በ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ምንም ግብ ሳያስተናግድ ተጠናቋል ።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ የጀመረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሰበታ ከተማ ጨዋታ ከጅማሬው ፈጣን ጨዋታ ያስመለከተ ነበር ። በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተለይም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል ። በጨዋታው በርካታ ጥፋቶች የነበሩ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በነዚህ ጥፋቶች የሚገኙ የቆሙ ኳሶችን በተገቢው ሁኔታ ሊጠቀሙባቸው አልቻሉም ።

በሰበታ ከተማ በኩል አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ለመሄድ ቢሞክሩም የተሳኩ ግን አልነበሩም ። በሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ከፍተኛ ብልጫ የነበራቸው ፈረሰኞቹ የሰበታ ተከላካይ መስመር ማለፍ ግን በዕጅጉ ከብዷቸው ነበር በ57ኛ ደቂቃ ላይ ሀይደር ሸረፋ በጥሩ ቅብብል ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ገብቶ ከሞከረው እና ኢላማውን ከሳተው ኳስ ውጪ ለግብ የቀረበ የግብ ሙከራ አላደረጉም ።

በማጥቃት መስመሩ ላይ ያደረጓቸው ቅያሪዎች ይበልጥ ጫና ከመፍጠር ውጪ ጎል ሊያስገኝላቸው አልቻለም ። ሰበታ ከተማዎች በመከላከሉ ረገድ ያሰቡትን ያሳኩ ቢመስልም ወደ ማጥቃቱ ሲሸጋገሩ ግን ኳሱን ብዙም በእግራቸው ስር ሳይቆይ ይቀሙ ነበር ።

88ኛ ደቂቃ ላይ አንተነህ ተስፋዬ በሀይደር ሸረፋ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። ይህም በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች የታየ 4ኛው የቀይ ካርድ ሆኗል ።
አስተያየት ይስጡ