መልቲቾይስ አፍሪካ ሱፐርስፖርት እና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማህበር ካሳለፍነው አመት የውድድር ዘመን ጀምሮ በጋራ በመስራት የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ በዲኤስቲቪ የቀጥታ ሽፋን እንዲያገኝ ማድረግ ችለዋል ።
ከቀጥታ ስርጭቱ በተጨማሪ በነዚህ አካላት መካከል ባለው ስምምነት መሰረት ሱፐር ስፖርት ለእግርኳሱ የሚረዱ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል ።

ከዚህ ቀደም ነሐሴ 2013 ላይ ለክለብ ፕሬዝዳንቶችና ዋና ስራ አስኪያጆች በብራንዲንግ ፤ በማርኬቲንግ መርሆዎች ፤ በኮንትራት ስምምነቶች አዘገጃጀትና ምንነት እንዲሁም በስፖንሰርሺፕ ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና በሀያት ሪጄንሲ ሆቴል መሰጠቱ ይታወሳል ።

አሁን ደግሞ በሊጉ ተሳታፊ ለሆኑ የክለብ ዋና አሰልጣኞች እና ምክትል አሰልጣኞች በሁለት ዙር ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል ። ለዋና አሰልጣኞች ከመስከረም 24 እስከ 29 እንዲሁም ለምክትል አሰልጣኞች ከጥቅምት 2 እስከ 7 ድረስ የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠና ተዘጋጅቶ በመሰጠት ላይ ይገኛል ። በዛሬው ዕለትም በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ የመክፈቻ ፕሮግራም ተካሂዷል ።

የንድፈ ሀሳብ ስልጠናው በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል የተከናወነ ሲሆን የተግባር ስልጠናው ደግሞ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚከናወን ይሆናል ። ስልጠናው በሱፐር ስፖርት ከፍተኛ አሰልጣኞች እና ከ1.2 ሚሊየን በላይ አባላት ካሉት ከሆላንዱ ኬኤንቪቢ ( KNVB ) የስፖርት ማህበር በመጡ አሰልጣኞች የሚሰጥ ነው ።
አስተያየት ይስጡ