በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ዘንድሮ ለኢትዮጵያ ቡና በኮሪደር ስፍራው ላይ በመጫወት ጥሩ ብቃታቸውን ካሳዩ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው፤ አስራት ቶንጆ ይባላል፤ ይህ ተጨዋች በወለቴ አካባቢ ተወልዶ ካደገ በኋላ እግር ኳስን ለሰበታ ከተማ፣ ለጅማ ከተማ /አሁን ስሙ ተቀይሮ ጅማ አባጅፋር ተብሏል/ ለእነዚህ ቡድኖች በጥሩ መልኩ ተጫውቶ አሳልፏል፤ አስራት በተፈጥሮው የአማካይ ስፍራው ላይ በመጫወት እውቅናን ቢያገኝም በኮሪደር /የመስመር ተጨዋችነት/ ላይም በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናን ማሊያ ካጠለቀ በኋላ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እያመጣ ባለው ለውጥ የአሁን ሰዓት ላይ ጎልቶ በመውጣት እስከ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ በመመረጥ ሀገሩን ጭምር እያገለገለ ይገኛል፡፡
ለኢትዮጵያ ቡና በመጫወት በዘንድሮ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ክለቡ በያዘው አጨዋወት ነጥሮ ከወጡት ተጨዋቾች መካከል ስሙ የሚጠራው አስራት ቶንጆ ዘንድሮ በቡድኑ ውስጥ የነበረውን የውል ጊዜ ጨርሶ የበርካታ ትላልቅ ክለቦችን ትኩረት ቢስብም፤ የተጫወትልን ጥሪ ቢያቀርቡለትም እሱ ግን ቅድሚያን ለነበረበትና ከፍተኛ እውቅናን ላተረፈበት ኢትዮጵያ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ፊርማውን በማኖር ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት የክለቡ ንብረት መሆኑን ሊያረጋግጥ ችሏል፡፡
ከኢትዮጵያ ቡናውና ከዋልያዎቹ ስኬታማ ተጨዋች አስራት ቶንጆ ጋር የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ተጨዋቹ ፊርማውን ካኖረ በኋላ በምን መልኩ ውሉን ሊያራዝም እንደቻለ እንደዚሁም ደግሞ ከክለቡና ከራሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቆይታን አድርጎ የሚከተለው ምላሽ ተሰጥቶታል፤ ተከታተሉት፡፡
ሀትሪክ፡- ቃለ-ምልልሳችንን ከዚህ እንጀምር በእግር ኳስ ተጨዋችነትህ ነው ብዙዎች የሚያውቁህ፤ ምንአልባት ዛሬ ላይ በዚህ ሙያ ላይ ባትገኝ ኖሮ በምን ላይ ትሰማራ ነበር?
አስራት፡- /በጣም ከባድ ጥያቄ ነው/፤ የሰው ልጅ የሚገጥመው ነገር ስለማይታወቅና ባላሰብከው መንገድ ላይ ልትገኝ ስለምትችልም ለአንድም ቀን ቢሆን በዚህ ጉዳይ ላይ አስቤበት አላውቅም፤ እኔ እግር ኳስና እግር ኳስን እያልኩ ነው የመጣሁት፤ በዛም ተሳካልኝ፤ በኳሱ ባልቀጥል ኖሮ ምንአልባት ነው የምለው የቴክኒክ ሙያን በጄኔራል ሜካኒክነት ደረጃ እማር ነበርና ያን ነው ላስቀጥል እችል የነበረው፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ጨምሮ በእግር ኳስ ተጨዋችነት በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ለማሳለፍ ቻልክ፤ ለአንተ ምርጡ ጊዜ የቱ ነው፤ በኳስ ህይወትህ ደስተኛስ ነህ?
