በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ከሽንፈት መልስ የተገናኙት መከላከያ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታቸውን አድርገው እስካሁን በውድድር አመቱ 3 አቻ ተለያይቶ 3 የተሸነፈው እና ምንም ማሸነፍ ያልቻለው በሙሉጌታ ምህረት የሚመራው ሀድያ ሆሳዕና በሀብታሙ ታደሰ ሁለት ግቦች መከላከያን አሸንፏል ።
መከላከያ በስድስተኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ 11 የሁለት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ኤርሚያስ ሀይሉ እና ደሳለኝ ደባሽ ጨዋታውን እንዲጀምሩ ሲያደርጉ በሀድያ ሆሳዕና በኩል በአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ የሶስት ተጨዋቾችን ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ተጫዋቾቹም ሄኖክ አርፊጮ ፤ ባዬ ገዛኸኝ እና ኤፍሬም ዘካርያስ ናቸው ።

በጨዋታው ጅማሮ በሁለቱም በኩል በፈጣን እና በትንሽ ንክኪዎች ወደ ተገጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሞከሩበት ነበር ። በተወሰነ መልኩ ብልጫ የነበራቸው ሀድያ ሆሳዕናዎች ከመከላከያ በተሻለ ወደፊት መሄድ ቢችሉም ክሌመንት ቦዬን የፈተነ የግብ ሙከራ ለማድረግ ተስኗቸው ነበር ። በአንፃሩ መከላከያዎች በቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ቢንያም በላይ አልፎ አልፎ በፈጣን እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የጣሩ ሲሆን በሌላ ሏኩል ደግሞ የአየር ላይ ኳሶችን ወደ ግብ በመላክ በፊት አጥቂው ኦኩቱ ኢማኑኤል አማካኝነት ሙከራዎችን አድርገዋል ። በጨዋታው የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የተደረገው በኦኩቱ ኢማኑኤል ሲሆን ተጫዋቸለ 3ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረ ኳስ በጭንቅላት በመግጨት ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ያሬድ ተይዞበታል ። በሀድያ ሆሳዕና በኩልም የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት 17ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ባዬ ገዛኸኝ ወደ ግብ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በክሌመንት ቦዬ ተይዟል ።

22ኛ ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አገኙ ። ኢያሱ ታምሩ በግራ መስመር ወደ ሳጥን ኳሱን እየገፋ ሲመጣ ሊከላከለው የነበረው ገናናው ረጋሳ በጡንቻ መሸማቀቅ ምክንያት ባለበት በመውደቁ ክፍተቱን በመጠቀም ለሀብታሙ ታደሰ አቀብሎት ሀብታሙ ግቡን ማስቆጠር ችሏል ።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ቀድሞ እንደነበረው ቶሎ ቶሎ መቀማማቶች እና መመላለሶች የበዙበት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያስመለከተ ሆኖ ነበር ። የመጀመሪያው አጋማሽ ሌላ ተጨማሪ ግብም ሆነ የግብ ሙከራ ሳይታይበት በሀድያ ሆሳዕና 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽ በአብዛኛው በመከላከያ የበላይነት የታየበት ነበር ። በተለያዩ አጋጣሚዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት መከላከያዎች ጥረቶቻቸው ፍሬ ማፍራት የቻሉ አልነበሩም ። በሀድያ ሆሳዕና በኩልም ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት በተጨማሪ ግብ የታጀበ ሆኖላቸዋል ።

ይህ ነው ሊባል የሚችል የግብ ሙከራ ያላስመለከትን የሁለተኛው አጋማሽ 82ኛ ደቂቃ ላይ ግን በመጀመሪያው ግብ አስቆጣሪ በኩል ግብ አስተናግዷል ። ልክ እንደመጀመሪያው ጎል ሁሉ ለግብ አመቻችቶ ያቀበለው እና ግቡን ያስቆጠረው በሁለተኛው ጎል ላይም ይህንኑ ደግመውታል ። እናሱ ታምሩ በተከላካዮች መሀል ያቀበለውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ ተጠቅሞ ኳስን ከመረብ ማገናኘት ችሏል ።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች መከላከያዎች የፈጠሩት ጫና ቀደም ብሎ ከነበረው የተለየ ሳይሆን የቀጠለ ነበር ። ይባስ ብሎም መደበኛው የጨዋታው ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ዳዊት ማሞን በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶባቸዋል ።

ውጤቱን ተከትሎም አሸናፊው ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 6 በማድረስ ወደ 14ኛ ደረጃ ከፍ ሲል መከላከያ ባለበት 10 ነጥብ እና 7ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