በ2013 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ሳይጠበቅ የዉድድር አመቱን ላለመዉረድ ሲታገል የነበረዉ ሲዳማ ቡና በመጨረሻም በአሰልጣኝ ገ/ሙድህን አማካኝነት የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታዎች ሀዋሳ ላይ ሲደረጉ ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ በሊጉ መቆየት ችለዉ ነበር። አሁን ደግሞ በቀጣይ አመት በሊጉ ለሚኖራቸው ዉድድር ተጠናክረዉ ለመቅረብ ይረዳቸዉ ዘንድ የቀድሞውን የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካኝ ሙሉአለም መስፍን/ዴኮ/ በሁለት አመት የኮንትራት ዉል አስፈርመዋል።
የመሀል ሜዳ ተጫዋች ሙሉአለም የ2013 አመትን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ማሳለፉ የሚታወስ ነዉ። ነገር ግን ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዲሲፕሊን ምከንያት እርሱ ላይ እና የተወሰኑ የቡድን አጋሮቹ ላይ ከበድ ያለ ቅጣት በማስተላለፉ ምክንያት የሊጉን የመጨረሻ 8 ጨዋታዎች መጫወት አልቻለም ነበር።
አሁን ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት የነበረዉ የኮንትራት ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ በዛሬዉ ዕለት የቀድሞ ክለቡን ሲዳማ ቡና በሁለት አመት የዉል ስምምነት በይፋ ተቀላቅሏል።
አስተያየት ይስጡ