አስራት፡- በእርግጥ በሰበታ ከተማ ኳስን መጫወት እንደጀመርኩና ኢትዮጵያ ቡና ሳለውም ከጉዳት አንፃር አስቸጋሪ ጊዜያቶችን ያሳለፍኩባቸው ወቅቶች ቢኖሩም ፈጣሪ ይመስገን ኳስን ደስተኛ ሆኜ ነው እየተጫወትኩኝ የምገኘው፤ በኳስ ተጨዋችነቴ ለእኔ ምርጥ ጊዜ የምለው በሰበታም በጅማም የነበሩትን ጊዜያቶች ጨምሮ ቢሆንም ከሁሉም ላቅ ያለውና በሰዎች እይታና አመለካከት ድረስ የተሳካን ጊዜ ያሳለፍኩበት ግን በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ያለኝን ቆይታ ነው፤ በተለይ ዘንድሮ ለእኔም ለክለቤም ጥሩ የውድድር ዓመትን ነው ልናሳልፍበት የቻልነው፤ ወደ እኔ ስመጣ ለክለቡ በደረጃው ሰንጠረዥ የሁለተኝነትን ውጤት እንዲያስመዘግብና ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ እንዲያልፍም ከቡድን አጋር ጓደኞቼ ጋር ያበረከትኩት አስተዋፅኦ አለና በዛ ውስጥ በማለፌ ደስ ብሎኛል፤ ሌላው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የተመረጥኩትና በቋሚ ተሰላፊነትም ልጫወት የቻልኩት በዚህ ቡድን ውስጥ በነበረኝ ጉልህ ድርሻም ስለነበር በቡና የነበረኝ የጨዋታ ጊዜ ከሁሉ በበለጠ ምርጡ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- አስራት ቶንጆን የኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት በጣም አጉሉቶት አውጥቶታል፤ ይሄ አባባል ያስማማሃል…..?
አስራት፡- አዎን፤ የምቀበለውም ነው፤ የቡና አጨዋወት ኳስን እንደ ቡድን በመጫወት መሰረት ያደረገ ነው፤ በዛ ላይ ደግሞ በሁሉም መልኩ ማለትም በስልጠናውም ሆነ በስብህናው ጥሩ አሰልጣኝም ሊያጋጥመኝ ችሏልና በእሱ የታክቲክ ስራ ውስጥ የሚሰጠኝን ስልጠና በአግባቡ በሜዳ ላይ እተገብራለውና ያ እንቅስቃሴዬ ከራሴ ብርቱ ጥረት ጋር ተዳምሮ ጎልቼ እንድወጣበት አድርጎኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ቆይታህ በአንተ እና በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወይንም ደግሞ በሌሎች ተጨዋቾችና በእሱ ስር ያለው የስራ ግንኙነትና ትስስር ምን ይመስላል?
አስራት፡- የእውነት ለመናገር እኔም ሆንኩ በቡድኑ ውስጥ ያለነው ተጨዋቾች ከስራ ውጪ ከእሱ ጋር የተለየ የሚባል ግንኙነት የለንም፤ ያለን ግንኙነት ሁሌም በልምምድ ሜዳ ላይም ሆነ በጨዋታ ወቅት የእሱን የአጨዋወት ፍልስፍና ለመረዳት በመሞከሩ ላይ ትኩረት አድርገን ጥሩ ለመንቀሳቀስ ነው የምንሞክረው፤ በዛ ላይ ለተጨዋቾች ነፃነትን የሚሰጥበትና ኃላፊነትንም የሚወስድበትም መንገድ በሁሉም ተጨዋቾች ዘንድ ተወዶለታል፤ ባመነበትም መንገድ ነው የሚጓዘውና ካሳዬ አራጌ ምርጥ እና ጥሩ የሆነ አሰልጣኝ መሆኑን ልመሰክርለት ነው የምወደው፡፡
ሀትሪክ፡- አስራት ቶንጆ ብዙ አያወራም ቁጥብ ነው ይባላል፤ እንደዛ ነህ?
