገባደዋል።
በመጨረሻም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት እና አቶ መላኩ የአርማ ልዉዉጥ አድርገው ፕሮግራሙ በዚሁ ተጠናቋል።
አስተያየት ይስጡ