16ኛውን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተከትሎ ወደ ለንደን ያቀናው የሀትሪክ ጋዜጣ
ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ባለፈው ሳምንት የለንደን ቅኝቱንና የአትሌቲክሱ
ሌሎች አደጋዎች ወይም የተቀበሩ ፈንጂዎች ናቸው ባላቸው ጉዳዮች ላይና ስጋቶቹን “በለንደን
ክፍል አንድ” ትዝብቱ አሰቃኝቶናል፡፡ ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ዛሬ ደግሞ “ዋው ኤምሬትስ
- ማሰታውቂያ -
ከስቴድየምም በላይ” በማለት ስለ ግዙፉ ኤምሬትስ ስቴድየምና በውስጡ አካቶ ስለያዛቸው
የሚነበቡ ታሪኮች በስፋት ሊነግረን ተዘጋጅቷል፡፡ ጋዜጠኛው “ኤምሬትስ ስቴድየም ብቻ
ሳይሆን በውስጡ በርካታ ገፆች ያሉት ታሪኮችን በውስጡ ሸሽጎ የያዘ የሚነበብ ዳጎስ ያለ
መፅሀፍ ነው” ሲልም ያየውንና የታዘበውን መሳጭ በሆነ አቀራረብ አዲስ አበባ ተቀምጠው
ኤምሬትስን ያስጎበኝዎታል፡፡ 360 ሰዓቶችን በለንደን ሰማይ ስር ያሳለፈው ጋዜጠኛ ይስሀቅ
በላይ በኤምሬትስ ምን አየ? ምንስ ታዝቦ ተመለሰ? የለንደን ትዝብቱስ ምን ይሆን? ቀጣዩ
በጋዜጠኛው የተዘጋጀው መሳጭ ዘገባ መልስ አለው፡፡
ጉዞ ወደ ኤምሬትስ
ወደ ለንደን የሚያስገባኝን ቪዛ
እንዳገኘሁ የጉዞ ዕቅዴን ሳወጣ ይህችን
በእግር ኳስ እሳት የምትንቀለቀል፤ የምትፋጅ
አገር ክለቦችን በተለይ ግዙፉን ኤምሬትስ
ስታዲየም፣ የቀያይ ሰይጣኖቹን ኦልድ
ትራፎርድ እና ስታምፎርድ ብሪጅን በአካል
ተገኝቶ መጎብኘትና ጨዋታ መከታተል
የሚለው በማስታወሻ ደብተሬ በመጀመሪያው
ረድፍ ላይ የሚገኝ ዕቅዴ ነበር፡፡ ዕድል
ቀንቶኝ የምኞቴን ወይም የጉጉት ረሃቤን
ያስታገስኩበት ግን ደግሞ ደግሜ ደጋግሜ
የጎበኘሁትና የፕሪሚዬር ሊጉን የመክፈቻ
ጨዋታ በግዙፉ ኤምሬትስ ስቴዲየም ተገኝቼ
የተከታተልኩ ቢሆንም “The Home of The
Champions” በሚል ተቆላምጦ የሚጠራውን
በለንደን እምብርት (Central London)
የሚገኘውን የቼልሲውን ስታምፎርድ ብሪጅን
የመጎብኘት ዕድል አግኝቼ ከመንግስት
የተለመደ ቃል ልዋስና “ከእቅዴ ከግማሽ
በላይ” አሳክቼ ተመልሼያለሁ፡፡ የጊዜ
እጥረትና መግቢያ ትኬት አለማግኘት
በፈጠሩብኝ ርብርቦሽ ወደ ቀያዮቹ መንደር
ኦልድ ትራፎርድ ሄጄ እውነተኛውን ስሜት
አጣጥሜ መመለስ አለመቻሌ በውስጤ
የፈጠረብኝን ቁጭት ያገኘኋቸው ሁለቱ
አጋጣሚዎች ለማስረሳት መሞከራቸውን ግን
አልሸሽግም፡፡
ዋው ኤምሬትስ…! ከስቴዲየምም በላይ
በውስጡ በርካታ ገፆች
ያሉት፤ ታሪኮችን በውስጡ
ሸሽጎ የያዘ የሚነበብ ዳጎስ
ያለ መፅሀፍ
ኤምሬትስን ለማየት በጣም ጓጉቻለሁ፤
የእነዛ ክዋክብት ድንቅ ጥበብ እንደ ዥረት
የሚፈስበት ይህ ግዙፍ ስቴዲየም በቅርበት
ተጠግተው ሲያዩት ምን ይመስል ይሆን?
የሚለው ጥያቄ የጉጉቴን መጠን በዕጥፍ
ጨምሮታል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኛ
ያረፍንበት ቤት ለማየት ከጓጓሁት ኤምሬትስ
ስቴዲየም በጣም በቅርብ ርቀት ላይ
የሚገኝ መሆኑን መስማቴ ህልሜን በእጄ
እንደምጨብጠው የስሜን ያህል እርግጠኛ
እንድሆን አድርጎኛል፡፡
ከለንደን ባህሪ፣ ከትራንስፖርት
ሲስተሙ፣ መውጪያ መግቢያውን እስከማ
ውቅና በአጠቃላይ አገሪቱን እስክላመድ
ጥቂት ቀናትን ለመግዛት ብወስንም
ውስጤ “ኤምሬትስ፤ ኤምሬትስ ስቴዲየም”
እያለ መወትወቱን አላቆመም፡፡ “ጉዞ ወደ
ኤምሬትስ” እያለ ውስጤ ለሚያቀርበው ጥያቄ
አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ሐምሌ 27 የእኔና
የኤምሬትስ ስቴዲየም በአካል የመተዋወቂያ
የመጨረሻ ቀን ሆና ተቆረጠች፡፡
በፈካችው የዕለተ ዓርብ የማለዳ
ፀሐይ ሙቀት ታጅቤ የፒካዲሊ ላይን
ባቡሬን ለመሳፈር ለሰባት ቀናት ብቻ
የሚያገለግለውንና በ47 ፓውንድ (በጥቁር
ገበያ ምንዛሬ 1 ሺህ 654 ብር) የገዛኋትን