አስራት፡- ቁጥብም ዝምተኛም አይደለውም፤ ማውራት ባሉብኝ ነገሮች ላይ ከምግባባቸው ጓደኞቼ ጋር እነጋገራለው፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና በሜዳ ላይ የምትሰጠውን ጥሩ ግልጋሎት አስመልክተው ደጋፊዎቻችሁ ዝምተኛው ገዳይ ስለሚሉህ ይሆን ብዙዎች “ቁጥብ” ነህ የሚሉህ?
አስራት፡- ሊሆን ይችላል፤ እኔ ግን ማውራት ባሉብኝ ነገሮች ላይ የማወራ ተጨዋች ስለሆንኩኝ ከላይ እንደገለፅኩትም ዝምተኛ አይደለውም፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና የነበረህን የውል ጊዜ መጠናቀቅ አስመልክቶ ወደተለያዩ ትላልቅ ክለቦች ልታመራ እንደምትችል ሰምተን ነበር፤ አንተ ግን ወደየትኞቹም ክለቦች ጋር ሳትሄድ ለቡና ለሶስት ዓመታት ለመጫወት ፊርማህን አኖርክ፤ እስኪ በጉዳዩ ዙሪያ አውራን? ወደየትኞቹ ክለቦችስ ነበር ልታመራ የነበርከው ?
አስራት፡- በኢትዮጵያ ቡና በነበረኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፤ ባለኝ ችሎታም ለክለቤ አቅሜ የሚችለውን ግልጋሎት በመስጠት ጭምርም ጥሩ ጊዜን ለማሳለፍ ችያለው፤ ያም ሆኖ ግን የውል ጊዜ በተጠናቀቀበት የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ ከክለቡ ጋር የውል ጊዜህን አራዝመህ ትቀጥላለህ? አትቀጥልም በሚለው የድርድር ወቅት ላይ በርካታ ትላልቅ ክለቦች የእኔን ከቡና ጋር ያለኝን የኮንትራት ጊዜ መጠናቀቅን ያውቁ ስለነበር ሊወስዱኝ በሚያናግሩኝ ሰዓት “እኔ ቅድሚያ የምሰጠው ለኢትዮጵያ ቡና ውሌን አድሼ ለመጫወት ነው፤ ከዚህ ቡድን መልቀቅም አልፈልግም፤ የማልስማማ ከሆነ ብቻ ወደ እናንተ ጋር እመጣለው” አልኳቸውና በዚህ ዙሪያ ነበር ከፈለጉኝ ቡድኖች ጋር ስነጋገር የነበረው፤ ከቡናም ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በምናወራ ሰዓት መጀመሪያ ላይ አልተስማማንም ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ተስማማንና ለክለቡ ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ለመጫወት ፈረምኩኝ፤ በኢትዮጵያ ቡና ቆይታዬም ውሌን ከጨረስኩ በኋላ እኔን ሊወስዱኝ የፈለጉት ክለቦች ፋሲል ከነማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ባህርዳር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማን የመሳሰሉት ቡድኖች ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ሲባልስ የነበረው?
አስራት፡- ማንም አልደወለልኝም፤ በወሬ ደረጃ ከመስማት ውጪ የማውቀው ነገር የለም፡፡
ሀትሪክ፡- አስራት ቶንጆ ለኢትዮጵያ ቡና በመጨረሻ ውሉን ሊያራዝም የቻለው በተሰጠው የፊርማ ክፍያ ላይ የክለቡ ባለሀብት ደጋፊዎችም እገዛ ተጨምሮበት ነው የሚል ነገርንም እየሰማን ይገኛል፤ ይሄን ከአንተ አንደበት እስኪ እንስማው?
