መነሻ ገጽ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ዘገባ | ወላይታ ድቻ ነጥቡን ዘጠኝ ማድረስ የቻለበት ድል አግኝቷል
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግኢትዮጵያ ቡናወላይታ ድቻዜናዎችየጨዋታ ዘገባ

የጨዋታ ዘገባ | ወላይታ ድቻ ነጥቡን ዘጠኝ ማድረስ የቻለበት ድል አግኝቷል

አጋራ
አጋራ

በሊጉ አራተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ የመጀመሪያ ጨዋታ በወላይታ ድቻ እና በኢትዮጵያ ቡና መካከል ተደርጎ በጦና ንቦቹ የ 3 ለ 1 አሸናፊነት ውጤት ተጠናቋል ።

ከሶስተኛ ሳምንት ጨዋታቸው በሁለቱም በኩል በቋሚ አሰላለፉ ለውጦች የነበሩ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩል ከባለፈው ጨዋታ በቋሚ 11 ከተጠቀሙት አንድ ቅያሪ ብቻ ያደረጉ ሲሆን ቃልኪዳን ዘላለም ወደ አሰላለፉ መግባት የቻለው ተጫዋች ነው በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በቋሚ አሰላለፍ ላይ አራት ቅያሪዎችን ሲያደርጉ ወንድሜነህ ደረጄ ፤ ስዩም ተስፋዬ ፤ ዊልያም ሰለሞን እና አላዛር ሽመልስ በቋሚ 11 ውስጥ ገብተው ጨዋታውን መጀመር ችለዋል ።

ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች የጥንቃቄ ጨዋታን በመምረጥ ከኋላ መስመር በረጅሙ ወደ አጥቂ መስመር በሚላኩ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡና ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ቢያደርጉም የወላይታ ድቻን የተከላካይ መስመር ለማለፍ በእጅጉ ተቸግረው ነበር ።

ጨዋታው በተጀመረ 11ኛ ደቂቃ ላይ የጦና ንቦቹ ያገኙትን የማዕዘን ምት በረጅሙ ምንይሉ ወንድሙ ሲያሻማው ተከላካዩ አንተነህ ጉግሳ በግንባር በመግጨት ከግቡ ቅርብ ለነበረው ቃልኪዳን ዘላለም አቀብሎት ነፃ የነበረው ቃልኪዳንም ኳሱን መቶ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ ። ከግቧ መቆጠር በኋላ በወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ላይ መነቃቃት ቢታይም ብዙም ሳይቆይ ቡናማዎቹ ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል ።

በመጀመሪያው አጋማሽ በቡናማዎቹ በኩል ሊጠቀስ የሚችለው ሙከራ የተደረገው በ23ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ። እንዳለ ደባልቄ በአየር ላይ ያሻገረለትን ኳስ አቡበከር ናስር በጭንቅላቱ ገጭቶ ወደ ግብ ሲልከው ፅዮን መርዕድ ጨርፎት የግቡን አግዳሚ መቶ ግብ ሳይሆን ቀርቷል ።

በወላይታ ድቻ በኩል አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ በረጅም በተደጋጋሚ ኳሶች ሲላኩለት የነበረ ቢሆንም በአጨራረስ ድክመት ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል ። 21ኛ ደቂቃ ላይ ስንታየሁ በረጅም የደረሰውን ኳስ ተከላካዩን ወንድሜነህ ደረጄን አልፎ በመሄድ ለማስቆጠር ቢሞክርም በአበበ ጥላሁን ተመልሶ የወጣበት ሲሆን በተመሳሳይ 28ኛ ደቂቃ ላይ የተሻገረለትን ኳስ ጠንከር አድርጎ ባለመምታቱ አቤል ማሞ በቀላሉ ሊይዘው ችሏል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በዚሁ በወላይታ ድቻ የ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።

የሁለተኛው አጋማሽ በፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ የተጀመረ እና በስድስት ደቂቃዎች ውስጥም ሁለት ግቦች የተቆጠሩበት ነበር ።

አጋማሹ ከተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ የጦና ንቦቹ ከቀኝ መስመር ያገኙትን የቅጣት ምት ያሬድ ዳዊት ወደ ግብ ሲያሻግረው የደረሰው ምንይሉ ወንድሙ እግር ስር ነበር ምንይሉም በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ስንታየሁ መንግስቱ አቀብሎት ስንታየሁ በግራ እግሩ መቶ የወላይታ ድቻን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አደረገ ።

ግቧ ከተቆጠረች ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ቡናማዎቹ ወደ ጨዋታው ሊመለሩ የሚችሉበትን ግብ አስቆጠሩ ። አቡበከር ናስር ከግራ መስመር ላይ ተከላካዮች በመሸወድ ለታፈሰ ሰለሞን ያደረሰውን ኳስ ታፈሰ ተረጋግቶ ወደ ግብ በመምታት የጨዋታው ውጤት 2 ለ 1 እንዲሆን አስቻለ ።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በተደጋጋሚ የወላይታ ድቻን የግብ ክልል በመድረስ ጫናዎችን ለመፍጠር የሞከሩ ሲሆን የጦና ንቦቹን የኋላ መስመር ለማስከፈት ለረጅም ደቂቃዎች ተቸግረዋል ። ወላይታ ድቻዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው በመመጫወት እና አልፎ አለፎ በሚፈጠሩ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን አድርገዋል ። በዚህም 66ኛ ደቂቃ ላይ በፈጣን እንቅስቃሴ የሄደውን ኳስ ተጠቅሞ ስንታየሁ መንግስቱ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ለራሱ ሁለተኛውን ለክለቡ ደግሞ ሶስተኛውን ግብ አስቆጠረ ። ግቡ የተቆጠረበት መንገድ የመጫወቻ ሜዳው ተፅዕኖ በግልፅ የታየበት ነበር ።

ከአንድ ደቂቃ በኋላ ዊልያም ሰለሞን ከግራ መስመር በመነሳት ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ ተመልሶበታል ።

71ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ታፈሰ ሰለሞን ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ አቡበከር ናስር በግንባር ወደግብ ቢልከውም ፅዮን መርዕድ መልሶታል ።

የጨዋታው መደበኛ ጊዜ ሊጠናቀቅ አምስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት የወላይታ ድቻው የግብ ዘብ ፅዮን መርዕድ በእግሩ ኳስ ይዞ አቡበከር ናስርን ለማለፍ ሞክሮ የተቀማ ቢሆንም ኳሱ ከአቡበከር የደረሰው የአብቃል ፈረጃ ሳያስቆጥረው ቀርቷል ።

90+3 ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ቢንያም ፍቅሬ ከግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ጋር ፊትለፊት ቢገናኝም በውሳኔ ችግር ምክንያት ኳሱ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ የገባው ሮቤል ተክለሚካኤል ከሳጥን ውጪ ጠንካራ ምት በመምታት አስደናቂ ሙከራ ቢያደርግም ፅዮን መርዕድ መልሶ የማዕዘን ምት አድርጎታል ። የማዕዘን ምቱን ቡማናዎቹ እዛው ሲጀምሩት የመሀል ዳኛው የጨዋታውን መጠናቀቅ በፊሽካቸው አበሰሩ ።

በዚህም ወላይታ ድቻ ነጥቡን ወደ ዘጠኝ በማሳደግ ከመሪው ፋሲል ከተማ በግብ ክፍያ ብቻ በማነስ የሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡና በሁለት ነጥብ አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...