“Oyster” ካርዴን ወደ ባቡር ጣቢያው
የሚያስገባውና ካርዱን ወደሚያነበው ማሽን
አስነካሁ፤ ማሽኑም የካርዱን ህጋዊነትና
ሂሳብ እንዳለው በማረጋገጥ አረንጓዴ
መብራት በማሳየት እንዳልፍ አጠር ያለውን
የኤሌክትሪክ በር ከፈተልኝና ገባሁ፡፡
ባቡር በምንጠብቅበት ቦታ ላይ የባቡሩ
መምጪያን የሚጠቁመውን ዲስፕሌይ
ለማየት ቀና ባልኩበት ቅፅበት እኔን ከአርሰናሉ
ኤምሬትስ ስቴድየም ጋር ለማገናኘት ተሸክማ
የምትወስደኝ የመሬት ውስጥ ባቡር አጠገቤ
ደረሰች፤ ሳላመነታ በፍጥነት ተሳፈርኩ፡፡
ኤምሬትስ ስቴዲየም ለመድረስ ሁለት የባቡር
ጣቢያዎች (Stops) ብቻ እንደሚያስፈልገኝ
መረጃ ስለያዝኩ ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ
ክለቦች ለንደን ውስጥ በስሙ በብቸኝነት
የባቡር ጣብያ (Arsenal Station) በሚል
የተሰየመለት አርሰናል ስቴሽንን አልፌ
ሆላዌይ ስቴሽን ጋር ወረድኩ፡፡ ይሄ የባቡር
ጣቢያ ከኤምሬትስ ስቴዲየም በ10 ደቂቃ
የእግር ጉዞ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ
ለማየት ወደ ጓጓሁበት ቦታ ያለ ብዙ ድካም
እንደምደርስ የበለጠ እምነት እንዳሳድር
አድርጎኛል፡፡
መድረሴ አይቀርም ደረስኩ፡፡ አንገቴን
ቀና አድርጌ ግርምት በተሞላበት ሁኔታ
አይኖቼን ስወረውር 931 ሚሊዮን ፓውንድ
እንክት አድርጎ የበላው ግዙፉ የኤምሬትስ
ስቴድየም በማን አለብኝነት የኩራት መንፈስ
ደረቱን ገልብጦ ከፊት ለፊቴ ተገትሯል፤
የማየውን ሁሉ ማመን አቃተኝ፤ ህልም
የሚመስል ዕውነት ሆነብኝ፡፡ ግርምት፤
ደስታ፤ የተዘበራረቀ ስሜት ለአፍታ በውስጤ
ተፈጠረ፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች
ላይ ተጋብዤ ከአፍሪካ እስከ ኤሽያ፤ ከኤሽያ
እስከ አሜሪካ፤ ከአሜሪካ እስከ ካናዳ፤
ከካናዳ እስከ አውሮፓ ተዘዋውሬ በርካታ
ስቴዲየሞችን ጎብኝቻለሁ፡፡ ውድድሮችንም
በአካል ተገኝቼ ተከታትያለሁ፤ ኤምሬትስ
ግን ፍፁም ልዩ ነው፤ የሆነ ቀልብን የሚስብ
ማራኪ ግርማ ሞገስ ተላብሷል፡፡
ከዚህ በፊት የቻይናውን በርድስኔስት
(የወፍ ጎጆ) ስቴዲየም፣ የጀርመኖቹን የበርሊን
ኦሎምፒክ ስቴዲየም፣ የፍራንክፈርቱን
ፍራንክፈርት ስቴዲየም፣ የሆፌኔይም
ስቴድየም፣ የፖላንዱን Stadion Narodowy
Warszawe (ዋርሶው ስቴዲየም)፣ የደቡብ
አፍሪካውን ሶከር ሲቲና የደርባኑን Moses
Mabhida ስቴዲየሞችን፣ በካናዳ የኦታዋና
ሞንትሪያል ስቴዲየሞችን የመጎብኘትና
ውድድሮችን የመከታተል ዕድልን
ሰጥተውኛል፤ እነዚህ ሁሉ ስቴዲየሞች ግን
የአርሰናሉን ኤምሬትስን ያህል ገዝፈውና
ደምቀው አልታዩኝም፡፡ ኤምሬትስ ስቴዲየም
በዕውነት ለመናገር ስቴዲየም ብቻ ነው
ለማለት ይቸግረኛል፤ የሥነ-ህንፃ ግንባታው፤
ግርማ ሞገሱ አንዳች የደስታ ስሜትን
በውስጥ ይፈጥራል፡፡ የበለጠ እየተጠጋሁትና
እየቀረብኩት በሄድኩ ቁጥር ነፍስና ስጋ
ተላብሶ የሚንቀሳቀስ ግዑዝ አካል ሆኖ ነው
የታየኝ፤ ብቻ ምን አለፋችሁ ኤምሬትስን
በግርምትና በመደነቅ ለደቂቃዎች ፈዝዤ
ተመልክቼዋለሁ፡፡
ሌላ ታሪካዊ ነገር ፍለጋ ወደ ዋናው
የስቴዲየሙ የመግቢያ በር እየተጠጋሁ
ስሄድ ከፊት ለፊቴ የቆመ አንድ ሀውልት
ይበልጥ ትኩረቴን ሳበው፤ ለአንድ የክለቡ
መስራች ወይም ባለውለተኛ የቆመ ሀውልት
እንደሆነ ለመገመት ግን ብዙም ማሰብ
አልፈለግኩም፡፡ ይበልጥ ወደ ሀውልቱ
እየተጠጋሁና እየቀረብኩ ስሄድ ሀውልቱ
ከግምቴ ውጪ አለመሆኑን አረጋገጥኩ፡
፡ እንደ ግምቴ በስቴዲየሙ መግቢያ
ደረጃውን እንደወጡ በዋናው መግቢያ በር
ላይ እንደሚበር አሞራ ሁለቱን እጆቹን ወደ
ጎን ዘርግቶ፤ ደረቱን ለፀሃይ ሰጥቶ የቆመው
ሃውልት ለ23 ዓመታት ከ22 ዓመት ዕድሜው
ጀምሮ አርሰናሎችን በአምበልነት የመራው
ጠርሙስና መለኪያ ውስጥ መደበቁና የመጠጥ
ሱሰኝነቱ ለክለቡ የዋለውን ውለታ ያልሸፈነበት
የቶኒ አዳምስ ሀውልት ነው፡፡ ሀውልቱን ጠጋ
ብዬ ስመለከተው ያ ለዓመታት በቴሌቪዥን