አስራት፡- በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እኔ ምንም ነገርን አላውቅም፤ ከቡና ጋር መጀመሪያ ላይ አለመስማማት ነበር፤ ከዛ በኋላ ግን የደጋፊ ማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ክፍሌ አማረና ሌላኛው አመራር ክፍሌ ወልዴ ባልተስማማሁበት ጉዳይ ዙሪያ ደውለው ሲያናግሩኝ ልንግባባ ቻልንና ለቡድኑ ልፈርም ቻልኩ፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማዎች ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ዘንድሮ አነሱት፤ አንተ የቡድኑ ተጨዋች ባትሆንም ምን አልክ?
አስራት፡- ድሉ ይገባቸዋል፤ ምክንያቱም የዘንድሮው የውድድር ጅማሬ ላይ ጥቂት ከመቸገር ውጪ ዓመቱን ሙሉ በወጥ አቋም ላይ የተጓዙ ስለሆኑ ልክ እኛንና ቅዱስ ጊዮርጊስን ነጥብ ሲወስዱብን ነው ሻምፒዮና እንደሚሆኑም ያረጋገጥኩት፡፡
ሀትሪክ፡- የእናንተው አቡበከር ናስርም ዘንድሮ ጎልቶ በመውጣት የኮከብነት ሽልማቶችን ጠራርጎ ወስዷል፤ ስለ እሱስ ምን አልክ?
አስራት፡- አቡኪ ዘንድሮ ልዩ ተጨዋች ነበር፤ ከቡና ጋር በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር ጭምርም ጥሩ ጊዜን አሳልፏል፤ ለብሔራዊ ቡድንም ጥሩ ተጫውቶ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሀገራችንን ካሳለፉት ተጨዋቾች መካከልም አንዱ ሊሆን ችሏል፤ ስለ እሱ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም እየመሰከረ ነው፤ እሱን በቀላል ቃላት መግለፅም ይከብዳል፤ ፈጣሪ ይርዳው እንጂ ወደ ውጪ ወጥቶም መጫወት የሚያስችል ምርጥ ብቃት ስላለውም የእሱ የዘንድሮ ኮከብነት ሲያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይደለም፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና አስቆጪና ፈታኝ የነበረው የዘንድሮ ግጥሚያ የቱ ነው? የተደሰታችሁበትስ?
አስራት፡- ያስቆጨንና ፈታኙ ጨዋታ ከሻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ ጋር ያደረግነውና 1-0 የተሸነፍንበት ነው፤ በመጀመሪያው ዙር እኛ አሸንፈናቸው ነበር፤ ሁለተኛው ዙር ላይ ግን ግጥሚያው ለእኛም ወደ ዋንጫው ለምናደርገው ጉዞ ወሳኝ ነበርና በመሸነፋችን ያ ነው ያስከፋን፤ የተደሰትንባቸው ጨዋታዎች ደግሞ የዘንድሮ አብዛኛዎቹን ግጥሚያዎች በኳስ ቁጥጥርም በልጠን ያሸነፍንባቸው ስለሆኑ እነሱን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከመጣ በኋላ ኳሳችን በተመረጡ ሜዳዎች ላይ ነው የተካሄዱት፤ ከዛ በፊት ግን በእያንዳንዱ ክለብ ሜዳ የደርሶ መልስ ጨዋታ ነበር የሚካሄደው የቱ ይሻላል?
