ካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫን ለአምስተኛ ጊዜ አንስታለች። እሁድ ፍጻሜውን ባገኘው የጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ ግብፅ እና ካሜሩን ለዋንጫ ቀርበው በካሜሮን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል።
በጨዋታው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን (ፈረኦኖች)ቀደመው በ22ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረው መምራት ችለው ነበር።
በጉዳት ምክንያት ሁለት ጨዋታ ያለፈው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን አማካይ መሃመድ ኤል-ኒኒ በጥሩ መልኩ ከመሃመድ ሳላህ የተቀበለውን ኳስ አስቆጥሮ ግብፅን በመጀመሪያው አጋማሽ መሪ ማድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ሆኖም ግን በሁለተኛው አጋማሽ የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን (ማይበገሩት አንበሶች) ሙሉ ለሙሉ ተጭነው በመጫወት በጫወታው ላይ ብልጫ ወስደዋል።
ካሜሮንን ከግብፅ ጋር አቻ ያደረገችው ጎልም በ58ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ኒኮላስ ንኮሉ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።
የግብፅ ብሄራዊ ቡድን (ፈረኦኖች) ጨዋታው በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ በመከላከል ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።
መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩ ተቀይሮ ወደ የገባው ቪንሶን አቡበከር በ88ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ጎል ካሜሮንን ሻምፒዮን ማድረግ ችሏል።
በዚህም መሰረት የማይበገሩት አንበሶች ካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫን ሰባት ጊዜ ያነሱትን የግብፅ ብሄራዊ ቡድን ፈርኦኖችን በመርታት የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ሆነዋል።
በትናንት ምሽቱ የፍጻሜ ጨዋተታም ካሜሮን ከ15 ዓመታት በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ የአፍሪካ ዋንጫን ማሸነፍ ችላለች፡፡
ካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫን ስታነሳ የአሁኑ አምስተኛዋ ነው።
በ31ኛው የቶታል የአፍሪካ ዋንጫ ሶስት ጎል ብቻ የገባበት የ44 ዓመቱ የግብ ጠባቂ ኤሳም ኤል-ሃዳሪ የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ የተመጠረ ሲሆን፥ የካሜሮኑ አጥቂ ክሪስቲያን ባሶጎግ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡
በተያያዘ ቅዳሜ ምሽት የተደረገው የደረጃ ጨዋታም ቡርኪና ፋሶ ጋናን 1ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ 3ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች።
እንዲሁም በውድድሩ ጋና 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።