መስኮት ብቻ ስመለከተው የነበረውን ሰው
በአካል ያገኘሁት ያህል ተሰማኝ፤ የአርሰናሉ
ድንቅ ሰው በህይወት ቆሞ የሚያናግረኝ
ነበር የሚመስለው፡፡ ሀውልቱ የቆመው
ለትክክለኛውና ለተገቢው ሰው ነው ብዬ በልቤ
ምስክርነቴን ሰጠሁ፡፡ በዕለቱ የኤምሬትስ
ስቴዲየም ጉብኝቴ እንደተረዳሁት ይህ የቶኒ
አዳምስ ሀውልት አርሰናል በ1988 ዓ.ም
ኤቨርተንን 4ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፎ
የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ቶኒ አዳምስ
ለራሱም ለአርሰናልም የመጨረሻ የሆነችውን
ጎል ካስቆጠረ በኋላ ያሳየውን የደስታ አገላለፅ
ህያው አድርጎ ያስቀረ ሀውልት እንደሆነ
የክለቡ ስቴዲየምና የትጥቅ መሸጫ ሰራተኞች
ግርምት በተሞላበት ሁኔታ አጫውተውኛል፡፡
ቶኒ አዳምስ በአርሰናል የሚከበር
ምንጊዜም የማይዘነጋ ተጨዋች በመሆኑ
ክለቡ ተጨዋቹ በህይወት እያለ ለውለታው
ማስታወሻና መጠሪያ የሚሆን ሀውልት
በግዙፉ ስቴዲየም ውጫዊ ክፍል ማቆሙ
የሚያስተላልፈው መልዕክት በቃላት የሚገለፅ
አይደለም፡፡ እኔም የዚህን የክለቡ ሌጀንድ
(ህያው) ተጫዋች ሀውልት ስመለከት
ወዲያውኑ ወደ አዕምሮዬ የመጣው
ለአርሰናል ለ23 ዓመታት ያበረከተው በወርቅ
ቀለም የተፃፈው ውለታው ወይም ስሙ
ከመጠጥ ጋር ባለው የጠነከረ ፍቅር ተያይዞ
ሲነሳበት የነበረው ዘመን ሳይሆን ከክለቡ ጋር
የነበረውን የ23 ዓመታት ቁርኝትን የገለፀበት
መንገድ ነው። “ከምወደው ከዚህ ክለብ ጋር
ለ23 ዓመታት በትዳር የቆየሁ፣ ክለቡም
ልክ የቀድሞ ባለቤቴን ያህል ነው አሁን
የሚሰማኝ” በሚል የገለፀበት መንገድ ሁሉን
ነገር ይገልፀዋል፡፡ ይህ አባባሉ እውነትነት
ስላለውና ባነበብኩት ጊዜ ስለማረከኝ ነው
ያነሳሁት፤ የቶኒ አዳምስና የአርሰናል ግንኙነት
ከጋብቻም በላይ ነው፤ ቶኒ ከአርሰናል ጋር
በፍቅር በተሳሰረበት 23 ዓመታት ለክለቡ
ውጤታማነት ደምቷል፣ በደስታ ጮቤ
ረግጧል፣ በሃዘን አንብቷል፣ ክለቡንም ወደ
ሌላ ምዕራፍ እንዲሸጋገር የራሱን ጡብ
ያስቀመጠ ተጨዋች በመሆኑ ግንኙነቱ በዚህ
ደረጃ ቢገለፅና ሀውልት ቢቆምለት አይገርምም
አልኩ ሳላስበው ብቻዬን፤ ደግነቱ አማርኛ
የሚሰማ ሰው በዙሪያዬ አለመኖሩ ጠቀመኝ
እንጂ ውስጤና አንደበቴ ተስማምተው ለቶኒ
ድጋፋቸውን በአንድነት ሰጥተዋል፡፡
ቶኒ አዳምስ ለአርሰናል ያበረከተው
ውለታን የሚታዘቡ ሰዎች በመኖራቸው
በህይወት እያለ ያቆሙለትን ሀውልት አይቼ
ከጨረስኩ በኋላ “በእኛስ ሃገር ባለውለተኛ
በህይወት እያለ ውለታው በቁም የሚዘከርለትና
ሀውልት የሚቆምለት መቼ ይሆን?” እያልኩ
ከራሴ ጋር ራሴው እየተጨቃጨኩ ድንገት
ዞር ስል ሌላ ልቤን ለሁለት የሚከፍል
ታሪካዊ ሀውልት ተመልክቼ እጄን በአፌ
ላይ በግርምት ጫንኩ፡፡ ሳላስበው ድምፄን ከፍ
አድርጌ “ዋው ሆንሪ” ብዬ በአካል ያገኘሁት
ያህል ስጮህ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች “
በደህና ነው?” በሚል አይነት ስሜት ሁሉም
ዞር ብለው ገረመሙኝ፤ አዎን በአርሰናል
ክለብ ውስጥ ለስምንት ዓመታት (ከ1999-
2007 ዓ.ም) ደምቆ ያንፀባረቀውን ለበርካታ
ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊያን
ጭምር የአርሰናል ደጋፊ እንዲሆኑ
ጫና ያሳደረው የሆንሪን ሀውልት ያውም
በተለመደው የደስታ አገላለፅ ማየት ያስጮሃል፤
ከላይ እንደገለፅኩት በኤምሬትስ መግቢያ በር
ላይ ያለው የክለቡ ትጥቆች መሸጫ ሱቅና
ከሜዳው ሰራተኞች እንደተደረገልኝ ገለፃ
ከሆነ በእኔ ላይ የታየው ግርምትና ድንጋጤ
በብዙዎች በተለይ ከአፍሪካ በሚመጡ
ጎብኚዎች ላይ የሚንፀባረቅ በመሆኑ ፊቴ
ላይ በታየው የደስታ ስሜትና ጬኸቴ
ብዙም እንዳልተገረሙ ዘና ባለና በፈገግታ
በታጀበ ስሜት ገልፀውልኛል፡፡ እንደ እነዚሁ
የክለቡ ምንጮች አገላለፅ ከሆነ የፈረንሳዊው
የአርሰናል ኮከብ የብር ሀውልት የሚያሳየው