አስራት፡- የአሁኑ ነዋ! ምክንያቱም በፊት በነበረው ውድድር ከበቂ ጥበቃ አንስቶ ብዙ ችግሮችን ልንመለከት ችለናል፤ በዚህ ወቅት ላይ ግን ጨዋታዎቹ በዲ.ኤስ.ቲቪ እየተላለፉ ስለሆኑም ጭምር ግጥሚያዎቹ በጥራት የሚቀረፁ ስለሆነና አንድ ጥፋት ቢሰራም እነዛ በማስረጃ መልክ ቀርበው ቅጣት ሊያስጥሉ ስለሚችሉ ከዛ ውጪም ግጥሚያን የምታሸንፈውም ኳስን መሰረት ባደረገ ነገርና ባለህም አቅም ላይ ተንተርሰህ ስለሆነ ይኸው አሁን ከበፊት አንፃር ሰላማዊ በሆነ መልኩ ጨዋታዎች እየተካሄዱ ይገኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእስካሁን ቆይታህ የሊጉን ዋንጫ ለአንዴም አላነሳህም፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
አስራት፡- አዎን፤ የእውነት ነው፤ በተለይ ደግሞ በምርጡና በትልቁ ቡድን ኢትዮጵያ ቡና ስር ሆኖ ይህን ዋንጫ ከዚህ ክለብ ጋር አለማንሳት በጣም ይቆጫል፤ ስለዚህም ትልቅ የቤት ስራ አለብኝና በመጪው ዘመን በሚካሄደው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ይህን ዋንጫ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ከፍ አድርጎ ማንሳት ዋንኛው ምኞቴ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- እንደ ኢትዮጵያ ቡና ተጨዋችነትህ ይህን ድል የምታሳኩ ይመስልሃል?
አስራት፡- ለማሳካትማ ነው ለክለቡ እየተጫወትን የምንገኘው፤ በዚህ ጉዳይ ዋናው የአሰልጣኙ ስራ ቢሆንም ኢትዮጵያ ቡና እንደ ትልቅ ቡድንነቱ ይህ ድል ይገባዋል፤ እኛ ተጨዋቾችም በእሱ ስር የሚሰጠንን ስልጠና ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እያደረግንለት ከሄድን እልማችን ይሳካል፤ ደግሞም አሁን ተመሳሳይ የነበረው እንቅስቃሴው እያደገም መጥቷልና ጊዜው ሲደርስ ሁሉን ነገር የምናየው ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- ስለ ግል ህይወትህ እናንሳ፤ ስለ ውሃ አጣጪህ አንድ ነገር ብትል?
አስራት፡- በጣም ጥሩ የሆነች ሚስት ነው ያለኝ፤ መሰረት ጣሰው ትባላለች፤ ከእሷ ዮሃና አስራት የምትባል የአንድ ዓመት ከሁለት ወር ሴት ልጅንም ልናፈራም ችለናል፤ የግል ህይወቴን በተመለከተ ፈጣሪ ይመስገን ከባለቤቴ ጋር በመልካም ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው፤ ስለ እሷ ለማለት የምፈልገው ተጨማሪ ነገር ስለ ኳስ ተጨዋች ህይወት ከክልል ወደ ክልል በመሄድ የምንጫወትበት ሁኔታ ስላለ በደንብ ነው ስለ እሱ የምትረዳውና ከጎኔ ሆና የአቅሟን ብዙ ነገሮችን እያደረገችልኝ ነው፤ ለእዚህም ከፍ ያለ ምስጋና ለእሷ ላቀርብላት እፈልጋለው፤ በጣምም እወዳታለው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?
አስራት፡- በኢትዮጵያ ቡና ቆይታዬ ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ነው፤ ከእዚህ ቡድን ጋርም በመጪው የውድድር ዘመን ላይ ዘንድሮ ካሳየሁት ብቃት በተሻለ መልኩም ለክለቡ ግልጋሎትን ከመስጠት ባሻገር በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎአችን ላይም የቡድኑን አጨዋወት ባለቀቀ መልኩ ከቡድን አጋር ጓደኞቼ ጋር ጥሩ ውጤትን ለማስመዝገብ ጥረትን እናደርጋለን፤ ለተመረጥኩበት ብሔራዊ ቡድንም በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሻለ ነገር ለመስራት ራሴን ከወዲሁ አዘጋጃለው፤ በተረፈ በኳስ ህይወቴ ከጎኔ ለነበሩትና ሁሌም ያለስስት ድጋፋቸውን ለሚሰጡኝ የቡና ደጋፊዎች ምስጋናን አቀርባለው፡፡
አስተያየት ይስጡ