በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር የጅቡቲውን ጅቡቲ ቴሌኮምን በቅድመ ማጣሪያው የመልስ ጨዋታ አስተናግዶ 2-2 የተለያየ ሲሆን በድምር ውጤት 5-3 አሸንፎ ቀጣዩን ዙር መቀላቀል ችሏል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ለማግኘት 1ደቂቃ ብቻ ነበር። 1ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋር ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ የጅቡቲ ቴሌኮሙ መሐዲ ሁሴን አስቆጥሮ ክለቡን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላም ጅቡቲ ቴሌኮሞች ሁለተኛ ግብ ለማግኘት ጅማ አባጅፋርን ተጭነው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ይህንንም ተከትሎ 15ኛው ደቂቃ ላይ የጅቡቲ ቴሌኮሙ ፋቲአ አብዬደን ከሳጥን ውጪ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥታለች።
ከዚህች ሙከራ 2 ደቂቃዎች በኋላ ጅማ አባጅፋር አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 19ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ዲዲዬ ለብሪ ከፍፁም ቅጣት ሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደግብ የላካትን ኳስ የጅቡቲ ቴሌኮሙ ግብ ጠባቂ ሲተፋው በቅርብ ርቀት የነበረው ማማዱ ሲዴቤ ወደ ግብነት ቀይሯት ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከአቻነት ግቡ በኋላ ባለሜዳዎቹ ጅማ አባጅፋሮች ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። 27ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ዲዲዬ ሊብሬ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ኤልያስ አታሮ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቶበታል። ከዚህም ሙከራ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ይሄ ነው የሚባል የረባ እንቅስቃሴም ሆነ ሙከራ ሳይደረግበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተጨማሪ ግብ በማስቆጠር አሸናፊ ለመሆን ከበድ ያለ ፉክክር አድርገዋል። ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ 10 ደቂቃዎች በኋላ 55 ደቂቃ ላይ ጅማ አባጅፋሮች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ይዘው የገቡትን ኳስ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ ያስፈረሙት ዲዲዬ ሊብሬ ወደ ግብነት ቀይሮት ክለቡን ከኋላ በመነሳት ቀዳሚ እንዲሆን አስችሎታል። ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላም ጅማ አባጅፋሮች ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመግደል ተጭነው የተጫወቱ ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ግን ማስቆጠር አልቻሉም።
ሆኖም ግን ጅማ አባጅፋር ግብ ካስቆጠረ ከ15 ደቂቃዎች በኋላ 70ኛው ደቂቃ ላይ ጅቡቲ ቴሌኮሞች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ፋአቲ አቢአዶን መቶት የጅማ አባጅፋሩ ግብጠባቂ ዳንኤል አጄይ ቢመልሰውም የተመለሰውን ኳስ ራሱ ፋአቲ አቢአዶን አስቆሮት ክለቡ ጅቡቲ ቴሌኮሞን አቻ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታ የመጨረሻዎቹ 20ደቂቃዎች እጅግ አሰልቺ እና የማይስብ ጨዋታ ተከናውኖ ጨዋታው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል። በመጀመሪያው ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ወደ ጅቡቲ ተጉዞ 3-1 ማሸነፉን ተከትሎ በድምር ውጤት 5-3 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል። በቀጣዩ ዙርም ታህሳስ 6 2011 ዓ.ም ካይሮ ላይ የግብፅ እና የአፍሪካውን ሀያል ክለብ የሚገጥም ሲሆን በሳምንቱ አ/አ ላይ የመልስ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