የደስታ አገላለፅ ሁሌም ጎል ሲያስቆጥር
የተለመደው አይነት የደስታ አገላለፅ ቢሆንም
ሀውልቱ በዋናነት የሚያንፀባርቀው ግን ሆንሪ
በኖቬምበር 2002 ዓ.ም በሀይብሪ ስቴዲየም
ኒውካስትል ዩናይትድ ላይ ምርጥ ጎሉን
ካስቆጠረ በኋላ ያሳየው የማይዘነጋ የደስታ
አገላለፅ በሀውልት ተቀርፆ እንደተቀመጠ
አውግተውኛል፡፡
የኤምሬትስ ስቴዲየምን በቀንም በምሽትም
ተዘዋውሬ ብጎበኝም በቀላሉ ልጠግበው ግን
አልቻልኩም፤ በጉብኝቴ ወቅት ለመረዳት
እንደ ቻልኩት ኤምሬትስ ስቴዲየም ብቻ
ሳይሆን የሚነበብ ቅርስ ወይም ቤተ-መፅሃፍት
ነው ማለት እችላለሁ፤ ኤምሬትስ ስቴዲየም
ዙሪያውን ታሪክ ይናገራል፤ ስለ ታሪክ አፍ
አውጥቶ ይመሰክራል፤ ስቴዲየሙ ይታያል
ብቻ ሳይሆን ገለጥ ገለጥ እየተደረገ የሚነበብ
መፅሐፍም ነው፡፡ ኤምሬትስ ለባለውለተኞች
ተገቢውን ምስክርነት እንዴት መስጠት
እንደሚቻል ብቻ ሳይሆን ባለውለተኞች
ዋልታና ማገር ሆነው እንዳቆሙት ይናገራል፡፡
አርሰናል 125ኛውን ክብረ-በዓሉን
ባከበረበት ዕለት ከላይ በዋናነት ካነሳኋቸው
ቶኒ አዳምስና ቲዬሪ ሆንሪ በተጨማሪ
ለአምስት የክለቡ ባለውለተኛ ለሆኑት ለዴኒስ
ቤርግካምፕ፣ ለምትክ አልባው የክለቡ
የቀድሞ ማናጀር ሄርበርት ቻፕማን፣ የክለቡ
ማኔጂንግ ዳይሬክተር ለነበሩት ኩን ፍሪያር
በኤምሬትስ በብርየተለበጠ የመታሰቢያ
ሀውልት እንደቆመላቸው ወደዚህ ግዙፍ
ስቴዲየም እግር ጥሎት ብቅ ያለ ሁሉ አይቶ
የሚመሰክረው ነው፡፡
እግሬ እስኪቀጥን ኤምሬትስን
እየተዟዟርኩ መጎብኘቴን ቀጥያለሁ፤
በኤምሬትስ ውጫዊ ክፍል
ወይም ክሎክ ኢንድ
በሚባለው ቦታ ላይ የቆመው
የአርሰናሉ አንፀባራቂ ኮከብ
ዴኒስ ቤርግካምፕን ሀውልት
ሲመለከቱ ፈጣኑ የሃሳብ
ባቡር በቅፅበት ወደ ጨዋታ
ዘመኑ ይወስዶታል፡፡
የዴኒስ ቤርካምፕ
ሀውልት የሚያንፀባርቀውና
መነሻው አድርጎ ሀውልቱ የተቀረፀውም
ፌብሪዋሪ 9/2003 ዓ.ም ከኒውካስትል
ዩናይትድ ጋር የተደረገውን ምርጥ የጨዋታ
እንቅሰቃሴ በሚዘክር መልኩ ነው፤ በኤምሬትስ
ስቴዲየም ጉብኝቴ በጣም የገረመኝ ዴኒስ
ቤርግካምፕ ለአርሰናል ሲፈርም በወቅቱ
የክለቡ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የነበሩት የኩን
ፍሪያር የመታሰቢያ ሀውልትም ከእሱ ጎን
አብሮ በኤምሬትስ ስቴዲየም ውጫዊ ክፍል
መታየቱ ቀልቤን በተለየ መልኩ ስቦታል፡፡
የኤምሬትስን ስቴዲየም ልዩ ድባብ
ያላበሱት የእነዚህ የአምስቱ የክለቡ
ባለውለተኞች ሀውልት ተሰርተው ለመጠናቀቅ
625 ሰዓታትን የፈጁ ሲሆን እያንዳንዳቸውም
200 ኪ.ግራም እንደሚመዝኑም የጉብኝቴ
ውጤት አረጋግጦልኛል፡፡ ዋው ኤምሬትስ…!
ስቴዲየም ብቻ ሳይሆን በውስጡ በርካታ
ገፆች ያሉት በርካታ ታሪኮችን በውስጡ ሸሽጎ
የያዘ የሚነበብ ዳጎስ ያለ መፅሀፍ፡፡
N Stand የወንበር ቁጥር 932
ከላይ በርዕሱ የተቀመጠው ይህ ቁጥር
በህይወቴ ውስጥ የማይረሳ ብቻ ሳይሆን
ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው፤ ወንበር
ቁጥር 932 ከእንግዲህ በትልቅ ታሪክነት
ከማነሳቸው ቁጥሮች ትልቁን ቦታ ይይዛል
ለእኔ፡፡ የ2017/18 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ
የመክፈቻ ጨዋታ በትልቅ ባህር (ውቅያኖስ)
በሚመሰለው የአርሰናሉ ግዙፍ ስቴዲየም
የአርሰናልና የሌይሲስተርን ጨዋታ ቁጭ ብዬ
የኮመኮምኩበት ታሪካዊ የወንበሬ ቁጥር ነው-
932፡፡
የኤምሬትስ ስቴዲየም ውጫዊው
ክፍል ጉብኝቴ የፈጠረብኝ ከፍተኛ የደስታ
ስሜት ሳያባራ ፈረንጆች “Over the
moon” እንደሚሉት ጥግ የደረሰ ደስታን
የሚያገጎናፅፈኝ አጋጣሚ ተፈጠረ፡
፡ በኤምሬትስ ስቴዲየም
N Stand ወንበር ቁጥር 932
ተቀምጬ የተመለከትኩት ሁሉ
በዕውኔ የተመለከተኩት ህልም ይመስላል፤
የወንበር ቁጥር 932 በዕለቱ የሁለቱን ቡድኖች
ጨዋታ ከተከታተሉት 59,387 አንዱ ሆኖ
ስሜ እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኖኛል፤
በኤምሬትስ ተገኝቶ ጨዋታ መከታተል የተለየ
ስሜት ይፈጥራል፤ አንዳች የተለየ የሙቀት
ስሜት እንዲሰማም ያደርጋል፤ በምድር ላይ
ለብቻው የተቀመጠ ጥልቅ ባህር (ውቅያኖስ)
የሚመስለው ስቴዲየም የተመልካቹ ድባብና
ለየት ያለው የድጋፍ አሰጣጥ እስከ ዛሬ ካየሁት
ፍፁም የተለየ ነው፡፡ በአርሰናልና በሌይሲስተር
መካከል የሚደረገው የውድድር ዓመቱ
የመጀመሪያና የመክፈቻ ጨዋታ መሆኑ
ተዳምሮ የስቴዲየሙን ውስጣዊና ውጫዊ
ድባብ የተለየ በማድረጉ ሃሴትን አጎናፅፎኛል፤
በኤምሬትስ ስቴዲየም N Stand በወንበር
ቁጥር 932 የተመለከትኩት የሁሉቱ ቡድኖች
ጨዋታ የ90 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ክንፍ
አውጥቶ ሲበር ያየሁት ኤምሬትስ ላይ ነው፤
መቼ ተጀምሮ ከመቼው እንዳለቀ ለማስታወስ
እቸገራለሁ፤ ዘፈን ይደገም እንደሚባል
አውቃለሁ፤ ይደገም ከተባለ ግን የአርሰናልና
የሌይሲስተር ጨዋታ ህጎች ተሽረውም ቢሆን
ቢደገም ምርጫዬ ነው፡፡ 7 ጎል የዘነበበት፣
ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር የታየበት የሁለቱ
ቡድኖች ጨዋታ ከሌሎች ታላላቅ ታሪኮቼ ጋር
በግንባር ቀደምትነት ሲነሳ ይኖራል፡፡
የኤምሬትሱ N Stand የወንበር ቁጥር
932 በርካታ ታሪኮችን ስላሳፈሰኝና መልካም
የሚባሉ አጋጣሚዎችን ስለ ፈጠረልኝ በህይወት
ዘመኔ በመልካምነት ስዘክረው እኖራለሁ፤
ከፒተር ቼክ እስከ ላካዜቴ፣ ከዣካ እስከ ዳኒ
ዌልቤክ፣ ከሆልዲንግ እስከ ቻምበርሌይን፣
ከኦዚል እስከ ኤልኔኒ እና ዋልኮት በዕለቱ
ሞዴል መስለው የቀረቡትን ፕሮፌሰሩን
ቬንገርን ጨምሮ የ2016/17 ዓ.ም የፕሪምዬር
ሊጉ ክስተት የነበሩትን የሌይሲስተሮቹን
ሽማይክል፣ ጃሚ ቫርዲ፣ ኦካዛኪ፣ ማህሬዝን
እና ሌሎችን የሁለቱ ክለቦች አንፀባራቂ
ክዋክብቶችን ድንቅ ጥበብ የወንበር ቁጥር
932 ያለ ስስት እንደምኮመኩም ስላደረገኝ
ይሄን የወንበር ቁጥር ከሌሎች ቁጥሮች
በተለየ ሳከብረውና ሳሳታውሰው እኖራለሁ፡
፡ ለአንድ የስፖርት ጋዜጠኛ፤ አንድ እግር
ኳስን ለሚወድ ሰው ከዚህ በላይ ምን አይነት
ውድ ስጦታ አለ? ለእኔ መልሱ “ምንም” ነው፡
፡ አልማዝ፣ ወርቅና ብር ወይም ቤትና መኪና
ትልቅ ስጦታዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለዘላለም
አብሮ የሚኖር ዕውነተኛውን ውስጣዊ እርካታ
ስለመስጠታቸው ግን እጠራጠራለሁ፡፡ ከዚህ
በፊት ደጋግሜ እንደ ገለፅኩት የስቴዲየም
የመግቢያ ትኬት በማመቻቸት የዚህ ታሪካዊ
ጨዋታ አካል እንድሆንና ለዛላለም በአዕምሮዬ
ታትሞ የሚቀር ታሪክ ባለቤት ያደረጉኝን
የትሪቡን ስፖርት የሬዲዮ ቶክ ሾው አዘጋጆች
ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃልን እና ኤፍሬም
የማነን ስለ መልካሙ ውለታቸው ደጋግሜ
ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ በለንደን በተለይ
በኤምሬትስ ስቴዲየም የተመከትኩት ታላቅ
ታሪክ በድንጋይ ተቀርፆ ከተቀመጠ ሃውልት
በላይ አብሮኝ የሚኖርና ዘመንን የሚሻገር
መሆኑን የምገልፀው ሌላ አዲስ ስኬትን
በመራብ ጭምር ነው፡፡
ስታምፎርድ ብሪጅ
“The home of the
Champion’s”
የአርሰናሉ
ግዙፉ ኤምሬትስ
ስቴዲየም የደስታ
ስሜት በሴንትራል
ለንደን የሚገኘውን
“The home of
the Champion’s”
የሚል የድል
መጠሪያ ያለውን
የቼልሲውን
8ስታምፎርድ ብሪጅ አጭር ጎብኝቴ
ሸፈነብኝ እንጂ ለንደን የሰጠችኝ ሌላው ወርቃማ
እድል ነው፡፡
ከዌስትሃም ክለብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ
ለሚሰራውና በአገራችን እግር ኳስን ወደ
ቢዝነስ ለውጦ የመስራት ትልቅ ሃሳብን
ሰንቆ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የwww.
abeshakickabout.com መስራችና ባለቤት
ለሆነው ትውልደ ጃማይካዊ በዜግነት እንግሊዛዊ
ለሆነው Alvin Grant ምስጋና ይግባና በነበረችኝ
አጭር ጊዜ ስታምፎርድ ብሪጅን እንድጎበኘውና
በቅርበት እንዳውቀው አድርጎኛል፡፡
በበርካታ በናጠጡ ሀብታሞች የተከበበውና
እጅግ በጣም ውድ የሆኑ ቤቶች በዙሪያው
የተበተኑበት በሚመስለው ፉልሃም ሮድ
የሚገኘው የወቅቱ ሻምፒዮኖች መቀመጫ
የሆነው ስታምፎርድ ብሪጅ ተገኝቼ ጨዋታ
የመከታተል ዕድሉን ባለማግኘቴ ብቆጭም
ከንግስቲቷ መኖሪያ ቤት በ10 ደቂቃ ርቀት
ላይ የሚገኘውን ስታምፎርድ ብሪጅንና የክለቡን
ሙዚየሞች ዙሪያውን ጎብኝቼ መመለሴ
ለሙያዬ ተጨማሪ ስንቅ ከወደ ለንደን ይዤ
እንድመለስ ረድቶኛል፡፡
ከለንደኖች የጠላሁት
15 ቀናትን ወይም 360 ሰዓታትን
ባሳለፍኩባት ለንደን በርካታ በህይወት
ዘመኔ የማላገኛቸው ታሪኮችን ያለ ስስት ጀባ
ብላኛለች፤ ከእኛዎቹ የሩጫው ዓለም ክዋክብት
ከሆኑት አልማዝ አያና፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣
ሙክታር እድሪስ፣ ታምራት ቶላ እና ሌሎች፤
ዓለም ሁሌም በድላቸውና በጀግንነታቸው
ስታስታውሳቸው፣ ስትዘክራቸው ከምትኖራቸው
አንፀባራቂ ኮከቦች ከሆኑት ከዩዜይን ቦልት
እስከ ሞ ፋራህና ጀስቲን ጋትሊን የመሳሰሉ
ድንቆችን ለንደን በቅርበት በማሳየት ታላቅ
ውለታን ውላልኛለች፤ ተዓምራዊ እግሮቻቸው
የሚሰሩትን ስራ በአካል የምታደምበትን ምቹ
ሁኔታም ፈጥራልኛለች፡፡ በእግር ኳሱም
ታሪካዊው የኤምሬትስ ስቴዲየምን ስታምፎርድ
ብሪጅን የእግር ኳሱ ዓለም ክዋክብት ከሆኑት
ደግሞ ከፒተር ቼክ እስከ ላካዜቴ፤ ከጃሚ ቫርዲ
እስከ ኦካዛኪና እስከ ትንሹ ሽማይክል (ካስፐር
ሽማይክል) ድረስ ተዓምራዊ ጥበባቸውን
አስኮምኩማኛለች፡፡ በበርካታ ላንድማርኮች
(የቱሪስት መስህቦች) የሆኑትን የለንደን
ሀብቶች፣ እድገትዋን፣ ስልጣኔዋን፣ ትናንትን
ከዛሬ አጣምራ በመያዝዋ የተፈጠረውን
ውበትዋን በአካል ተገኝቼ አጣጥሜ ነፍሴ
ሐሴት አድርጋለች፡፡
ይሄንን ሁሉ መልካም ነገር የሰጠችኝ
ለንደን ግን አንድ ጎደሎ ነገር አይቼባታለሁ፤
እንግሊዞች (ለንደኖች) ግለኝነት የሚያጠቃቸው
ከራሳቸው ውጪ የሚወዱትም ሆነ
የሚያወሩት ሰው አለመኖሩ አስገርሞኛል፡፡
ለንደኖች ማህበራዊ ህይወት የማያውቁ፣ በራስ
ወዳድነት ክፉኛ የተጠቁ፣ በእጃቸው ከያዙት
ስልክ ውጪ የሚያወሩት ነገርን አለማየቴ
በውስጤ ግርምትን ፈጥሮብኛል ብቻ ሳይሆን
ከለንደኖች ያየሁት ጎደሎ ነገር ሆኖብኛል፤
በቃ ለንደኖች ጨዋታቸው፣ ወሬያቸው ሁሉ
በእጃቸው ከያዙት ስልክ ጋር እንጂ አጠገባቸው
ካለው ዜጋቸው ጋር አለመሆኑ በሌላ አገር
ያልጠገመኝና ከልክ ያለፈ ግለኝነት መሆኑ
የግርምቴ ምክንያት ነው። በመዝናኛ ቦታ፣
ባቡር ላይ፣ በመንገድ ላይ ለንደኖች ጨዋታቸው
ሁሉ ከእጅ ስልካቸው ጋር ብቻ ነው፡፡
እንደ እኔ አይነቱ ባቡርና ትራንስፖርት
ውስጥ በመዝናኛ ቦታ ላይ ገበያ የሚመስል
ጨዋታ ከለመደበት አገር ለመጣ እንግዳ ሰው
በለንደኖች ግለኝነት የበዛበት ህይወት ቢገረም
አይፈረድበትም፤ እንደውም የለንደኖችን እጅግ
የበዛ ግለኝነት አይቼ በታዘብኩበት ቅፅበት
በአንድ ወቅት ብራዚሊያዊው የማን.ሲቲ
ተጫዋች ጋብርኤል የሱስ በለንደኖች ግለኝነት
የበዛበት ህይወትን ለመላመድ መቸገሩን
ለዴይሊ ሜይል ጋዜጣ የሰጠውን አስተያየት
አስታውሶኛል፡፡
“እንግሊዝን ሁሉንም ነገርዋን ወድጄው
ራስ ወዳድነታቸውን፣ ማህበራዊ ህይወት
አለማወቃቸውንና የበዛውን ግለኝነታቸውን
አልወደድኩትም ብቻ ሰይሆን መላመድ
አቅቶኛል” በማለት የሰጠው አስተያየት እኔንም
በለንደን የ15 ቀናት ቆይታዬ አጋጥሞኛል፡፡
እንግሊዞች (ለንደኖች) በስነ-ምግባር የታነፁ፣
ፍፁም ዲሲፕሊንድ የሆኑ ዜጎች እንደሆኑ
ባልክድም እጅግ የበዛው ግለኝነታቸውን ግን
እኔም እንደ ጋብርኤል የሱስ አልወደድኩትም፡
፡ ከሰው ይልቅ ከእጅ ስልካቸው ጋር የሙጥኝ
ማለታቸው ምቾት እንደነሳኝ ለንደንን ለቅቄ
ተመልሻለሁ፡፡
በለንደን ፖሊስ ጣቢያዎች
ታጥፈው ክስ (አቤቱታ)
በኦን ላይን መሆኑ
እዚህ በአገራችን በየመንደሩ ሳይቀር
የኮሚኒቲ ፖሊስ ጣቢያዎች እንደ አሸን
ፈልተዋል፤ መንግስት የህዝቡን ሰላም
በቅርበት ሊያስጠብቅ ይችላል በሚል ከዋና
ዋና ጣቢያዎች በተጨማሪ የኮሚኒቲ ፖሊስ
ጣቢያዎች በየ100 ሜትር ርቀት ላይ
ከፊታችን ቆመው እናያለን፡፡ ምን ያህል
ችግሮቹን አቅልለዋል የሚለው በጥያቄ ውስጥ
እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ በቅርቡ በተደጋጋሚ
በሽብር ጥቃት በተጠቃችው ለንደን ግን ነገሮች
ሁሉ ከእኛ በተቃራኒው ሆነው አይቼ በትዝብት
ተመልሻለሁ፤ በቅርቡ የግሪንፊል ታወር የእሳት
ቃጠሎ፣ የለንደን ብሪጅ የሽብር ጥቃት፣
ህፃናቶችን ጨምሮ 22 ሰዎች የሞቱበትና 59
ደግሞ የቆሰሉበት የማንቸስተር ከተማ ጥቃት
ሰለባ የሆነችው ለንደን የሚደርስባትን የሽብር
ጥቃት ለመከላከል የፖሊስ ጣብያዎቿን ቁጥር
በእጥፍ መጨመር ሲገባት በየቦታው ያሏትን
ፖሊስ ጣቢያዎች በማጠፍ ዜጎቿ ማንኛውንም
የፀጥታ ችግሮችም ሆነ የሽብር ጥቃቶች አሊያም
የእርስ በርስ አለመግባባቶች ሲከሰቱ ወደ ፖሊስ
ጣቢያ ከመሮጥ ይልቅ ባሉበት ቦታ ሆነው
በኢንተርኔት በኦን ላይን ሪፖርት የማድረግ
አዲስ ስርዓት ለመዘርጋት እየተንቀሳቀሰች
መሆኑ በለንደን ቆይታዬ ከስፖርቱ ውጪ
ግርምት ከጫሩብኝ ነገሮች አንዱ ሆኗል፡፡
የተደጋጋሚ የሽብር አደጋዎች ሰለባ የሆነችው
ለንደን ፖሊስ ጣቢያዎቿን አጥፋ በኦን ላይን
ሪፖርት የሚያደርጉበትን አሰራር ያውም በዚህ
ወቅት የመረጠችበትን መንገድ የሚያስረዳኝ
አጥቼ ወደ አገሬ ተመልሻለሁ፡፡ ይሄ ነገር
ለእኛ አገር በአውሮፕላን የተበተኑ የሚመስሉ
የኮሚኒቲ ፖሊስ ጣብያዎች ለበዙባት አገር
የሚያስተላልፈው ወይም የሚሰጠው ምን
ትምህርት ይኖር ይሆን?
የ2019ኛ ቀጣዩ የዓለም
አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስጋቴና
የዶሃ (ኳታር) ፈተናዎች
የለንደኑ 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ
ሻምፒዮና ጊነስ ወርልድ ሪከርድስ ላይ
በተመዘገበ አዲስ ሪከርድ መጠናቀቁና የቀጣዩ
17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን
የምታዘጋጀው ኳታር (ዶሃ) መሆኗ የ2019ኙን
ውድድር በስጋት እንድመለከተው አስገድዶኛል፡
፡ ኳታር (ዶሃ) ውድድሩን ባህላዊ እንደሆነውና
እንደተለመደው በኦገስት ወር መጀመሪያ
ላይ ሳይሆን ውድድሩን ባልተለመደ ሁኔታ
በሴፕቴምበር መጨረሻና በኦክቶበር መጀመሪያ
/September28- October 6/2019 ባለው
ጊዜ ውስጥ ለማከናወን መምረጥዋ በአገርዋ
ያለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ተዳምሮ
በውድድሩ ወቅት ከ37ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ
ይሆናል ተብሎ መገመቱ ለተመልካቾች ብቻ
ሳይሆን ለአትሌቶችም ትልቅ ጉዳት ያመጣል
በሚል ኳታር (ዶሃ) ላይ ከወዲሁ የጠነከሩ
ተቃውሞችን በለንደን ቆይታዬ ማድመጤ
የ2019ኙን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና
በገልፍ አገርዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለመካሄዱ
ስጋት እንዲያድርብኝ አድርጓል፡፡ ለመጀመሪያ
ጊዜ በተጠቀሱት ወራቶች በኳታር (ዶሃ)
የአትሌቲክስ ውድድሮች ተካሂደው የሙቀት
መጠኑ ለአትሌቶች ጉዳት ብቻ ሳይሆን
ለቀጣይ ጤንነታቸውም ጭምር አስጊ እንደሆነ
በባለሙያዎች በስፋት መነገሩ እንዲሁም በዚህ
ወቅት የተካሄዱት ውድድሮች በባዶ ሊባል
በሚችል ስቴዲየሞች ውስጥ መካሄዱ በአሁኑ
ወቅት ከአራት የገልፍ አገሮች ጋር ፖለቲካዊ
ውጥረት ውስጥ ላለችው አገር ኳታር (ዶሃ)
ነገሮች ከወዲሁ ፈታኝ ይሆንባታል የሚል
የጠነከረ እምነቱ አለኝ፡፡
የአሜሪካዋን Eugene Oregon ከተማ
እና የስፔንዋን Barcelona በ15 ድምፅ ብልጫ
የአትሌቲክሱን ታላቅ ድግስ በአካባቢው አገራት
ለመጀመሪያ ጊዜ ለማዘጋጀት የቆረጠችው ኳታር
(ዶሀ) ስለሙቀቱም አታስቡ፤ መስተንግዶውም
የተዋጣለት ይሆናል ብላ ብትናገርም ለንግግርዋ
ቁብ የሰጡት ጥቂት አገሮች ናቸው፡፡
የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለንደን
በሚገኘው ሚደያ ትሪቡን የጋዜጠኞች መቀመጫ
ቦታ ላይ ያገኘኋቸው ጋዜጠኞች ስጋትም ከእኔ
ጋር ተመሳስይ መሆኑን ባደረኳቸው ውይይቶች
ወቅት ያረጋግጡ ሲሆን አብዛኛዎቺ የሚዲያ
ሰዎች የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች
ማህበር የቀድሞ አመራሮች በተለይ አሁን
በእስር ላይ የሚገኙት ላሚን ዲያክ ስህተት
እንደፈፀሙ ገልፀውልኝ ጉዳዩ ከአትሌቲክስ በላይ
ሆኖ ሁዩማን ራይትስ ዎች ከመቃወም በዘለለ
ውደድሩ በፍፁም የሰዎችን ሰብአዊ መብት
በማታከብርውና ዲፕሉማሲያዊ ግንኙነትዋ
ከአጎራባች አገሮች ጋር እየተበላሸ ለመጣባት
አገር መሰጠት የለበትም የሚል አቋም መያዙን
ሳይሸሽጉ አጫውተውኛል፡፡
አሁን 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ
ሻምፒዮና ሊጀመር ድፍን ሁለት ዓመታት
ይቀሩታል ኳታር (ዶሃ) የውድድሩ አዘጋጅ
አገር ኃላፊነትን በመቀበል አረጋግጣለች፤
ኳታር ባንዲራውን ከተረከበችበት እለት ጀምሮ
መስተንግዶው ያማረ እንዲሆን ደፋ ቀና ማለት
መጀመርዋን ይፋ አድርጋለች፡፡ ይህ ሁኔታ
ግን ለብዙዎች ማረጋገጫ ሊሆናቸውና ከስጋት
ውጭ እንዲሆኑ አላደረጋቸውም፤ ብዙዎች
ዛሬም የኳታር (ዶሃን) የዓለም አትሌቲክስ
ሻምፒዮናን በስጋት መነፅር አሻግረው
እየተመለከቱ ነው፡፡ በተለይ የዓለማችን
ታላላቅ አትሌቶች ውድደሩ የሚካሄድበት
ቀን ከተለመደው መውጣቱና እስከ 37 ድግሪ
ሴንት ግሬድ በሚደርሰው የሙቀት መጠን
የመሮጣቸው ነገር ያሳሰባቸው በኳታር ዶሃ
ላይ ጥያቄ እየመዘዙ ነው፤ ውድድሩ ከኳታር
ተነጥቆ ለአዘጋጅነት እጩ ተፎካካሪ ለነበሩት
አገሮች ለአሜሪካዋ Eugene Oregon ወይም
ለስፔንዋ ባርሴሉና Barcelona 16ኛው የዓለም
አትሌቲክስ ሻምፒዮና የለንደኑን ኦሎምፒክ
በብቃት ላስተናገደችው አገር በድጋሚ እንዲሰጥ
ፍላጎት እያሳዩ ነው፡፡ ከዓለም አትሌቲክስ
ሻምፒዮናው ውጪ በ2020 በምታዘጋጀውና
የዓለም ዋንጫ የገልፍ አገራት ከሆኑት
ጎረቤቶቿ ጋር በገባችው እስጣ እገባ ውጥረት
ውስጥ ያለችው በነዳጅ ሀብት የናጠጠችው
ኳታር (ዶሃ) እነዚህን ሁሉ መሰናክሎችን
አልፋ 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና
ታስተናግድ ይሆን..? ጊዜ የሚሰጠውን ምላሽ
መጠበቅ መርጫለሁ፡፡
በመጨረሻም
ሁሌም አያቴ የሰውን ውለታ እንዳልበላ
የሚከላከል አንድ ቃል ትናገረኛለችለ “የፈረሱን
ለፈረስ፤ የአህያውን ለአህያ ስጥ” ትለኝ ነበር፡
፡ ዛሬ እኔም የለንደኑ ጉዞዬ በስኬት ተጀምሮ
በስኬት እንዲጠናቀቅ በተለያየ መንገድ
አሻራችሁን ላሳረፋችሁ፤ የዚህ ታሪክ አካል
እንድሆን ያደረጋችሁትን በሙሉ በውስጤ
አብሮኝ ባደገው የአያቴ መመሪያ መሰረት
ለመልካሙ ስራችሁ ባርኔጣዬን ከፍ በማድረግ
እጅ እነሳለሁ፡፡ በዚህም መሰረት በዋናነት የድል
(ቪክ ኦሎምፒያ) ባርና ሬስቶራንት ባለቤት አቶ
ደግአረገ ተሾመ (ቪክ)፣ ቃላቶች ሁሉ ቢደረደሩ
ስለ መልካሙ ስራችሁ አቅም የሚያንሳቸው
በለንደን የምትኖሩ ባለውለተኛዎቼ አቶ አክሊሉ
ነጋሽ (ዴቪድ)፣ ከኤርፖርት በወንድማዊ
ፍቅር ተቀብለህ የሸኘኸኝ አቶ ግርማ፣ በለንደን
ባይተዋርነት እንዳይሰማን በየዕለቱ ክትትልና
ድጋፍ ያደረጋችሁልን አቶ ዘውድነህ (ካፒቴን)፣
ወጣት ኤፍሬም፣ ደራሲ ጌታቸው አያልቄ፣
ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ መሆናቸውን
የሚሰብከው የማሳዋ ምግብ ቤት ባለቤት አቶ
ፍስሀ ብርሃኔ እንዲሁም ስስት የሌለው ፈገግታን
በመልካም መስተንግዶ አጅበህ ላስተናገድከኝ
የአይኒ ኢንተርኔት ካፌና ሬስቶራንት ባለቤት
አቶ ገረመው ሀይሉ፣ እንዲሁም በለንደን
ነዋሪ የሆነውና ከዌስትሀም ጋር በአጋርነት
የሚሰራው Alvin Grant በኢትዮጵያዊነት
ለታነፀው አጋርነታችሁ በራሴ እና በአንባቢዎቼ
ስም የማመሰግናችሁ አምላክ ወሮታችሁን
ይክፈል በሚል ማሰሪያ ቃል ጭምር ነው፡፡
ያለ እናንተ ድጋፍ የለንደኑ
ጉዞዬ የማይታሰብ ነው
“ወደ ለንደን የምትጓዘው ሀገራዊ ውክልናን
ይዘህ ነው፤ ጋዜጠኞችን ማገዝ ሙያውን ማገዝ
ነው” በሚል የተቀደሰ ሀሳብ ወደ ለንደን ተጉዤ
የዚህ ታሪክ አካል እንድሆን የልምድና የዕውቀት
ሽሽግር እንዳገኝ አጋርነታችሁን ላሳያችሁኝ
የሁልጊዜም ተባባሪያችን የሆነው የሞሀ ለስላሳ
መጠጦች ኢንዱስትሪ አ.ማ ዋና ስራ አስፈፃሚ
አቶ ጌታቸው ቢርቦ፣ በአጭር ጊዜ የባንኮችን
ኢንዱስትሪ ተቀላቅሎ ከዕድሜው የገዘፈ
ዕምርታን ያሳየው የብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ
ፕሬዝዳንት አቶ አብርሀም አላሮ፣ የማርኬቲንግ
ክፍል ሀላፊው አቶ የኋላሸት ካሳ፣ ሁልጊዜም
ለሰዎች ቅን፣ በጎ አሳቢና አጋር በመሆን
ተለይተው ለሚታወቁት የካንትሪ ትሬዲንግ
ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ለሆኑት ለአቶ
ቢኒያም ያለ እናንተ ድጋፍ የለንደኑ ጉዞዬ
የማይታሰብ ነው፡፡ ላደረጋችሁልኝ ድጋፍ
ከልብ እያመሰገንኩ ሀገራዊ ጥያቄዬን ችላ
በማለት ፊት የነሳችሁኝን ደግሞ አምላክ ልቦና
ይስጣችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